በጋምቤላ ክልል 80 ወጣቶች በታጣቂዎች ታግተዋል

0
1368

ኹለት የኢንቨስተሮች ካምፖች ተቃጥለዋል ተብሏል

በጋምቤላ ክልል ኢታንግ ልዩ ወረዳ ሜራ ቀበሌ በቀን ሥራ የተሰማሩ 80 ወጣቶች በጋምቤላ ነጻ አውጪ ንቅናቄ ታጣቂዎችና በኦነግ ሸኔ መታገታቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

የቀን ሠራተኞቹ ከታገቱ አምስት ቀን ቢያስቆጥሩም፣ እስከ አሁን ያሉበት ሁኔታ አይታወቅም ሲሉ ከአካባቢው ነዋሪዎች መካካል ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ የአዲስ ማለዳ ምንጮች ተናግረዋል።

በታጣቂዎች የታገቱት 80 ወጣቶች መሆናቸውን ነዋሪዎቹ የገለጹ ሲሆን፤ ታጣቂ ቡድኑ እገታውን ያከናወነው በጋምቤላ ክልል እና በቄለም ወለጋ መካከል በምትገኘው ኢታንግ ልዩ ወረዳ ሜራ ቀበሌ መሆኑንም አብራርተዋል።

ታጋቾቹ ከታገቱበት ጊዜ ጀምሮ በሕይወት መኖራቸውና አለመኖራቸውን ማወቅ አልተቻለም ያሉት ነዋሪዎቹ፤ የእገታ ጥቃቱ የተከሰተው ባሳለፍነው ሰኔ 20/2014 መሆኑንም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ወጣቶቹ በታጣቂ ቡድኑ የእገታ ጥቃት የደረሰባቸው በኹለት የባለሀብት የእርሻ ማሳዎች ላይ በጉልብት ሥራ በተሰማሩበት ወቅት ነው። የእገታ ጥቃቱ የተከናወነው ከሰዓት በኋላ ነው የተባለ ሲሆን፤ ኹለት የኢንቨስተሮች ካምፖችም የቃጠሎ አደጋ ደርሶባቸዋል ነው ያሉት ነዋሪዎቹ።

ባለ ካምፖቹ ከዚህ በፊት በሁመራ የነበሩና በጦርነት ምክንያት ሁመራን ለቀው በኢታንግ ልዩ ወረዳ ሰፍረው የነበሩ የአማራ ተወላጅ ኢንቨስተሮች መሆናቸውን ነዋሪዎቹ አብራርተዋል።

የኢንቨስተር ካምፖቹ ሲቃጠሉም በውስጡ የነበሩ የተለያዩ መሣሪያዎች አብረው ከጥቅም ውጪ ሆነዋል ተብሏል። በካምፖቹ ውስጥ የነበሩ የእርሻ ማረሻ ተሽከርካሪዎችና የእርሻ ማዳበሪያዎች በቃጠሎው ምክንያት ከጥቅም ውጭ የሆኑ ንብረቶች መሆናቸውንም ነዋሪዎቹ ለአብነት ጠቅሰዋል።

በቀን ሥራ የተሰማሩትን ወጣቶች አግተዋል የተባሉት ታጣቂዎቹ፤ ታጋቾቹን ወደ ቄለን ጫካ እንደወሰዷቸው ቢታወቅም፣ የአካባቢው ሚሊሻና ልዩ ኃይል ጉዳዩን ለመከታተል ሞክረው ከአቅማችን በላይ ነው ብለው ተመልሰዋል ሲሉ ነው ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት።

አካባቢው ሜዳማና ወደ ጋምቤላ ክልል፤ ወደ ቄለን ወለጋ እንዲሁም ወደ ደቡብ ሱዳን የሚያዋስን ስለሆነ ለጥቃት ምቹ ነው ያሉት የአዲስ ማለዳ ታማኝ የመረጃ ምንጮች፤ ታጣቂ ቡድኑ ያገታቸውን ሰዎች ጉዳት ሳያደርስባቸው ማግኘት ከባድ እንደሆነ አንስተዋል።

ኦነግ ሸኔ በጋምቤላ ከተማ፤ በደንቢ ዶሎ እንዲሁም ባሳለፍነው ሰኔ 11/2014 በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ያደረሳቸውን ጥቃቶች ያስታወሱት የአዲስ ማለዳ ምንጮች፣ አሁን ደግሞ ጥቃት የተከፈተባቸው ራሳቸውን የጋምቤላ ሕዝብ ነጻ አውጭ ንቅናቄ ብለው የሚጠሩ ታጣቂዎች ከኦነግ ሸኔ ጋር በመተባባር ነው ብለዋል።

ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከሆነ፤ የጉልበት ሠራተኞቹ የታገቱት የአማራ ተወላጅ ናችሁ ተብለው ከሌሎች ሠራተኞች መካከል እየተመረጡ ነው።

የጉልበት ሠራተኞቹ ያሉበት ሁኔታ ስጋት ያሳደረባቸው ነዋሪዎቹ፤ የሚመለከተው አካል ጉዳዩን እልባት እንዲሰጠው አሳስበዋል። ወጣቶቹን ያገታቸውና የላቀ ኃይል ያለው የኦነግ ሸኔ ታጣቂ መሆኑንም ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳ የጋምቤላ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ኦገቱ አዲንግ ለተከሰተው ችግር ምን መፍትሄ እየተወሰደ እንደሆነ ምላሽ ለማግኘት ያደረገችው ሙከራ አልተሳካም። ሙከራው ያልተሳካው ኃላፊው ስልካቸውን አንስተው ምላሽ ሳይሰጡ በመዝጋታቸው ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 191 ሰኔ 25 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here