በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ዙሪያ በሚገኙ አራት ቀበሌዎች ቁጥራቸው በትክክል ያልታወቀ በርካታ ንጹሐን ዜጎች የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ለህልፈተ ሕይወት መዳረጋቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ደራ ወረዳ ዳግም በተከፈተ ጥቃት ከሰኔ 19/2014 ጀምሮ በከባድ መሣሪያ እየተናጠች ነው የሚሉት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ በወረዳው ስር በሚገኙ ባቡ ድሬ፤ አሙማ ግንደ (በተለምዶ ራቾ)፤ ዕሮብ ገበያ እንዲሁም ግንደ በርበሬ በሚባሉ ቀበሌዎች ያሉ ነዋሪዎች እየተገደሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ያንን ተከትሎ በነበረ የተኩስ ልውውጡ ከ33 በላይ የሚሆኑ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ተገድለዋል ያሉት ነዋሪዎቹ፤ በወገን በኩል ኹለት ሚሊሻዎች መሞታቸውንም ነው አዲስ ማለዳ የሰማችው።
ነዋሪዎቹ እስከ አሁን (ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት እለት ድረስ) በአካባቢው የተኩስ ልውውጥ መኖሩን የጠቀሱ ሲሆን፤ ይህን ተከትሎም የሟቾች ቁጥር በትክክል አልታወቀም ብለዋል። ዘገባው እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ግን ኹለት ንጹሐን ሰዎች መሞታቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በእነዚህ አራት ቀበሌዎች በአራት አቅጣጫ በተከፈተው የተኩስ ልውውጥም ዘገባው እየተዘጋጀ በነበረበት ወቅት የከባድ መሣሪያ ድምጽ እንደሚሰማ ነው አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ የተነገራት።
በሌላ በኩል፣ ከጉንደ መስቀል ደራ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ የነበሩ 260 ተሳፋሪዎች በታጣቂ ቡድኑ ሰላላ ተብሎ ከሚጠራው ቦታ ታግተው የነበረ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል ስምንቱ ያሉበት እንደማይታወቅ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
ታጣቂ ቡድኑ ስምንት ታጋቾችን ያስቀረ ሲሆን፤ ቀሪዎቹን ብር እያስከፈለ መለቀቃቸውንም የአዲስ ማለዳ ምንጮች ተናግረዋል። ተሳፋሪዎቹ ኦነግ ሸኔ አግቶ በወሰዳቸው ወቅት ከእያንዳንዱ ተሳፋሪ ከ1ሺሕ 500 ብር በላይ ነው ያስከፈሏቸው ተብሏል።
የመከላከያ ሠራዊት ጦርነቱ ከተጀመረ አራት ቀን ዘግይቶ ነው የገባው ያሉት ነዋሪዎቹ፤ ቀድሞ ገብቶ ቢሆን ታጣቂ ቡድኑ ወደ ነዋሪዎቹ የመግባት እድል አያገኝም ነበር ብለዋል።
በጦርነቱ በተለይም ሴቶች፤ ሕጻናትና አዛውንቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል የተባለ ሲሆን፤ የአካባቢው ነዋሪ እንስሳትም በታጣቂ ቡድኑ ተዘርፈዋል ሲሉ ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።
ነዋሪዎቹ እንደገለጹት ከሆነ፤ ታጣቂ ቡድኑ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ጥቃት ሲሰነዝር አሁን ለአራተኛ ጊዜ ሲሆን፤ ሰሞኑን ያለው ጦርነት የተባባሰው የኦነግ ሸኔ ታጣቂ መሪ የነበረው ጃል ገለታ ንጉሤ በአካባቢው ሚሊሻዎች መገደሉን ተከትሎ ነው።
በአበቴ ወረዳ በኩል ያለው መንገድ ለተከታታይ ስምንት ወራት ተዘግቶ መቆየቱን ያስታወሱት ነዋሪዎቹ፤ በሰላሌ በኩል አድርጎ ወደ አማራ ክልል መውጣት አይቻልም ነበር ብለዋል።
አሁን ላይ የመከላከያ ሠራዊት ወደ ደራ ወረዳ ማቅናቱን ተከትሎ በነዋሪዎች ላይ ጥቃት የሚያደርሰው ታጣቂ ቡድኑ ኃይሉ እየቀነሰ ነው ተብሏል። ታጣቂ ቡድኑ ወደ ጀማ ወንዝ መጠጋቱ የተመላከተ ሲሆን፤ ክረምቱን ተከትሎ ወንዙ በመሙላቱ ቁጥራቸው ያልታወቀ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በጎርፍ መወሰዳቸው ሌላኛው ቡድኑን ያዳከመው ክስተት ነው ብለዋል ነዋሪዎቹ።
በሌላ በኩል፣ በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ባሳለፍነው ሰኔ 11/2014 ሽብርተኛ ተብሎ በተፈረጀውና ራሱን የኦሮሞ ሕዝብ ነጻ አውጭ ቡድን ብሎ በሚጠራው ቡድን እስከ 32 የቤተሰብ አባላት የተገደሉባቸው ሰዎች የአእምሮ ጤናቸው በከፍተኛ ሁኔታ እንደተቃወሰ ተሰምቷል።
እነዚሁ ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸው ሰዎች አእምሮአቸውን ስተው በገመድ ታስረው ቢቀመጡም፣ የሕክምና እርዳታም ማግኘት አልቻሉም ነው የተባለው።
የደራ ወረዳ አስተዳዳሪ ውብሸት አበራ በወረዳው በተከፈተው ተኩስ ልውውጥ ስላለው ሁኔታ ያላቸውን ምላሽ ለመስጠት ያሉበት ሁኔታ እንደማይመች ጠቅሰው ቀጠሮ ሰጥተዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 191 ሰኔ 25 2014



