የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ዓመታዊ የንባብ ቀን መርሃ ግብር ያካሄደውና በክረምቱ ንባብ ትኩረት እንዲሰጠው ለማድረግ ድምጹን ያሰማው በዚሁ ሳምንት ነበር። ማኅበሩ ባሳለፍነው ሐሙስ ሰኔ 30/2014 ነበር፤ በአብርኆት ቤተመጻሕፍት የንባብ ቀንን አስቦ፣ ንባብን በሚመለከትም የተለያዩ ሐሳቦችን ያጋራው።
ማኅበሩ ሰኔ 30 የንባብ ቀን እንዲሆንና መሆኑም ሰርጾ ሕዝቡ እንዲያስበው ለማስቻል ጥረት ማድረግ ከጀመረ ጥቂት ዓመታት አልፈዋል። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እለቱ የንባብ ቀን ሆኖ እንዲታወጅም እየሠራ ይገኛል።
በእለቱ ከተነሱ ሐሳቦች መካከል የሚበረታው፣ ለከንቱና ለማይረባ ጉዳይ ‹ሂድ!› ሲባል የሚሄድ ‹ና!› ሲባል የሚመጣ ትውልድ እንዲፈጠር ያደረገው የንባብ ባህል በማነሱ ነው የሚለው ነው። የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ፕሬዝዳንት አበረ አዳሙ በዝግጅቱ ላይ ሲናገሩም ይህን ነጥብ አንስተዋል። አያይዘውም ይህን ሁኔታ ለመቀየር የሚቻለው የንባብ ባህልን በማዳበርና በንባብ ነው ብለዋል።
አያይዘውም የሰኔ 30 የንባብ ቀን መታሰቡ፣ የንባብ ባህል እንዲዳብር በማድረግ አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር በማለም እንደሆነ ጠቅሰዋል። በተጨማሪም እለቱ መታወሱ ወቅቱ ትምህርት ቤቶች የሚዘጉበት እንደመሆኑ፣ ልጆችና ወጣቶች በሞባይልና በተለያዩ ስክሪኖች በኩል በዲጂታሉ ዓለም የሚያጠፉትን ጊዜ ቀነስ አድርገው፣ በንባብ የሚያሳልፉትን ጊዜ ጨመር እንዲያደርጉ ለማበረታታትም እንደሆነ ነው የጠቀሱት።
በዚሁ መሰናዶ ላይ አንጋፋ እንዲሁም ወጣቶች የንባብ ልምዳቸውን አጋርተዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 192 ሐምሌ 2 2014



