በቤንሻጉል ጉምዝ ክልል በሚገኘው ካማሺ ዞን በርካታ ማዕድናት ቢኖሩም፣ በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት አሁን ላይ ማዕድን የማውጣት ተግባር ተቋርጦ እንደሚገኝ ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
በዚህም ከአዲስ አበባ፣ ከአማራ እና ከኦሮሚያ ክልል መጥተው ሲሠሩ የነበሩ በርከት ያሉ ባለሀብቶች ሥፍራውን ለቀው መውጣታቸውን ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ በማኅበር ተደራጅተን ከባለሀብቶች ጋር በመሥራት ነበር የምንጠቀመው ሲሉ ገልጸው፣ አሁን ላይ ግን በማኅበር ተደራጅተው እየጠበቁ ቢሆንም ሊሠራ የሚችል ባለሀብት ማግኘት እንዳልቻሉ ገልጸዋል።
ለአብነትም በአንድ አካባቢ የሚገኝ የመዳብ ማዕድን ለማውጣት ማኅበር አደራጅተው እየጠበቁ እንደሆነ በመግለጽ፣ መሥራት የምንችልበት ሁኔታ ቢፈጠር ሌሎች ብዙ ፈልገን ያገኘናቸው ማዕድናት አሉ ብለዋል።
በዞኑ ካማሺ ከተማ የሚኖሩት ኤጀርሶ ዓለማየሁ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ በተለይ የከሰል ድንጋይ ማውጣት ላይ ለተሰማሩ ወደ 200 ለሚደርሱ ባለሀብቶች ሕዝቡ ተደራጅቶ በጋራ ሲሠራ የነበረ ሲሆን፣ በዞኑ የጸጥታ ችግር ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ሥራ አቁመዋል።
ሰላም በነበረበት ጊዜ በሕገ ወጥ መልኩ ማዕድናትን እያወጡ የመሸጥ ተግባር መኖሩንም ጠቁመው፣ በተለይ ‹ኦሜቲስት› የሚባል ማዕድን ወደ ኦሮሚያ ክልል በመውሰድ በኪሎ 500 ብር ሲሸጥ እንደነበር ጠቁመዋል። አክለውም፣ ብዙዎች በኪሳቸው እየደበቁ አንድና ኹለት ኪሎ ማዕድን ሲሸጡ እንደነበር አንስተዋል።
በዞኑ በሚገኙ ኹሉም ወረዳዎች በጣም በርካታ የተለያዩ ማዕድናት ክምችት መኖሩን በማንሳትም፣ በዚህ ወቅት ግን የሚገዛ አካል ባለመኖሩ የሚቆፍር አካል የለም ነው ያሉት።
ሰላም በነበረበት ወቅት በዞኑ ማዕድን ማውጣት ተግባር ላይ ተሰማርተው የነበሩት ኢትዮጵያ ባለሀብቶች መሆናቸውን ከገለጹ በኋላም፣ አንድ የውጭ ኩባንያ አጋሎ ወረዳ ላይ በ14 ቀበሌዎች ማኅበራትን አደራጅቶ ወርቅ ለማውጣት ሲንቀሳቀስ እንደነበር አውስተዋል።
በወቅቱ ባለሀብቶች ከተደራጁ ማኅበራት ጋር ሲሠሩ 70 በመቶ ለባለሀብቱ፣ 30 በመቶ ያህሉ ደግሞ ለማኅበሩ ይከፋፈል የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ ማዕድን ሚኒስቴር አሠራሩን አሻሽሎታል የሚባል መረጃ መስማታቸውን ጠቁመዋል።
ካማሺ ዞን ለረዥም ጊዜያት የጸጥታ ችግር እንዳለበት የሚታወቅ ሲሆን፣ በዚህ ወቅት የመከላከያ ሠራዊት በተለያዩ ቦታዎች ገብቷል ነው ያሉት።
በዞኑ ይገኛሉ ከተባሉ በርካታ የማዕድን ክምችቶች ለአብነትም እንደ ወርቅ፣ ኳርትዝ፣ ድንጋይ ከሰል፣ ኦሜቲስት፣ መዳብ፣ እብነ በረድ፣ እጣን እንዲሁም ‹‹magnetic stone›› እና ‹‹opal›› ካልተጠቀሱ ሌሎች ማዕድናት ጋር በብዛት እንደሚገኙ ተመላክቷል።
ኢትዮጵያ የማዕድን ሀብቷን በአንድ ቋት መዝግቦ ለማስቀመጥና ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማዋል የምትገለገልበት የማዕድን ዳታ ቤዝ ፕሮጀክት ቀርጻ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን ማዕድን ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል።
የማዕድን ዳታ ቤዝ ፕሮጀክቱም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ማዕድናት ያሉበትን ቦታ እና መጠን ለማወቅ እንደሚረዳ ነው የተገለጸው።
አዲስ ማለዳ በጸጥታ ችግር ምክንያት ችግር ስላጋጠማቸው የማዕድን ቁፋሮ ሥራዎች ከማዕድን ሚኒስቴር ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ብትሞክርም ሳይሳካ ቀርቷል።
ቅጽ 4 ቁጥር 193 ሀምሌ 9 2014



