ኢትዮጵያ በየእለቱ የንጹሐን ዜጎች ደም የሚፈስባት አገር ሆናለች። ያም መስዋዕትነት መከራ አልበቃ ብሎ፣ የመከፋፈልና የመበታተን አደጋ ከፊቷ ተደቅኗል። ‹አምላኳ አይተዋትም!› የሚል እምነት በብዙዎች ዘንድ ያለ ቢሆንም፣ ሰዎች በተግባር እየሠራቸው ያሉ ነገሮችና እየተከሰቱ ያሉት ጦርነት እና እልቂት የመሳሰሉት ሁሉ፤ ተስፋን በእጅጉ መፈተናቸው አይቀርም። ግዛቸው አበበ በወለጋ በተከታታይ የደረሰውን የንጹሐን ሞት አውስተው፤ በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ እንድሚከተለው በዕይታቸው አስቃኝተዋል።
በዕለተ ሰኞና ማክሰኞ፣ ሰኔ 28 እና 29 ቀን 2014 ከወደ ወለጋ ሌላ የሰቆቃ ዜና ተሰማ። በቤታቸው የተቀመጡ ሰላማዊ ሰዎች የከባድ መሣሪያ ተኩስ ጭምር የተቀላቀለበት ጥቃት ደረሰባቸው። ይህኛው ጥቃት የደረሰው ሰኔ 11/2014 የተፈጸመው አስከፊና የብዙዎችን ሕይወት የቀጠፈውን ጭፍጨፋ የሚመለከተው ወሬና ውዝግብ ጋብ ሳይል ነው።
‘የብልጽግናው’ መንግሥትና እሱ የሚዘውራቸው መገናኛ ብዙኀን መጀመሪያ በጸጥታ በኋላም እንደ ነገሩ፣ ማለትም የናይጄሪያው ቦኮ-ሐራም ልጃገረዶችን አፍኖ ሲወስድ የሚሰጡትን ያህል ትኩረት እንኳ ነፍገውት ወይም በአንዳንድ የአዲስ አበባ ጓሮዎችና የጅረት ዳርቻዎች ከሚተከሉ የቆስጣና የሰላጣ ወሬዎች ያነሰ ጉዳይ አድርገው ሊያሳዩት ሞክረዋል።
ሆኖም የወለጋው ሰቆቃ በዓለም ታላላቅ መገናኛ ብዙኀን ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠውና የዩክሬንና የሩስያን የጦርነት ወሬዎች ተጋፍቶ ለዓለም ሕዝብ ሊነገር የሚገባው አሳሳቢ ችግር ሆኖ ተገኝቷል። ብዙዎች መገናኛ ብዙኀን የወለጋውን የሰኔ 11 ጭፍጨፋ ከሩዋንዳው የዘር ማጥፋት ዘመቻ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተ አሳሳቢ ዘር ተኮር ጥፋት መሆኑን ጭምር በግልጽ ተናግረዉለታል።
እነዚህን ኹለት የሰኔ ወር የግፍ ጭፍጨፋዎች ተከትሎ፣ የብልጽግና መንግሥት የፖለቲካና የጦር ባለሥልጣናት ትኩረት የሰዎችን በግፍ መጨፍጨፍ መቃወምና ወንጀለኞችን ማሳደድ መሆን ሲገባው፣ የሟቾችን ቁጥር በሚመለከት የሚወጡ ዘገባዎችን በመሞገት፣ ጭፍጨፋው ዘር ተኮር እንዳልሆነ ለማሳመን በመሞከር፣ ጭፍጨፋው የተካሄደው ዘርን ለማጥፋት በታሰበበት መንገድ ሳይሆን ኦነግ ሸኔ ሽንፈቱ የፈጠረበትን ብስጭት ለመግለጽ ሲል ያደረሰው ተራ የግድ ዘመቻ አስመስለው ለማሳየት ላይ-ታች ሲሉ ተስተውለዋል።
