በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ የእርቀ ሰላም ኮንፍረስ ተካሄደ

0
1071

በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ እና አካባቢው የተገኘውን ሰላም አጠናክሮ ለማስቀጠል በቡለን ወረዳ ሕዝባዊ እርቀ ሰላም ኮንፍረስ መካሄዱ ተሰምቷል።

በእርቀ ሰላም ኮንፈረንሱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አቢዮት አልቦሮን ጨምሮ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች፤ የክልል፤ የዞን እንዲሁም የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ከፍተኛ አመራሮች መገኘታቸው ተሰምቷል።

በኮንፈረንሱ አሁን ላይ እየተካሄደ ያለውን ሕግ የማስከበር ተግባር ተከትሎ የተገኘውን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል ያለፈውን በደል በይቅርታና በእርቅ በመፍታት አንድነትን እና አብሮነትን መመለስ የሁሉም ድርሻ ሊሆን ይገባል መባሉ ተጠቅሷል።

የሰው ልጅ ሲኖር ግጭቶችና አለመግባባቶች ሊከሰቱ ይችላሉ። ነገር ግን የሕይወት ቀጣይነትን በመገንዘብ የግጭት መንስኤዎችን በመለየት ያለፈውን በይቅርታና ምህረት መጋረጃ በመዝጋት መጻኢ እድሎችን በመቻቻልና በመከባበር አብሮ መኖር መቻል የብልህና አገር ወዳድ ማኅበረሰብ መገለጫ መሆኑን በመገንዘብ ለሰላም ዘብ መቆም አስፈላጊ መሆኑም ተነስቷል ነው የተባለው።

የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ ጋሹ ዱጋዝ በበኩላቸው፣ ቀጠናው የልማት ኮሪደር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተለያዩ ፍላጎት ያላቸው የውስጥ እና የውጭ ኃይሎች ክንዳቸውን የሚያሳርፉበት አካባቢ መሆኑን ጠቁመዋል።

መንግሥት የሕዝቡን የሰላምና የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እያከናወነ ያለውን ተግባር ከዳር ለማድረስ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች የጎላ ድርሻ እንዳላቸው ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል ነው የተባለው።

የቡለን ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ግዛቱ ባልዳ ደግሞ፣ በቀጠናው የተገኘውን ሰላም አጠናክሮ ለማስቀጠል በቀበሌ ማዕከላት ሲካሄድ በነበረው ሕዝባዊ ኮንፍረስ የተገኙ መልካም አስተያየቶችን ለማስቀጠል እርቀ ሰላሙ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል። አሁን ባለው ሰላም ተፈናቅለው የነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መመለስ መጀመራቸውን ነው ዋና አስተዳዳሪው የተናገሩት።


ቅጽ 4 ቁጥር 193 ሀምሌ 9 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here