የአየር ንብረት ለውጥና ወጥነት የሌለው የአየር ፀባይ

0
2006
© SANDILE NDLOVU

የአየር ንብረት ለውጥ ዓለማችንን ስጋት ውስጥ ከሚከቱ የተፈጥሮም ሆኑ ሰው ሠራሽ ምክንያቶች በቀዳሚነት የሚቀመጥ ነው። ይህ ለውጥ በሰው ሠራሽ ምክንያት እየተባባሰ ነው የሚሉ የተመራማሪዎች ምልከታ አሁን አሁን በርካቶች እየተቀበሉት ቢሆንም፣ የተፈለገውን የተግባር ለውጥ ለማምጣትና ሂደቱን ለማሻሻል አስፈላጊ የሆኑት ፖለቲከኞች ግን ሲያመነቱ ይታያል።

የምርጫ ሰሞን ደጋፊን ለማግኘት በሚካሄድ ቅስቀሳ፣ ታዳሽ የኃይል ምንጮችን ለመጠቀምና የመንግሥት ትኩረትን ወደ ተፈጥሮ ለማዞር የሚገቡ ቃልኪዳኖች ሥልጣን ከተያዘ በኋላ ተግባራዊ ሲደረጉ አይስተዋልም። የኢኮኖሚ መናጋትና የባለሀብቱ ጫና እያሳሰባቸው ፖለቲከኞቹ ብዙዎችን ስጋት ላይ ለጣለው የአየር ንብረት ለውጥ ጆሯቸውን መስጠት አይፈልጉም። ይህ ቢሆንም ግን ተመራማሪዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች አሁንም ከምርምር ሥራዎቻቸውም ሆነ ከውትወታቸው አልቦዘኑም።

የሰው ልጆች ተግባር ለአየር ፀባይ መቀያየር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል ብለው የሚያምኑ ግለሰቦች፣ የአየር ንብረት ለውጥ እንዲከሰት የሚያደርጉ የሰው ልጆች ተግባራት እንዲቀየሩ አልያም ቢያንስ ለወደፊት እንዲሻሻሉ ይጠይቃሉ። በካይ ጋዞችን ወደ አየር የሚለቁ ኩባንያዎችም ሆኑ መንግሥታት ለለውጡ አስተዋፅኦዋቸው የጎላ እንደመሆኑ ሊጠየቁ ይገባልም ይላሉ። ሆኖም፣ ቀጥተኛ ማስረጃ አምጡ እየተባሉ የሚያቀርቡት የምርምር ውጤት ውድቅ ሲደረግባቸው ቆይቷል።

ይህ ስለሆነባቸውም፣ ያመኑትንና ያወቁትን ሕዝብ እንዲረዳቸው ሲሉ ከመቀስቀሳቸው ባሻገር፣ አሁንም ቢሆን የተለያዩ ጥናቶችን መሠረት በማድረግ የሰው ልጆች ተግባርና የአየር ንብረት ለውጥ ግንኙነታቸውን ለማረጋገጥ ይጥራሉ። ለዚህም ይረዳቸው ዘንድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተበራከቱ ያሉ ድንገተኛ የአየር ፀባይ ክስተቶችን ለማጥናት ተገደዋል። ከተለመደው መጠናቸው በጣም የተቀየሩ የአየር ፀባይ ለውጥ ክስተቶችን በማየት፤ ለተባባሱ ሁኔታዎች የሰው ልጆች ተግባር ምክንያት መሆኑን ለማወቅ መጣራቸውን አላቋረጡም።

የጎርፍና መጥለቅለቅ አደጋ መበራከት፣ የአውሎ ንፋስ መብዛት፤ “ሂት ዌቭ” የሚባለው የከፍተኛ ሙቀት መጠን መጨመር፤ የድርቅ መደጋገም፣ የዝናብ መጠን መዛባት እንዲሁም የወቅቶች ያለጊዜያቸው መቀያየርን በማጥናት፣ እነዚህ ክስተቶች ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ያላቸውን ዝምድናና ግንኙነት ለማወቅ እንደቻሉ ይናገራሉ።