በጣም አሳፋሪውና አጠያያቂው ነገር አንዳንድ የብአዴን/ብልጽግና ሹማምንት በዚህ ጊዜ ተመርጠው የአዲስ አበባ ቆስጣና ሰላጣ መትከል አብዮት ለሌሎች ክልሎች አብነት መሆኑን እንዲሰብኩ፣ ችግኝና ሰላጣ ተከላው የኢትዮጵያን ችግር ሁሉ የሚቀርፍ ቁም ነገር አስመስለው ለማሳየት ወደ መገናኛ ብዙኀን እንዲመጡ መደረጉ ነው። በእርግጥ ትላንትና ‹አቶ መለሰ ዜናዊ መተኪያ የሌላቸው የዓለማችን ድንቅ ሰው ናቸው› ሲሉ የነበሩ ግለሰብ፤ ዛሬ የአዲሰ አበባ ቆስጣ ተከላ ዘመቻን እያቆለጳጰሱ ያለ ሐፍረት ሲያወሩ ቢገኙ ብዙ ላይገርም ይችላል። ምክንያቱም ተጠያቂነት ሲመጣ ተላላኪ ነበርኩ ብሎ የአድር ባይነትና የራስ ወዳድነት ሩጫን አቃልሎ ከደሙ ንጹህ ነኝ ለማለት ሌላ ዕድል ይገኝ ይሆናል።
በኢትዮጵያ ዘመን ቀመር በ1968 በቀረጸው ማንፌስቶው ላይ ‘ለአማራ ብሔር ዕረፍት አልሰጥም’ ሲል ዛቻውን ያሰፈረው ሕወሐት፣ በ2012 ከአማራ ሕዝብ ጋር የሚያወራርደው ሒሳብ እንዳለው ሲናገር ተሰምቷል። ዛሬ ኢትዮጵያችን ለሕወሓት በመላላክ የገዛ ወገኖቻቸውን ጭምር በድለው ለማስበደል ቆርጠው በተነሱ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ነባር ሰዎች እየተመራችና ከሕወሓት ጋር ግንባር ገጥሜአለሁ በሚሉ በኦነግ ሸኔ እና በሌሎች ታጣቂ ቡድኖች እየታመሰች ባለችበት በዚህ ጊዜ፣ ‘ለአማራ ብሔር ዕረፍት አልሰጥም’ የሚለው የሕወሓት ዛቻ በሰፊው እየተተገበረ መሆኑ የሚካድ አይደለም።
ይህ ዛቻ በቀጥታ አማራውን ሕዝብ የሚመለከት ይምሰል እንጂ፣ ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ የሚመለከት መሆኑን መጠራጠር አይገባም። በኢትዮጵያዊነታቸው በጥብቅ የሚያምኑ ተጋሩዎችን ጭምር ለማጥፋት የተሰነዘረ ዛቻ ነው። ሕወሓት ወደ ቆላ ተንቤን በረሀ በርግጎ በነበረበት ወቅት ፈዳይን በሚባሉ ነፍሰ ገዳዮች ከገደላቸው ሰዎች መካከል፣ ያንን ወቅት በትግራይ ውስጥ የኢትዮጵያዊነት ትንሳኤ መከሰቱን የተናገሩ ሰዎች ይገኙበታል።
ከዚህ ሌላ ከክልሌ ውጣ የሚለው መጠቃቃትና የክልል ድንበር ግጭት ያልደረሰበት የኢትዮጵያ ክፍል የለምና የሕወሓት ማኒፌስቶ ዛቻም ሆነ የብቀላ ሒሳብ የማወራረድ ፉከራ በአማራ ሕዝብ ላይ ተወስኖ ይቀራል ብሎ መዘናጋት ከባድ ዋጋ ሊያከፍል ይችላል። ነገሩ በሕዝብ ላይ ብቻ ተወስኖ እንደማይቀርና የማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዕጣ እንደሚሆን በሰሜን ዕዝ ላይ የደረሰው ሰቆቃ ማስረጃ ነው።
ሕወሓት በ1968 ማኒፌስቶው ላይ ያሰፈረውን ታላቋን ትግራይ ማዋለድ የሚለውን ዓላማውን እውን ለማድረግ አስቦ የቀረጸውንና ሕዝብ ተስማምቶበታል ለማለት ያህል የስብሰባዎች ድራማ ሠርቶ በኢትዮጵያ ላይ የጫነው ሕገ-መንግሥት፣ በአንቀጽ 39፣ ንዑስ አንቀጽ 1 እና ንዑስ አንቀጽ 4 ላይ ኢትዮጵያ ፈራሽ አገር እንጂ ዘላለማዊ ሉዓላዊነት ያላት አገር አለመሆኗን በግልጽ ሐረግ አስቀምጦታል።
