በደንግ ወይም በዚካ ቫይረስ አማካኝነት የሚመጣ በሽታን የምታስተላልፈው ትንኝ ለመራባት ባስፈለጋት ጊዜ ደምን ስለምትሻ ቆዳን ነክሳ ትመጠዋለች። ይህን በምታደርግበት ወቅትም በሽታ አምጪ ቫይረስን ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው በማስተላለፍ እስከ ሞት የሚያደርስ ጉዳት ልታስከትል እንደምትችል ይታወቃል።
በተለምዶ የወባ በሽታ አስተላላፊ እንደሆኑ የሚታወቁት ቢንቢዎች እርስ በእርስ የሚግባቡበትና እንደንቦች ውዝዋዜ መልእክት የሚለዋወጡበት መንገድ አላቸው። ከዚህ ቀደም ይፋ በተደረገ ምርምር ትንኞቹ ጠረንን ተከትለው የሚነክሱትን ዒላማ እንደሚመርጡ ታውቆ ነበር።
ቢንቢዎች የሚመርጡትን የሚነከስ የሰው ዓይነት የሚለዩት በማሽተት እንደሆነ ቢታወቅም እንዴት አድርገው ጠረኑን እንደሚግባቡበት አይታወቅም ነበር። የወባ በሽታን የሚያመጡት ትንኞችም ተመሳሳይ ባሕሪ ቢኖራቸውም፣ ሠሞኑን ይፋ የተደረገው ጥናት ያተኮረው ግን በቫይረስ አማካኝነት ስለሚተላለፉት ዚካ እና ደንግ በሽታዎች ነው።
ዓለም ዐቀፍ የተመራማሪዎችን ቡድን ባካተተው በዚህ የምርምር ሥራ፤ አንዳንድ ቫይረሶች የተጣቡትን የሰውነት አካል ጠረን በቀላሉ መቀየርና ወደ ሌላ አካል መተላለፍ የሚያስችላቸውን ተግባር በጠረን አማካኝነት አስተላላፊ ቢንቢዎችን ተጠቅመው ማካሄድ እንደሚችሉ አውቀዋል። በቆዳ ላይ የሚወጡ ጠረን ያላቸው ላብ መሳይ ንጥረ ነገር አመንጪዎች ተግባራቸውን ይበልጥ እንዲጨምሩ ከሚያደርጉት መካከል በደቡብ አሜሪካና አፍሪካ ውስጥ በብዛት የሚከሰቱት ዚካና የደንግ ትኩሳት በመባል የሚታወቁት በሽታ አምጪ ቫይረሶች በግንባር ቀደምነት ተቀምጠዋል።
ኹለቱን በቫይረስ አማካኝነት የሚከሰቱ በሽታዎችን የሚያስተላልፉት ትንኞች አንዴ ሲነክሱ ሰውነት ላይ የሚተዉት ንጥረ ነገር ሌሎች ተከትለው እንዲነክሱና በሽታውን አምጪ ቫይረስ እንዲያስተላልፉ የሚያደርግ ነው። ሌሎች ቢንቢዎች በበሽታው የተለከፈን ሰው ይበልጥ ስለሚመርጡ ጠረኑ ያለበትን ቅድሚያ ይሰጡታል ሲሉ ተመራማሪዎች ግኝታቸውን ‹ዘ ኮንቨርሴሽን› ላይ ይፋ ማድረጋቸውን ኒው አትላስ አስነብቧል።
እንደተመራማሪዎቹ ገለፃ ከሆነ፣ ጥናቱን ለማካሄድ በርካታ በቫይረሶቹ የተያዙና ሌሎች ምንም ዓይነት በሽታ የሌለባቸውን አይጦች ተጠቅመዋል። እነዚህ የቤተ ሙከራ አይጦች ባሉበት ዝግ ቦታ ቢንቢዎቹን እኩል በመልቀቅ ምልክት አድርገው ትንኞቹ የትኞቹን አይጦች ለመንከስ እንደሚሽቀዳደሙ መዝግበዋል።
የቢንቢዎቹን ምርጫ ሲያስተውሉ፣ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም አብዛኞቹ ሰውነታቸው ውስጥ ቫይረሱ ያለባቸውን አይጦች መርጠው ደማቸውን ለመምጠጥ ሲታትሩ ተመልክተዋል። ይህን ያስተዋሉት ተመራማሪዎች አይጦቹን እንዴት ሊለዩዋቸው እንደቻሉ ለማወቅ ደማቸው ውስጥና ቆዳቸው ላይ ያለ ንጥረ ነገርን በመለየት በብዛት ያሉባቸውን ኬሚካሎች አውቀዋል። ወደ 20 ገደማ የሚሆኑ ተናኝ ጋዝ መሰል የሚሸተት ጠረን የሚያወጡትን በመለየትም ለየብቻ አይጦች ላይ አድርገውታል።