በያዝነው ሳምንት የእንግሊዝ ተመራማሪዎች ይፋ ባደረጉት የጥናት ውጤት፣ እየበዙ የመጡ የተዛቡና የከረሩ የአየር ፀባዮችን ለይቶ በማጥናት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማወቅ መቻላቸውን ያስረዳሉ። የሰው ልጆችን ሕይወት ፈተና ላይ የጣሉና ለትንበያ ምቹ ያልሆኑ የተፈጥሮ ክስተቶች መነሻ ዋናው የሰው ልጆች ተግባር እንደሆነ ለማሳወቅም ጥናቶቹ ማስፈለጋቸው ተነግሯል።

የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ፣ የለንደን ኢምፔሪያል ኮሌጅና የዊሊንግተኑ ቪክቶሪያ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በጋራ በመሆን፣ አምስት ዋና ዋና የከረሩ የአየር ፀባይ ክስተቶችን (extreme weather events) በመለየት አጥንተዋል። ተመራማሪዎቹ ስለክስተቶቹ እንደ አዲስ ሳይሆን ያጠኑት ከዚህ በፊት በተለያዩ ተቋሞችም ሆኑ ግለሰቦች የተካሄዱ የተናጠልም ሆነ አጠቃላይ ጥናቶችን እያነፃፀሩ በማየት ነው። ለዓመታት ተጠንተው መደርደሪያ ላይ ተሰቅለው የቀሩ የጥናት ውጤቶችን በመገምገም፣ እርስ በርሳቸው ያላቸውን ግንኙነትና ልዩነት በማጥናት ክስተቶቹ የተፈጠሩት በሰው ሠራሽ ምክንያት በመጣው የአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ስለመሆኑ ለማረጋገጥ አስችሏቸዋል።

ለምሳሌ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየበዛና መጠኑ እየጨመረ ስለመጣው ከፍተኛ የሙቀት ሞገድ የተጠኑትን ጥናቶች በመለየት፤ ማስረጃዎችን በማጠናከር ግንኙነቱ ቀጥተኛ እንደሆነ ለማመላከት መቻላቸውን ይናገራሉ። በጥናት ውጤቱ መሠረት፣ ግንኙነቱ ክፍተት የሌለው መቶ በመቶ የታወቀ ነው ማለት እንደማይችሉ የጠቆሙት ተመራማሪዎች፣ የጎደለውን ክፍተት የሚሞላ ተጨማሪ ጥናት እስኪደረግ ቀዳዳዎቹን የሚያጠብና ግልፅ መልዕክት የሚያስተላልፍ የጥናት ግኝት መሆኑን ለማሳየት ሞክረዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ በሰው ልጆች ላይ ያስከተለው የጉዳት መጠን ተለይቶ በማይታወቅበት ሁኔታ፣ የከረሩ የአየር ፀባይ ክስተቶች መነሻ የሰው ልጆች ተግባር የቀየረው የአየር ንብረት ለውጥ ስለመሆኑ በርካታ ምሁራን ይስማሙበታል። ይህ ቢሆንም፣ ፖሊሲ አውጪ መንግሥታትም ሆኑ የመድን ዋስትና ሰጪዎች እንዲሁም የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ስለለውጡ ያላቸው ግንዛቤ ያን ያህል አይደለም። በመሆኑም የዓለም ተመራማሪዎች በሙሉ የሚስማሙበትን የአየር ንብረት ለውጥ ከግምት ሳያስገቡ ውሳኔ እንደሚያስተላልፉ መመልከት ይቻላል።

የሰው ልጆችን የወደፊት እጣ ፋንታ የሚወስኑ ትልልቅ ውሳኔዎችን በተመለከተ፣ አማካሪዎችም ሆኑ ውሳኔ ሰጪዎች አስቀድመው ሊያውቁ የሚገባቸውን መረጃዎች እንዲያምኑ እንዲህ ዓይነት ማስረጃ የሚያስገኙ ጥናቶች ጥቅማቸው ተመላክቷል። እየተበራከቱ ለመጡት የአየር ፀባይ ለውጦች የሰው ልጆች ተግባር ምን ያህል አስተዋፅኦ እንዳለው ምርምሩ ያሳያል ሲሉ መናገራቸውንም አይ.ኦ.ፒ (IOP Publishing) አስነብቧል።