ኢትዮጵያ የብሔር-ብሔረሰቦች እስር ቤት ናት በሚለው ሽፋን ስር ሕገ-መንግሥቱ የኢትዮጵያን ዘላለማዊ ሉዓላዊ ግዛትነት ሽሮ እጣዋን መፍረስ አድርጎታል። የሕወሓት/ኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ‘የትኛውም አገር ያልደፈረውን አንቀጽ በሕገ-መንግሥታችን ያካተትን ፖለቲከኞች ነን’ እያሉ የሚኩራሩበት ይህ አንቀጽ፤ ማንኛውም ሕዝብ፣ ብሔርና ብሔረሰብ ባሰኘው ጊዜ ድርሻዬ ነው የሚለውን ምድር ይዞ ከኢትዮጵያ እንዲሰናበት በግልጽ ስለሚፈቅድ፤ የኤርትራውን ሕዝባዊ ግንባርንና ሕወሓትን የመሰለ ጠንካራ ቡድን በተነሳ ቁጥር የኢትዮጵያ ሕልውና ፈተና ይገጥመዋል።
አገሪቱም እየተቆራረሰች የማለቅ ዕጣን ለመጋፈጥ ትገደዳለች። ጉልበቱ ያልጠነከረ ቡድን ሲነሳ ግን የክልልነት ጥያቄ ስላነሱ ብቻ ሲዳማዎችና ወላይታዎች የተጋፈጡት የብልጽግናን የመሰለ ጡንቻ ይቀምስ ዘንድ ይገደዳል።
በዚህ የሕገ-መንግሥት አንቀጽ መጠቀም የሚሹ ቡድኖችና ታማኝ አባሎቻቸው ሁሉ ስለ ጎጣቸው (ስለ ክልላቸው) እና ስለ ዘራቸው ማሰብ ዋናው ዓላማቸው ነው። በሕዝቦች መካከል ግጭትን መፍጠርን ደግሞ ዓላማቸውን ለማራመድ ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች አንዱ እንዲሆን በብርቱ የሚሠሩበት ጉዳይ ነው። መጡብህ ብለው ሕዝብን ማስፈራራት፣ ወገኔ የሚሉት ሕዝብ ሌላውን ሕዝብ ሁሉ በጠላትነት እንዲፈርጅ ማድረግና የሕዝቦችን አብሮ የመኖር ባህል ማውደም የዘወትር ተግባራቸው ነው።
ሕዝቦች የተሳሰሩባቸውን የሐይማኖት፣ የታሪክ፣ የጋብቻና የሌሎች ዘርፎች ድርና ማጎች መበጣጠስ ከዘመነ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ጀምሮ እንደ ተገቢ ሥራ ተደርጎ ሰፊ ሥራ የተሠራበት መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም። ከፍተኛ ባለሥልጣን ከሆነው ከአባ ዱላ ገመዳ ጀምሮ የስልጤ ፖሊስ ሹም እስከሆነው ዝቅተኛ የሕወሓት አገልጋዮች የጻፏቸው የታሪክ የተባሉ መጽሐፍት ወጣቶችን ለማደናገርና ለሌላው ሕዝብ ጥላቻን እንዲጸንሱ፣ ሕዝብም ጎሳውን መሠረት አድርጎ በሌላው በሕዝብ ላይ ይነሳሳ ዘንድ ለሚካሄደው ዘመቻ ግብአት ይሆኑ ዘንድ የተዘጋጁ መሆናቸው የሚካድ አይደለም።
በሐይማኖት ተቋማት ውስጥ የተሰበኩ አደገኛ የጥላቻ ቅስቀሳዎችና የእምነት ምሁራን ነን ባይ ግለሰቦች ጽፈዋቸው በእምነት ተቋማት አጥር ጥግ የተቸበቸቡ ‘እምነቴ ሲበደል ኖሯል’ ባይ መጽሐፍትም ሕዝብ ሐይማኖቱን መሠረት አድርጎ በሌላው ሕዘብ ላይ እንዲነሳ ለማድረግ ሴራ የመሸረቡ ዘመቻ ቅርንጫፎች መሆናቸው ግልጽ ነው። ለሐይማኖቴ እቆረቆራለሁ በሚል ሽፋን የፈጠራ ሥራ በሆኑና በተጋነኑ ግጭት ቀስቃሽ ወሬዎች፣ ጸረ-ኢትዮጵያና ጸረ-ኢትዮጵያዊነት ትርክቶች በሰፊው ሲነዙ ኖረዋል።
