በታቦር ተራራ የ200 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ

0
1884

የሐዋሳ ከተማ ልዩ መለያ የሆነውን ታቦር ተራራ ለማልማት የ200 ሚሊዮን ብር ‹ፋሮ ፕላዛ› የተሰኘ ፕሮጀክት እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ።
በታቦር ተራራ ላይ የሚገነባው ፋሮ ፕላዛ የተሰኘው ይህ የግንባታ ፕሮጀክት የተጀመረ ሲሆን፣ የፕላዛው ግንባታ አሁን ላይ በቆረጣና ቁፋሮ ሂደት ላይ እንደሚገኝ የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ፀጋዬ ተክሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ይህ ፕሮጀክት አገርኛ የኪነ ሕንፃ ታሪክን ወደ መሬት ለማውረድ የሚደረግ ጥረት አንድ አካል መሆኑን የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፣ ፕሮጀክቱ ከዓለም ባንክ በተገኘ በጀት የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ባለቤትነት የሚሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ የሲዳማ ሕዝብ ጉንጭ ለጉንጭ በመሳሳም በሚጨፍርበት ‹ፋሮ› ጭፈራ የተሰየመ መሆኑም ተሰምቷል። የሲዳማ ሕዝብ የ‹ፋሮ› ጭፈራ ጽንሰ ሐሳብ እርግቦች እርስ በእርስ ፍቅር ለመለዋወጥ ከሚያደርጉት መሳሳም የመጣ በመሆኑም፣ ፕሮጀክቱ ይህን የሚያንጻባርቅ የርግብ ዲዛይን እንዳለው ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

እንዲሁም አንፊ ቲያትር እንደሚኖረው የጠቀሱት ሥራ አስኪያጁ፣ የሲዳማ ሕዝብ ባህላዊ መገለጫ ይዘቶችን የያዘ እና ኢትዮጵያ ውስጥ ከተሠሩ የተራራ ላይ ደረጃዎች የተለየ የ‹ዳያመንድ› ቅርጽ ያለው ደረጃ ይኖረዋል ነው ያሉት።

የፋሮ ፕላዛ ዲዛይን ቀድሞ የታሰበው ፈርሶ እንደገና እንደተሠራ ገልጸውም፣ ሰው ወደ ተራራው በቀላሉ እንዲወጣ ከሚያደርጉት ደረጃዎች በተጨማሪም አስፈላጊ መሠረት ልማቶች የሚሟሉለት እንደሚሆን ጠቅሰዋል። ለአብነትም የባህል አዳራሾች፣ የሕጻናት መዝናኛዎች፣ የውሃ ፓርክና የማንበቢያ ቦታዎችም እንደሚኖረው ነው ያብራሩት።

ፕሮጀክቱ በመንግሥት ባለቤትነት የሚሠራ በመሆኑም የቦታ ችግር እንደሌለበት አንስተው፣ ወደፊት በግንባታ ወቅት በሚደረጉ የዲዛይን ማሻሻያዎች የሚሄድ ተራራውን ማእከል አድርጎ እየተሠራ ያለ ነው ብለዋል።

ይህ ፕሮጀክት በታቀደው ልክ የሚሄድ ከሆነ፣ ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ነው የተባለው። ታቦር ተራራ በኹሉም አቅጣጫ ከተማዋን የሚያስቃኝ በመሆኑ የተራራው መልማት ለቱሪዝም ፍሰቱ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው የተባለ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ የሲዳማን ሕዝብ ባህል ታሪክና ትውፊት ከማስተዋወቅ ባሻገር በርከት ያለ የሥራ እድል እንደሚፈጥርም ተመላክቷል።

በከተማዋ የሚገኘውን ፍቅር ሐይቅ መሠረት ያደረገና የዲዛይን ሥራው 70 በመቶ የተጠናቀቀ በመጪው ዓመት መስከረም ወር ይፋ የሚደረግ ሌላ የሐይቅ ዳር ፕሮጀክት እንዳለም ተመላክቷል።

በቅርቡም ጥቁር ውሃ ተብሎ በሚጠራው የከተማዋ መግቢያ በር በኩል በአንድ ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለና 100 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ የተነገረለት የሐዋሳ ከተማ የመግቢያ በር ፕሮጀክት ግንባታ እንደተጀመረ መገለጹ አይዘነጋም። ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁም፣ የሀዋሳ ከተማ ገጽታን በማሻሻል የበለጠ የቱሪዝም ከተማ እንድትሆን እንደሚረዳ ተስፋ ተደርጓል።


ቅጽ 4 ቁጥር 191 ሰኔ 25 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here