በበሽታዎቹ በተለከፉ አይጦች ናሙና ውስጥ ያሉ ንጥረ ነገሮችን ለይተው በተለያዩ አይጦች ላይ በመጨመር ድጋሚ ለቢንቢዎቹ አጋልጠዋቸዋል። እነዚህ ልዩ ልዩ ንጥረ ነገሮች ደማቸው ውስጥ እንዲበዛ ከተደረገባቸው አይጦች መካከል ቢንቢዎቹ የተወሰኑትን በይበልጥ መርጠዋል። ‹አሴዶፌኖን (acetophenone) የተሰኘው ንጥረ ነገር ያለባቸውን አይጦች በይበልጥ መምረጣቸውን የታዘቡት ተመራማሪዎች፣ ስለምንነቱ ጥናትን አካሂደዋል።
አሴዶፌኖን የተባለው ንጥረ ነገር የሰውነት ቆዳ ላይ ከተለመደው መጠን በ10 እጥፍ ላብ መሳይ ንጥረ ነገር እንዲወጣ በማድረግ የሰውነትን ጠረን የሚቀይር እንደሆነ ለማወቅ ችለዋል። ይህም በቀላሉ አካሉ እንዲለይ ስለሚያደርግ ትንኞቹ ይመርጡታል ብለዋል። ኬሚካሉ አይጦች ላይ በብዛት ከተገኘ ሌሎች ቢንቢዎች እንዲረባረቡ ከማድረጉ ባሻገር፣ የመጀመሪያዋ ነካሽ ቢንቢ ጠረኑ በንክሻዋ አማካኝነት እንዲመጣ በማድረግ ለሌሎች መልእክቱን በማስተላለፍ በሽታው በፍጥነት እንዲዛመት እንደምታደርግ ለማወቅ ተችሏል።
በበሽታዎቹ ከተለከፉ ሰዎች ብብት ውስጥም ናሙና ተወስዶ ሲመረመር በቫይረሶቹ የተጠቁት ሰዎች ላይ አሴዶፌኖን በብዛት ተገኝቷል። በጤነኞች ላይ ከተገኘው በብዙ እጥፍ የሚመነጭ በመሆኑን በሽታው ያለባቸው ላይ ተለይቶ ለቢንቢዎች ጠቋሚ መሆኑ ታውቋል። እንደአይጦቹም በቫይረሱ የተለከፈና ያልተለከፈ እጅ ሲቀርብላቸው የሚነክሱት በሽታው ያለበትን ሰው እጅ መሆኑን ለማወቅ ችለዋል።
ተመራማሪዎቹ የቢንቢዎቹን ምርጫ የሚወስነው ንጥረ ነገር አሴዶፌኖን መሆኑን ካወቁ በኋላ ይህን ንጥረ ነገር የሚያስመነጩ አካሎችን ለመለየት ባደረጉት ጥናት ቆዳ ላይ ያሉ ውሕዶች በባክቴሪያ አማካኝነት እንደሚያበዙት ለማወቅ ችለዋል። ቆዳ ላይ የሚኖር ባሲለስ (Bacillus) እየተባለ የሚታወቅ ሙልሙል ባክቴሪያ፣ ንጥረ ነገሩ የበለጠ እንዲመነጭ በማድረግ ትልቅ ድርሻ እንዳለው በሙከራ ማረጋገጣቸውን ተመራማሪዎቹ አሳውቀዋል።
ባሲለስ የተባለው የአሴዶፌኖን ኬሚካል አመንጪ ባክቴሪያ፣ በተለከፉና በጤነኛ አይጦች ላይ ያለውን መጠን በመለየትም ምን ያህል ለጠረኑ አመንጪ የሆነውን ንጥረ ነገር እንደሚያወጡ ተረድተዋል።
ጤነኛ ቆዳ ይህን መሰሉን ባክቴሪያ ለመከላከል ሬልማ (RELMα) የተሰኘ ሞለኪውል የሚኖረው ሲሆን፣ በቫይረሱ የተለከፉት ላይ ግን መጠኑ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶ ታይቷል። የዚካ እና የደንግ ቫይረሶች ሰውነት ላይ ሲገቡ ሬልማ የተሰኘውን ይህን ንጥረ ነገር እንዳይበዛ ስለሚገድቡት እሱ ይቆጣጠረው የነበረው ባክቴሪያ እንዲበዛ፣ በተራውም ጠረን አምጪዎቹ 10 እጥፍ ያህል እንዲጨምሩ ማድረጉ በቀላል ምልከታ በማስተዋል የምርምር ሥራቸውን ይፋ አድርገዋል።