በእምነት ተቋማት ውስጥ ዘርንና ሐይማኖትን መሠረት አድርገው ከእነ እንትና ጋር ሰላም አትባባሉ፣ ለእነ እንትና ቤታችሁን አታከራዩ፣ በእነ እንትና ግቢ ቤት አትከራዩ ወዘተ… የሚሉ ስብከቶች ከጣራ በላይ የተሰበኩት ሰላምን በማጥፍት ጥላቻን ለመፍጠርና በአንድ ግቢ አብሮ መኖርን ተገቢ ያልሆነ በማስመሰል በኢትዮጵያዊነትን አብሮ የመኖር እሴትን ለማውደም ለሚካሄደው ዘመቻ ስኬት እንደ ጠቃሚ ግብአት ተደርገው የቀረቡ ነዳጆች መሆናቸው ሊካድ አይገባውም።
ከሳምንታት በፊት ጎንደር ውስጥ የተካሄደው በሙስሊሞች ላይ የተሰነዘረ ጥቃትና ለጎንደሩ ጥቃት ምላሽ ነው ተብሎ ስልጤ ዞን ውስጥ የተካሄደው ጥቃት በእነዚህ በእምነት ቤቶች በተሰበኩ የጥላቻ ስብከቶች የሰከሩና በእምነቴ ተበደለ በሚል ሥም ተጽፈው ሲቸበቸቡ የነበሩ መጽሐፍትን የሸመደዱ ግለሰቦች የፈጸሟቸው የግፍ ተግባራት ናቸው። እንደ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል ከጥቃቱ ጋር በተያያዙ ከተነበቡ መፈክሮችና ከተሰሙ ቀረርቶዎች መካከል ኢትዮጵያን ያቆሙ አጼዎችን የሚዘልፉ፣ የሚያጣጥሉና የሚሳደቡ በዝተው ተሰምተዋል። ይህ የሆነው ‘ሦሥቱ አጼዎች’ እና ‘ኪነት ያገነነው አጼ’ በሚል ርዕስ የተጻፉትና ኢትዮጵያ ለእስልምና እምነት ጠላት ሆና ብቻ የቆመችና የኖረች አገር እንደሆነች አድርገው የሚያሳዩት ኹለት መጽሐፍት፣ ለስሕተት የዳረጓቸውና ለጥፋት ያነሳሷቸው ግለሰቦች በርካቶች በመሆናቸው መሆኑን መገመት ይቻላል።
ሚዛናዊ ለሆነና ሐቁን ለሚያውቅ ሰው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ1400 ዓመታት በላይ ዕድሜን ያስቆጠረው የሐይማኖት መቻቻልና መከባበር በዛሬው ዕለት እንኳ ሳውዲ አረቢያን በመሳሰሉ አገራት የሌለ መሆኑ በጣም ግልጽ ነው። ሳውዲ አረቢያ አንድም ክርስቲያን ወይም ከእስልምና ውጭ የሆነ ሐይማኖት ያለው ዜጋ የላትም። ከዜጎቿ አንዱ እዚያው ሳውዲ ውስጥ የእስልምና እምነቱን መቀየሩ ቢደረስበት ወዲያውኑ በአደባባይ ተቀልቶ ይገደላል።
በሕወሓት/ኢሕአዴግ ዘመን እነዚህ የመሳሰሉ ስብከቶች በነጻነት የተስተጋቡት እና እነዚህን መሰል ጽሑፎች መጽሐፍት፣ በመጽሔትና በጋዜጣ መልክ በገሀድ ተዘጋጅተው ለንባብ ይቀርቡ የነበረው አብሮ የመኖር እሴትን በመሸርሸር ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ለማውደም የተጠነሰሰውን ሴራ ተገን አድርገው ነው። የሕወሓትና የተላላኪዎቹ የኢሕአዴግ ስርዓትም ይህን መሰሉን አውዳሚ ዘመቻ በዝምታ የተመለከቱት በ1968 ከተነደፈው የሕወሓት ማኒፌስቶ መንፈስ ጋር የሚጣጣም በመሆኑ ነው።