እንደጥናቱ ከሆነ ተለይተው ጥናት የሚደረግባቸው የከረሩ የአየር ፀባይ ክስተቶች እንደዓይነታቸው የተለያየ ውጤት አስገኝተዋል። ለምሳሌ ሂት-ዌቭ የሚባለው የታመቀ የሞቃት አየር ሞገድ በሁሉም ቦታ ተመሳሳይ ውጤት የተገኘበት ሲሆን፣ በዓለም ዙሪያ የሚከሰተው ሁሉም መነሻው የአየር ንብረት ለውጥ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል።

በተቃራኒው ሳይክሎንና ሄሪከን በመባል የሚታወቁትና ከውቅያኖስ ተነስተው ወደ ምድር ዘልቀው ጉዳት የሚያመጡት አውሎ ነፋሶች እንደአካባቢውና ጊዜው የተለያዩ ውጤቶችን አስመዝግበዋል። ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ይልቅም በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጠናቸውና ብዛታቸው በ13 በመቶ መቀነሱን አንድ ሌላ ጥናት መጠቆሙን ኔቸር ኤዢያ አሳውቋል።

ጎርፍ የሚያስከትሉ ዝናቦች መጠናቸው እያደር መጨመሩ እንዲሁም የሙቀት መጨመርና ድርቅ መከሰትን የመሳሰሉ የተፈጥሮ ክስተቶች በሰው ሠራሽ ምክንያት በመጣ የአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ መከሰታቸውን በእርግጠኝነት ማወቅ ከተቻለ፣ ሂደቱ አስቀድሞ እንዲታወቅና ጉዳት ሳያስከትሉ የቅድሚያ ዝግጅት በማድረግ የሰው ሕይወትንም ሆነ ኢኮኖሚን መታደግ ስለሚያስችል ጥናቶቹ ጠቀሜታቸው የጎላ ነው ተብሏል።

የካርቦን ልቀትን ማብዛት ከሚያስገኝልን ጥቅም አንጻር በሚከሰቱ ድንገተኛ የአየር ፀባይ መለዋወጦች የሚመጣውን ጉዳት በማነፃፀር፤ የትኛው የበለጠ ጉዳት ያስከትላል በሚል ፖለቲከኞች ትክክለኛ ውሳኔ ላይ በጊዜ እንዲደርሱ ያስችላቸዋል ሲሉ ነው ተመራማሪዎቹ የተናገሩት።

ስለአየር ንብረት ለውጥ የተደረጉ ምርምሮችም ሆኑ ጥናቶች ትኩረት አድርገው የሚካሄዱት ያደጉ አገራትን እንደመሆኑ ለወደፊት አድማሱን ለማስፋት መታሰቡም ተነግሯል። ለውጡ ባስከተላቸው ክስተቶች ይበልጥ ተጎጂ የሆኑት ድሃ የሚባሉት ያላደጉ አገራት እንደመሆናቸው፣ እነሱን ማዕከል ያደረጉ ጥናቶች ለወደፊቱ በሰፊው መሠራት እንዳለባቸው ተመላክቷል።

እነዚህ በማደግ ላይ ናቸው የሚባሉ አገሮች ስለአየር ንብረትም ሆነ ስለፀባዩ ትክክለኛና በቂ የሆነ መረጃን ስለማይዙ ይህን እንዲያስተካክሉና የበኩላቸውን ማስረጃ ለማቅረብ እንዲሠሩም ተጠይቋል። የችግሩ ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ እንደመሆናቸው፤ አቅማቸው በፈቀደ መጠን ለጉዳዩ ትኩረት ካልሰጡት ለማደግ በሚያደርጉት ጥረት ችግሩን እያባባሱት እንደሚሄዱም ተጠቁሟል።