የጠረን አምጪውን ማንነት መለየት ከቻሉ በኋላ ቀጣዩ ሥራቸው የነበረው ይህ ባክቴሪያ አሴዶፌኖንን አመንጭቶ ሌሎች ትንኞችን እንዳይጠራ ለማድረግና በሽታው በቢንቢዎች አማካኝንት ይበልጥ እንዳይስፋፋ ለማድረግ ስለሚያስችላቸው አማራጭ ጥናት ማድረግ ነበር። ይህም ባክቴሪያው የታወቀ እንደመሆኑ ብዛቱ የሚቀንስበትን መንገድ፣ መከላከያ የሚሆነውንም የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሠራሽ አማራጭን መለየት ነው።
በዚህም መሠረት በቫይረስ አማካኝነት የሚከሰተውን ይህን የሰውነት መደበኛ ተግባር መዛመትን የሚያስቀር ምንድን ነው ብለው የተለያዩ መንገዶችን መፈተሻቸውን ተናግረዋል። አይሶትሪቲኖይን (isotretinoin) የተሰኘ ከቪታሚን ኤ ይገኝ የነበረ ንጥረ ነገር፣ ሬልማ የተሰኘውን የሰውነታችንን የተፈጥሮ ኬሚካል ስለሚያስገኝ ይህንኑ በቫይረሱ ለተለከፉ በማቅረብ በሽታው ወደ ሌሎች በቀላሉ እንዳይተላለፍና ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን ማድረግ ይቻላል ሲሉ ግኝታቸውን ይፋ አድረገዋል።
በቫይረሱ የተጠቁ አይጦች አይሶትሪቲኖይን እንዲወስዱ ከተደረጉ በኋላ ቆዳቸው ላይ ያለውን የባሲለስ ባክቴሪያ መቀነስ በማስቻሉ ለቢንቢዎች የሚያስተላልፉትን መልዕክት መቀነስ አስችሏቸዋል። በዚህ መንገድ ቫይረሱ ያለባቸውም እንደሌለባቸው እኩል በትንኞቹ ተመራጭ እንደማይሆኑና በሽታው በቀላሉ እንዳይዛመት ማስቻሉ ታውቋል።
አይሶትሪቲኖይንን በሰዎች ላይ በመጨመር በተመሳሳይ በሽታውን እንዳያስተላልፉ ማድረግ የሚቻል መሆኑን ያሳወቁት ተመራማሪዎች፣ ዓለምን ስጋት ላይ የሚጥሉትን ቢያንስ የዚካ እና ደንግ ቫይረሶችን ስርጭት በቀላል ሕክምና ማስወገድ ይቻላል ብለዋል። ይህን መድኃኒት ማግኘት በማይችሉ ደሃ በሆኑና ቫይረሶቹ በሚያጠቋቸው አካባቢዎች የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፤ ንጥረ ነገሩን የሚያስገኙ ቪታሚን ኤ ያላቸውን ምግቦች በማዘውተር የቢንቢዎች ዒላማ ከመሆን መዳን እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
ዚካ ቫይረስ የሚተላለፈው በብዛት ቀን ቀን በሚናከሱ በበሽታው በተለከፉ አስቸጋሪ ቢንቢዎች አማካኝነት ሲሆን፣ በቫይረሱ የተለከፉ ሴቶች በወሊድ ወቅት ልጆቻቸው አካል ላይ ለውጥ በማስከተል ችግር ይፈጥራል፤ በትልልቆች ላይም ሕመምን ያስከትላል። ደንግ ቫይረስ ደግሞ ከዚካ በተለየ መልኩ ለሞት የሚዳርግ በሽታን የሚያስከትል ሲሆን፣ ለከፍተኛ ሕመምና ችግር ሊዳርግ የሚችል የዓለማችንን 390 ሚሊዮን ሰዎችን የሚያጠቃ ነው።
ሁለቱም ቫይረሶች በቢንቢ አማካኝነት የሚተላለፉ ቢሆንም ልዩነት አላቸው። ዚካ ‹Aedes albopictus› በተሰኘ ዝርያ የሚከሰት ሲሆን፣ ደንግ ደግሞ በ‹Aedes aegypti› አማካኝነት የሚተላለፍ ነው። ኹለቱም የየራሳቸው የሚያዘወትሩበት ንፍቀ ክበብ ቢኖራቸውም፣ ከአየር መዛባት ጋር በተገናኘ አውሮፓ ጭምር የተከሰቱና ለወደፊቱም የዓለማችን ወረርሽኞች እንዳሆኑ የሚያሰጉ ናቸው።
ቅጽ 4 ቁጥር 193 ሀምሌ 9 2014