ዛሬ ዛሬ ሕወሓት ብቻ ሳይሆን የትግራይ ምሁራንና የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ነን የሚሉ ቡድኖች ሁሉ ትግራይ ራሷን የቻለች አገር ለመሆን መቃረቧን በይፋ እየተናገሩ ነው። የትግራይ ሕዝብ ለሪፈረንደም እንዲዘጋጅ አዘውትረው በማሳሰብም ላይ ናቸው። እስከ አሁን ሦስት ሐይማኖቶች ከእናት የእምነት ተቋማቸው ተገንጥለው ራሳቸውን ችለው መቆማቸውን አውጀዋል። የትግራይ ኦርቶዶክስ፣ የትግራይ እስልምና እና የትግራይ ወንጌላውያን ተብለው እየተጠሩ አዲስ አበባ ከሚገኘው ዋና ጽሕፈት ቤት ስር አለመሆናቸውን በግልጽ አሳውቀዋል። የትግራይ ኦርቶዶክስ አይስማሙኝም ያላቸውን የሐይማኖት ቀኖናዎችና አስተምህሮዎች እያስወገደ በአዲስ ለመተካት በርካታ ሥልጠናዎችን ለጳጳሳቱ፣ ለቀሳውስቱና ለዲያቆናቱ ወዘተ… እየሰጠ ነው።
ይህን መሰሉ የትግራይ አካሄድ ማቆሚያው የት መሆኑ የሚታወቅ አይደለም። ነገር ግን የዘር ፖለቲካ ማራመድ ሕጋዊ እስከሆነ ድረስና የሕወሓት/ኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥት በሥራ ላይ መዋሉ በቀጠለ ቁጥር በየአካባቢው የተለያዩ ቡድኖች እየተነሱ የራሳችን አገር እንፈልጋለን ማለታቸውና ኢትዮጵያን ለማፍረስ መራወጣቸው አይቀሬ ነው። ከኦሮሞ ነጻ አገር አቀንቃኞች ጀምሮ እስከ ስልጤ እስላማዊ ኤምሬት ሰባኪ አክቲቪስቶች፣ ለአማራ የማትበጅ ኢትዮጵያ የራሷ ጉዳይ ከሚሉ የአማራ አክቲቪስቶች ጀምሮ ዕጣ ፋንታችን ከሕወሓት ጋር ነው እስከሚሉ የአገውና የቅማንት ፖለቲከኞች፣ ታላቋን ሶማሊያ ከሚመኙ የሶማሌ ክልል ፖለቲከኞች ጀምሮ ደቡብ ሱዳናዊ ነን እስከሚሉ የጋምቤላ ታጋዮች ኢትዮጵያን በማፍረስ የታላቋን ትግራይ ምስረታ እውን ለማድረግ፣ አውቀውም ሆነ ሳያውቁት ለሕወሓት በተላላኪነት እየሠሩ መሆኑን ሊክዱ አይገባም።
የሕወሓት/ኢሕአዴግን ሕገ-መንግሥት ተሸክሞ መጓዙን የቀጠለው የብልጽግና ቡድንም ቢሆን ሕወሓትን በተዘዋዋሪ መንገድ እያገለገለ መሆኑና የሕወሓትን አጀንዳ ለማስፈጸም እየሠራ መሆኑ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም። አገርን የሚያፈርስ አንቀጽ ያለው ሕገ-መንግሥት ተሸክሞ የሚጓዝ መንግሥትና በሕወሓት/ኢሕአዴግ ዘመን የተዘራውን የጥላቻ ትርክት መሞገትና ማረም ሲገባቸው፤ በየአጋጣሚው በሚያደርጉት ንግግር ሰዎችን በዘርና በሐይማኖት ልዩነት የሚያቋስል የፈጠራና የተጋነነ ታሪክ የሚተርኩ ባለሥልጣናት ባሉበት አገር፤ ‘ኢትዮጵያ አትፈርስም!’ እያሉ በባዶ ሜዳ መፎከር የትም የሚያደርስ አይደለም።