ደቡብ አፍሪካን በመሳሰሉ አገራት ሙስና ባስከተለው ችግር ምክንያት ትክክለኛ መረጃ እንደማይያዝና የተበጀተውም ሀብት ያለአግባብ እንደሚባክን ተመላክቷል። ሶማሊያን በመሳሰሉ ወጥ የሆነ ሰላም በሌላቸው አገራትም የየወቅቱን መረጃ መዝግቦ ለማጠናቀር የሚያስችሉ መሠረት ልማቶች ስለማይኖሩ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ለማካሄድ አዳጋች ሆኗል ተብሏል።

ፖላንድን በመሳሰሉ ሀብታም አገራት ደግሞ መረጃዎች ቢኖሩም ለጥናት ማስረጃ የሚፈልጉ ባለሙያዎች ለመረጃዎቹ ከፍተኛ ገንዘብ ስለሚጠየቁ፣ ልፋቱን መና ሊያደርገው ይችላል ሲሉ የአገራት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተመራማሪዎቹ ጠቁመዋል።

የጥናቱ ዓላማ የሰው ልጆችን ተግባርና የአየር ንብረት ለውጥን ግንኙነት ከማረጋገጥ ባሻገር፣ ጉዳት እያመጡ የሚገኙ ክስተቶች የሚያስከትሉትን ጥፋት መቀነስ ነው። አስቀድሞ በመተንበይ ዝግጁ ሆኖ መጠበቅ፣ ተደጋጋሚነታቸውን መቀነስ፣ መንስኤያቸውን በማወቅ መጠናቸውንም ሆነ ግዝፈታቸውን ማሳነስ እንዲቻል እንዲሁም ከለውጦቹ ጋር አብሮ ለመኖርና ችግሮቹን ተቋቁሞ ሕይወትን እንዴት መግፋት እንደሚቻል ለማሳየት ነው ተብሏል።

ይህ ዓይነት ጥናት ለመድን ዋስትና ሰጪ ኩባንያዎች ከማገልገሉም በላይ፣ ለውጦቹን ተቋቁሞ ለመኖር የሚያስችለውን ወጪ ለማወቅ፣ አልያም አየር በካይ ጋዞችን የሚለቁት አካላትን በፍርድ ቤት ሞግቶ ለመርታት እንደግብዓት ይውላል ሲል ሳይንስ ሚዲያ ሴንተር ጥናቱ ላይ ተመርኩዞ መረጃውን አጋርቷል።

እርግጥ የሆነ መረጃ በሌለበት ሁኔታ ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል የተመላከተ ሲሆን፣ ለውጡ ያመጣቸው የከረሩ የአየር ፀባይ ክስተቶች ያስከተሉት ጉዳት እንዲሁም ምን ያህል ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳላቸው ጥናቶቹ ማመላከት ቢጠበቅባቸውም፣ ገና ብዙ መሠራት እንዳለበት ተነግሯል። በተለይ በከፍተኛ ሙቀት ሳቢያ የሚከሰቱ ድርቅና ሰደድ እሳቶች፤ ያለማቋረጥ በሚጥል ዝናብ አማካኝነት የሚፈጠሩ ጎርፎችና የውሃ መጥለቅለቆች እንዲሁም በአውሎ ነፋሶች አማካኝነት በሚፈጠሩ ውሽንፍሮች የሚጠፋው የሰው ሕይወት፣ እንዲሁም የሚወድመው ሀብት በዓለም ዐቀፍ ደረጃ መታወቅ ስለሚኖርበት መረጃ አያያዝ ላይ ትኩረት እንዲሰጥ ተጠይቋል።

መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ችግር ተረድተው የፖለቲካቸው አንድ አካል አድርገው ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት የሚያስከትለውን መዘዝ መቀነስ እንዲችሉ ጥሪ ቀርቦላቸዋል። የሚዲያ ሰዎችም ሆኑ በተለያየ ዘርፍ ላይ ያሉ ባለሙያዎችም የችግሩን አንገብጋቢነት ተረድተው፣ ኅብረተሰቡ እንዲዘጋጅም ሆነ ከአባባሽ ተግባራት እንዲቆጠብና የበኩሉንም ግፊት እንዲያደርግ መቀስቀስ ይጠበቅባቸዋል ተብሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 191 ሰኔ 25 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here