በትግራይ ክልል ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ተሰማ

0
2625

በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች በጦርነቱ ምክንያት በተከሰተው ርሃብ ከመሰቃየት ሞትን በመምረጥ ቀድመው ራሳቸውን እያጠፉ መሆኑን በሥፍራው ተዘዋውረው የተመለሱ ታማኝ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገለፁ።

ኹለት ዓመት ሊሞላው ወራት በቀሩት ጦርነት ሳቢያ ርሃብ መከሰቱን ተከትሎ በርካታ ሰዎች ራሳቸውን ለማጥፋት እንደተገደዱ ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድርግ መቀሌ ከተማ ደርሰው የመጡ ሰዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

መረጃ ሰጪዎቹ እንደሚሉት ከሆነ፤ በክልሉ የሰብዓዊ ድጋፍ አነስተኛ በመሆኑ ነዋሪዎቹ በርሃብ እየተሰቃዩ ሲሆን፤ ይህን ተከትሎም ግለሰቦች ራሳቸውን እያጠፉ ነው ተብሏል። ነዋሪዎቹ ራሳቸውን እያጠፉ ነው የተባለው ጎዳና ወጥተው ቢለምኑም ማግኘት እንደማይችሉ በመረዳታቸውና ከመለመን ሞትን በመምረጣቸው ነውም ተብሏል።

ራሳቸውን እያጠፉ ያሉት አነስተኛ ገቢ የነበራቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ፤ ልጆቻቸው ርሃብ ሲያሰቃያቸው መመልከት የከበዳቸው ከዚህ በፊት ባለጸጋ የነበሩ ሰዎችም ጭምር ናቸው ነው የተባለው።

ትላልቅ ቤት ያላቸው ግን ልጆቻቸውን መመገብ ያልቻሉ ሰዎች ራሳቸውን እንዳጠፋ መረዳታቸውን በቦታው ደርሰው የመጡት የዐይን እማኞች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል፣ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ በርካታ እናቶች በወሊድ ምክንያት መሞታቸውንም ነው ምንጮቹ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።
በክልሉ የመድኃኒት እጥረቱ እንደቀጠለ ሲሆን፤ መድኃኒት ቢኖር የሞት ጉዳት የማድረስ ኃይላቸው አናሳ ነው በሚባሉ በሽታዎች ጭምር በርካታ ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል ነው የተባለው።

ጦርነትን በተመለከተ በከተማው ሰላም ሰፍኖ ይስተዋላል የተባለ ሲሆን፤ ጦርነቱ ያስከተለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ግን የከፋ በሚባል ደረጃ ላይ መሆኑ ተመላክቷል።

የአካባቢው ወጣቶች በማኅበር ተደራጅተው ገንዘብ በማሰባሰብ በርሃብ ምክንያት የተጎዱና መንቀሳቀስ ያልቻሉ ሰዎችን እየረዱ ቢቆዩም፣ አሁን ላይ ገንዘብ ማሰባሰብም የማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል።

ከሐምሌ 2013 ጀምሮ ወደ ክልሉ የገቡት የእርዳታ ጭነት መኪናዎች 1 ሺሕ 338 እንደሆኑና፤ በእርዳታቸው ማዳረስ የተቻለው ከ5 ሚሊዮን ሕዝብ 10 በመቶውን ብቻ እንደሆነ ኦቻ በዘገባው አመላክቷል፡፡ የድጋፍ እጥረቱን ተከትሎም ነዋሪዎቹ ርሃቡን መቋቋም እንዳልቻሉ ነው ማወቅ የተቻለው።

ከኢኮኖሚያዊ ቀውሱ ውጪ በመቀሌ ከተማ ያለው የጸጥታ ሁኔታ እንደሚባለው የከፋ አይደለም የተባለ ሲሆን፤ በፈለጉት ሰዓት ወጥተው በመግባት፤ መረዳዳቱ ላይ መልካም ሁኔታ እንዳለ ነው የተጠቀሰው።

መቀሌ ደርሰው ተመላሾቹ፤ ማኅበረሰቡ እስከ አሁን እየተረዳዳ ቢቆይም አሁን አሁን የሚያካፍሉት ነገርም ስለሌላቸው ለመፈናቀልና ጎዳና ለመውጣት እየተገደዱ ነው ብለዋል። ቤተሰቦቻቸው በጦርነት የሞቱባቸውና ርሃቡን መቋቋም ያልቻሉ ሕፃናትም ከቀሪ ዘመዶቻቸው ጋር ተጠፋፍተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በጦርነቱ ሳቢያ 8 ሺሕ 419 ሕጻናት ከቤተሰቦቻቸው መጠፋፋታቸውን ገልጾ፤ 7 ሺሕ 165 የሚሆኑት ሕጻናትም በትግራይ ክልል የነበሩ መሆናቸውን ማመላከቱ አይዘነጋም።

በሰሜን ኢትዮጵያ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ የሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልገውና ከእነዚህም ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በትግራይ ክልል ውስጥ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መግለጹ ይታወሳል።


ቅጽ 4 ቁጥር 192 ሐምሌ 2 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here