‹ወደ ነገ ሒያጅ ነንና›

0
1400

ጥበብ ለጥበበኛው ከሚሰጠው ስሜት ባሻገር፣ ለታዳሚው መድኃኒት አልፎም ብርታትና ተስፋ አንዳንዴም መቀስቀሻ ጭምር የመሆን አቅም አለው። በድምሩ ጥበብ ከሰጪው ይልቅ ለተቀባዩ ከበድ ያለ ዋጋ አለው። ለዛም ነው ሹመኞችና ባለሥልጣናት በተለያየ ዘመን ሲፈሩትና በተለያየ መንገድ ቁጥጥር ከፍ ሲልም እገዳ ሲጥሉበት የሚስተዋለው።

የለውጥ መንገድ ጀምረናል የሚለው ስርዓት ከመጣ አራት ዓመት ወዲህ፣ የጥበብ መሰናዶዎች ትኩረታቸው በጋራ ሆኖ ጠላትን ስለመመከት ከዛም ሲያልፍ ማኅበረሰብ እሴትና ሥነምግባሩን እንዲያስታውስና በዛ መልክ እንዲኖር የሚያሳስብ ዓይነት ነበር። አሁን ላይ ግን ከዛም አልፎ የማኅበረሰቡን ሐዘንና መከራ፣ የንጹሐንን እልቂት ልብ ወደማለት የተሻገረ ይመስላል።

‹ወደ ነገ ሒያጅ ነንና› የተሰኘው የአስታውሰኝ ረጋሳ የግጥም ስብስብ መጽሐፍ ምርቃት ላይ ይህን እውነት በሚገባ መታዘብ ይቻላል። የመጽሐፍ ምርቃቱን ለማድመቅና የዝግጅቱ አካል ሆነው የተገኙ የጥበብ ሰዎች፣ የመጽሐፉን አዘጋጅ እንኳን ደስ አለህ ከማለት ባሻገር ስሜታቸውን በተለያየ መንገድ አጋርተዋል።

ይህ ይቆየንና፤ የመጽሐፍ ምርቃቱንና የመጽሐፉን ነገር በጥቂት እናውሳ። ባሳለፍነው ሰኔ 27/2014 ማምሻውን ነበር፣ ‹ወደ ነገ ሒያጅ ነንና› የግጥም ስብስብ መጽሐፍ ምርቃት በአገር ፍቅር ቴአትር በድምቀት የተከናወነው። በዚህም ዝግጅት ላይ አንጋፋ የፊልም ባለሞያዎች፣ ገጣምያን እንዲሁም አዳዲስ ድምጻውያን በመድረኩ ሥራዎችን ከማቅረብ አንስቶ ሐሳብ አጋርተዋል። የገጣሚው ቤተሰቦች፣ ጓደኞችና አድናቂዎች እንዲሁም የጥበብ አፍቃሪያን ታዳሚ ነበሩ።

42 ግጥሞችን አካትቶ በ109 ገጾች የተዋቀረውና በ170 ብር ዋጋ የመጽሐፍ ገበያውን የተቀላቀለው ይህ ‹ወደ ነገ ሒያጅ ነንና› የተሰኘ የግጥም ስብስብ፤ ለገጣሚ አስታውሰኝ ረጋሳ ኹለተኛ የመጽሐፍ ሥራው ነው። ከዚህ ቀደም ‹ተስፋ› የተሰኘ መጽሐፍ ለአንባብያን አድርሷል። የግጥም ሥራዎቹም በተስፋና በብርሃን ላይ የሚያተኩሩ መሆናቸው ተመስክሮለታል።

ፍሬዘር ታሪኩ የግጥም ስብስብ መጽሐፉን ይዘት በሚመለከት ዕይታውን በመድረኩ ብሎም በመጽሐፉ መግቢያ ላይ አቅርቧል። በዛም ላይ የጠቀሰው፣ ገጣሚው ‹ተስፋ› በተሰኘ የመጀመሪያ የመጽሐፍ ሥራው ላይ የጀመረውን የብርሃን ጉዞ እንዳላቆመ ነው።

አክሎም ይህን በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ሲሲፍር እንዲህ አለ፤ ‹‹ገጣሚው በዚህ የግጥብ ስብስቡ ውስጥ ዛሬ ምንም ሆነ ምን፣ ወደ ነገ ሒያጅ ነኝ ይለናል። ነገስ ምን አለ ብለን ስንጠይቀው፤ ብርሃን፣ ተስፋ፣ ፍቅር እያለ ያወጋናል። እርሱ ብቻ ነው ወይ ስንለው ደግሞ አመስግን እያለ የተስፋ ዳናውን እየረገጠ ያዘግመዋል።›› ይላል።

ከመጽሐፉ አንድ ግጥም መዝዞም እንዲህ ያቀርባል፤
አመስግን
ከተሰጠህ ጸጋ…
የጎደለብህን በመምረጥ አትኮልኩል፤
ፈገግ በልና…
ምንጊዜም አመስግን በቀዳዳህ በኩል።


ቅጽ 4 ቁጥር 192 ሐምሌ 2 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here