ይህን መሰሉን ሃቅ በመገንዘብ ከክልላቸው ውጪ የሚኖሩና መጤዎች እየተባሉ የሚብጠለጠሉ ሕዝቦችን በሚመለከት አንድ ትልቅ ውሳኔ ላይ መድረስ ተገቢ ነው። ነገሮች በዚሁ ከቀጠሉ መነሳት የሚገባው ጥያቄ ‘ከክልላቸው ውጪ ነው የሚኖሩት ተብለው የተፈረጁ ምስኪን ሕዝቦች ጭፍጨፋ መቼ ይቆማል?’ የሚል ሳይሆን ‘ከክልሌ ውጡልኝ የሚለው ጭፍጨፋ ወደ የትኛው ከተማና የገጠር መንደር ይስፋፋል?’ የሚለው ጥያቄ ነው።
ሻሸመኔንና ባቱ-ዝዋይን በሚያካክሉ ከተሞች የተከሰቱት ገዳይና አውዳሚ ጥቃቶች፣ በድሬዳዋና በሐረር ወዘተ በተደጋጋሚ የተከሰቱ ትንንሽ ገዳይ ጥቃቶች ዘር ተኮርና ሐይማኖት ተኮር ጥላቻ የታየባቸው፣ ከክልላችን ወይም ከከተማችን ውጡልን የሚል ይዘት የነበራቸው መሆኑ የሚካድ አይደለም። አዲስ አበባም ብትሆን በየሰበቡና በየአጋጣሚው የችግሩ ቁርሾ አልቀረላትም።
ራሱን፤ ማን የት ሄዶ የጦር መሣሪያ ጥቃት መፈጸም እንዳለበት መመሪያ ሰጭ አድርጎ የሚቆጥረው ባልደራስ የተባለው ቡድን እና ከክልላቸው ውጭ የሚኖሩ ሰዎች ታጥቀው ራሳቸውን ይከላከሉ የሚለው አብን የተባለው ቡድን ጩኸት፣ የእብድ ገላጋይነት ሚናቸውን የሚያሳይ እንጂ ነገሩ በቀላሉ የሚተገበርና ጥሩ መፍትሔን የሚያስገኝ አለመሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። የእነዚህ ቡድኖች ምክር ምስኪኖችን ይበልጡን ለእልቂት የሚዳርግና ከለላ ሊሰጧቸው ከሚሞክሩ ሰላማዊ ጎረቤቶቻቸው ጋር ጭምር ግጭት ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርግ ውጤት የሚያመጣ ብቻ ነው።
10፣ 20፣ 50 ወዘተ መጤዎች ተብለው የተፈረጁ አባወራዎች ተበታትነው በሚኖሩባቸው በመቶዎች ወይም በሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮምያ የገጠር መንደሮች፣ በዐስሮች ወይም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን መልምሎ ማስታጠቅ ምስኪኖቹን ሰዎች የጦርነት መለማመጃ ከማድረግ የዘለለ ውጤት ያለው አይሆንም። ጥቂቶች ታጥቀው ወደሚጠብቁት መንደር በዐስርና በኻያ እጥፍ ብዛት ያለው ታጣቂ አጥቂ ቡድን በመላክ፣ ቆመህ ጠብቀኝ ወይም ክላሽንኮቭ መሣሪያዎችን ታጥቀው መንደራቸውን እንዲጠብቁ የተመደቡ ታጣቂዎች ወዳሉባቸው መንደሮች ኃይለኛ የተኩሰ አቅም ያላቸው ከባድ የጦር መሣሪያዎችን የታጠቁ አጥቂዎችን በመላክና በሌሎች መሰል ዘዴዎች ምስኪኖችን ለእልቂት የሚዳርግ በር መክፈት ተገቢ አይደለም።
