ጥያቄዋን ሥሙ!

0
1102

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

በኢትዮጵያ ያለው የሰላም ማጣትና ኹከት ማረፊያ ያለው አይመስልም። ብዙዎች በሕይወት ዋጋ ከፍለዋል። የተረፉ የመከራ ሕይወትን ሲገፉ፣ ደኅና ነን የሚለው ደግሞ በሥነልቦና በእጅጉ ስብራትና ጭንቀት ውስጥ ይገኛል።

ድርድር፣ ውይይት፣ ምክክር፤ አሁን ከሞትና እልቂት ዜናዎች በተጓዳኝ የምንሰማቸው ጉዳዮች ሆነዋል። በዚህም ጉዳይ ላይ መካሪዎች፣ ተሰብሳቢዎች፣ ተሟጋቾች…ሁሉንም ወንዶች ብቻ ይመስላሉ። የሰላም ሚኒስቴር ውስጥ ያሉት ሴት ሚኒስትር እንኳ የሌሉ ያህል ከደጃቸው ኮሽታ እንኳ እየተሰማ አይደለም።

በቅርቡ ወለጋ ላይ በተፈጸመ አሰቃቂ የሰዎች ግድያ፣ ሴቶችና ሕጻናት ኖረውም ሞተውም መከራውን በብዛት ተቀብለዋል። አሁንም በየክልሉ ባለው ሰላም ማጣት፣ ረሀብ፣ እንግልት፣ እንዲሁም የንጹሐን ደም መፍሰስ፣ በሁሉም በእያንዳንዱ ውስጥ የእናቶች እንባ እየፈሰሰ፣ መኖርንም ሆነ መሞትን ለመመኘት የማይመች ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑ ግልጽ ነው።

በዚህ መካከል መሀል ከተማ ላይ ድርድርና ስብሰባ እያለ የሚናገር ወንድ ብቻ ነው። ሴቶች ይሳተፉ ሲባል፣ ‹በምን መሳተፍ አማራችሁ!› ባዩ ጥቂት አይደለም። በሴቶች ጉዳይ ላይ የሚሠሩ ማኅበራት ‹እኛም እንሳተፍ› ብለው በጋራ መግለጫ ማውጣታቸውን ተከትሎ፣ ‹እነሱ ደግሞ ምን እንሁን ነው የሚሉት!› ብሎ ለመስማት ፈቃደኛ ባለመሆን እጁን በጆሮው የሚጭነው ጥቂት እንዳይደለ፣ በግል ገጠመኝ ሳይቀር መታዘብ ችያለሁ።

ወትሮም አንድ የሚያሰጋኝ ጉዳይ ነበር፤ የሴቶች ጥያቄ ቅንጦት ወይም ዘመናዊነት የወለደው ጥያቄ ተደርጎ መቆጠሩ። የሴቶች ጥያቄ የሕጻን ልጅ ከረሜላ ስጠኝ ዓይነት ጥያቄ የሚመስላቸው ወይም እንደዛ እንደመሰላቸው በሚያሳብቅ መልኩ ጥያቄውን የሚያስተናግዱ ሰዎች አሉ።

ልክ አይደለም! በድርድሩ ውስጥ ድምጽ ይኑረን ጥያቄ የቅንጦት አይደለም። ሁሌም እንደሚባለው፣ ይሄኔ ጾታ ብሔር ቢኖረው ኖሮ፣ ይህ ጉዳይ ተንቆ የሚተዉ ባልሆነ ነበር። በእርግጥ ደግሞ ይህ የብሔርም ሆነ የፖለቲካ ኹካታ ሲበርድ፣ የሴቶች ጉዳይ ወደኋላ ለመመለስ የማይቻልና እንደውም ምንአልበት ባህል፣ ታሪክ፣ ሀይማኖት ወዘተ የሚባሉ አጥሮችን ጥሎ ሊያልፍ የሚችል ጉዳይ እንደሚሆን እገምታለሁ። እናም ከወዲሁ ማዳመጥና ለጥያቄ መልስ መስጠት ተገቢ ነው።

የሴቶች ማኅበራት ቅንጅት በቅርቡ ያወጣው መግለጫና ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ፣ እንደ ኹለተኛ ጉዳይ ሳይሆን ቅድሚያ እንደሚሰጠው ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው ለማሳሰብ ፈልጌ ነው። ሕይወቷንም፣ ሕይወቴ የምትላቸውን ቤተሰብና ልጆቿንም እያጣች ያለች ሴት፣ በድርድሩም ሆነ በምክክሩ የመሳተፍ እድሏ፣ በትግል የሚገኝ ሳይሆን በተፈጥሮ የሚታወቅ ሊሆን የተገባ ነው።

ደግሞ እስቲ እንደው አዲስ ዕይታን እንስማ! ሥልጣኑንም፣ ጦርነቱንም፣ ክርክርና ድርድሩንም? ሁሉንም ይዛችሁታል፤ እስቲ ለሴቶች በሩን ከፈት አድርጉት!
ሊድያ ተስፋዬ


ቅጽ 4 ቁጥር 192 ሐምሌ 2 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here