የአብን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይታወጅ የሚል ጥሪም አስመሳይነትና ዝም አላልኩም ለማለት ታስቦ የተሰነዘረ መሆኑ ግልጽ ነው። በዘመነ ብልጽግና ለመቁጠር የሚታክት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል። ነገር ግን አገሪቱ ከትርምስና ከሁከት የራቀችበት ጊዜ የለም። እናም ሁሉም ወገኖች ምስኪን ሰዎች የገዳዮቻቸው ቀላል ዒላማዎች ሊሆኑ የማይችሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር እያሰቡ መናገርና መሥራት ይጠበቅባቸዋል። በነገራችን ላይ አብን የአማራ ክልል ሕዝቦች በክልላቸው በሰላም ተረጋግተው የሚኖሩበት ሁኔታ ይኖር ዘንድ አንዳንድ አባላቱን ቢያርም ተገቢ መሆኑን ማወቅ ይገባዋል።
በዐስሮች ወይም በመቶዎች የሚቆጠሩ አባወራዎች ተበታትነው የሚኖሩበት ሁኔታ መጤዎች የተባሉትን ለጥቃት ማጋለጡ በተደጋጋሚ ታይቷል። በየገጠር መንደሩ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን አጥቂ ሊመክት የሚችል በርካታ አባላትን ያቀፈ የፖሊስም ሆነ የመከላከያ ኃይል በቋሚነት ማስፈርና ሰዎችን መጠበቅ የማይቻል መሆኑ የሚካድ አይደለም። እናም አላባራ ያለውን የምስኪኖች ሕይወት ለማዳን የፌዴራሉ መንግሥትም ሆነ የክልል መንግሥታት ሃቁን መሠረት ያደረገና ምስኪኖችን ታድጎ ሰላም ሊሰጣቸው የሚችል መፍትሔ በማምጣቱ ላይ በጥልቀት ሊያስቡበት ይገባል።
መፍትሔው ሰዎቹን ከነሀብትና ንብረታቸው መጤዎች ከሚባሉበት ቦታ አንስቶ ወደ ሌሎች ቦታዎች ወስዶ ማስፈርና ማቋቋም ሊሆንም ይችላል። ሚሊዮን ሰዎችን ወደ ሌሎች ቦታዎች ወስዶ ማስፈር ከባድ ነው በሚል ሰበብ በየጊዜው በመቶዎችና በሺዎች የሚቆጠሩ ሕጻናትንና አዛውንቶችን ያካተተ እልቂት እንዲፈጸም መፍቀድ ተገቢ አይደለም።
ለእልቂት የተዳረጉት ሰዎች ዓይነትና ብዛት ብቻ ሳይሆን ጭፍጨፋው የሚካሄድበት ድግግሞሽና ዘዴ በራሱ የሚናገረው ብዙ ሃቅ አለ። የጭፍጨፋዎች አስደንጋጭ ወሬዎች በመንግሥት ችላ መባላቸው፣ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድናችን ሲሸነፍ የተለመደ ነው ተብሎ እንደሚታለፈውና ወዲያውኑ እንደሚረሳው ሁሉ፤ የምስኪኖች እልቂትም ከባለሥልጣናት ጀምሮ እስከ ጋዜጠኞቻቸው ተቃልለው እንዲታዩ የሚያደርጉት ጥረት ተደጋጋሚና አስደንጋጭ መሆኑን በማየት ምሁራንና ባለሀብቶችም ጭምር ምስኪኖቹ ሰዎች ከዕለት ዕለት ስጋት ተላቅቀው ሰላማዊ ኑሮ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲፈጠር መሥራትና መምከር ይገባቸዋል።
ግዛቸው አበበ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ይገኛሉ።
ቅጽ 4 ቁጥር 192 ሐምሌ 2 2014



