ቀድሞ ማመስገን!

0
1185

በአገራችን በማወቅ ወይም ባለማወቅ ካዳበርነው ልማድ መካከል ቸኩሎ ግብረ መልስ መስጠት አንደኛው ነው። ታግሶና ቀን ጠብቆ እንዲህ ቢሆንስ ከማለት ይልቅ፤ በቅንጣት ስህተት አልያም በአንዳች ጥሩ ነገር ብቻ በሚዛን አስቀምጦ፤ ‹እንዲህ ነው! እንዲያ ነው!› ብሎ መበየን በስፋት ይታያል። ይህን ያሉት መቅደስ ቹቹ፣ ይህን አመል በመውቀስ ሐሳባቸውን አጋርተዋል።

ሰው ከተፈጥሮ ቀጥሎ ማኅበራዊ ሕይወት የሚሠራው የሰዎች ስሪት ነው። ትውልድ በቀደመው ትውልድ ይገነባል፤ አንድ ግለሰብም በቤተሰቡ ከፍ ሲል በአካባቢው ማኅበረሰብ፤ ከዛ ሲልቅ ደግሞ በሚውልበት አካባቢና በሚኖርበት አገር ይሠራል (ጠብቆ ይነበብ)።

በዚህ መካከል አንዳንድ እንደ አገር ወይም እንደ ማኅበረሰብ አሉን የምንላቸው እሴቶች መቼ እንደጀመሩና እንደተነሱ ላናውቅ እንችላለን። ሰውነት ከሁሉም በላይ ቋንቋ የሚያደርገው አንድም ይህ ነው።

በአንድ ሥራ አጋጣሚ ከአንድ ጃፓናዊ ጋር በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ በተቀመጥኩበት ወቅት፤ እኔን ጨምሮ አብረን በጠረጴዛው ዙሪያ የተቀመጥነው ሰዎች ስለአገራችን ምን ሐሳብ እንዳለው ማወቅ ፈልገን ነበር። እናም ጥያቄዎችን አነሳንለት። ‹‹ኢትዮጵያ ካየኸው ሁሉ የገረመህ ወይም አዲስ የሆነብህ ምን አለ?›› የሚል ነበር ጥያቄው።

‹‹በጣም የገረመኝ ዐይን አፋር እና ሰው አክባሪ መሆናችሁ ነው። እኔ እንደዛ ያለ ስርዓት ያየሁት አገሬ ጃፓን ብቻ ነው። እዚህ እንዳየሁት ከሆነ ሰዎች ሲገናኙ ጎንበስ ብለው ሰላምታ ይለዋወጣሉ። አደባባይና መድረክ ላይም ተናገሩ ሲባሉ አፈር ይላሉ፤ ብዙም ፈቃደኛ አይደሉም። ይህ እኔም በአገሬ ያየሁት ነው።›› ሲል በተሰባበረ ኢንግሊዘኛ አስረዳን።

ከኢትዮጵያ በብዙ ሺሕ ኪሎሜትሮች በምትርቀው ጃፓን ተመሳሳይ የሰዎች እንቅስቃሴ ሊኖር የሚችለው፤ ሰውነት ብቻውን ራሱ በዓለም ላይ ያለን ሕዝቦች ሁሉ የምንግባባበት ቋንቋ በመሆኑ ነው። መቼ ነው ይህ ዓይነት ማኅበራዊ ስርዓት የተለማመዳችሁት ቢባል ግን፤ በዚህ ጊዜ ወይም ከዛ አካባቢና ከዚህ ሰፈር የወረስነው ነው ማለት አይቻልም። ባይሆን እንደውም እነዚህን እሴቶች መች አጣናቸው የሚለውን ለመመዝገብ ሩቅ አይደለንም መሰለኝ!

ወደነገሬ ልግባ። ይህን ያነሳሁት መቼ እንደሆነ ባናውቅም፤ ሰዎች የማኅበረሰብ ሥሪት መሆናችንን ለማውሳት ነው። በዛም ነው አንዳንድ አመሎቻችን ወይም ጠባዮቻችን የሚሠሩት። በዚህም መካከል ጥቂት ሰዎች ከተለመደው መንገድ ወጣ ብሎ ሊታዩ ይችላሉ እንጂ፤ ብዙዎቻችን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ፤ በማስተዋልም ሆነ በቸልታ…ለምን ብሎ ባለመጠየቅ በልምድ እንፈሳለን።

አንደኛው ዛሬ ላነሳ የወደድኩት ክፉ አመላችን ችኮላችን ነው። ለማመስገንም ለመውቀስም የሚቀድመን የለም። ጎበዝ አለመሆኔና ብዙዎቹን የአገሬን ቋንቋዎች አለማወቄ እንጂ፣ በእርግጠኝነት በብዙዎቹ ዘንድ ችኮላን የሚነቅፍ ብሂል እንደማይጠፋ አምናለሁ።

በቅርበት የማውቀው አንደኛው ግን ‹ቀድሞ ማመስገን ኋላ ለሐሜታ አይመችም።›› የሚለው ነው። ለማመስገን ስንሮጥ ነገ እንዲህ ቢሆንም ብሎ ማገናዘብም ሆነ ትላንት እንዲህ ነበር ለማለት እድል የምንሰጥ አይደለንም። አንዳንዴም አቸኳኮላችን በፍጹም ይቅርታ አድራጊ የሚያሰኝና ትላንትን ፍጹም የረሳ የሚመስል ነው። በእርግጥ የማስታወስ አቅማችን በተለያየ የአእምሮ አለመረጋጋት የተነሳ ሳይናጋ አልቀረም። በአንጻሩ ደግሞ ስንቸኩልና ‹ይሁን!› ብለን ስናመሰግን ጊዜና ዘመን ‹አበቃ!› ተብሎ ልክ ዛሬ ላይ የተዘጋ እንጂ ነገ የሚባል ቀን ያለ በማይመስል መልኩ ነው።

ቀድሞ ማመስገን ላይ ብቻ ሳይሆን ቀድሞ ባልተረጋገጠ ነገር መኮነን ላይም የሚቀድመን የለም። በድምሩ ችግሩ በቂ መረጃና እውቀት የሌለን ጉዳይ ላይ በቶሎ ግብረ መልስ ለመስጠትና ስሜትን ለመግለጽ እንፈጥናለን ነው። ይህም ብዙ ጊዜ ጉዳት እንጂ ትርፍ አስገኝቶን አያውቅም።

ብዙ ጊዜ በቀላሉ የሚሸወደው ቅንጣት ነገርን ከአንድ አንጻር ዐይቶ የሚወስን ሰው ነው። እንደ ማኅበረሰብም መንግሥትን በሠሩ ፖለቲከኞች ጭምር ማኅበረሰቡ በተደጋጋሚ ሲታለል የሚታየው፤ ከዚሁ የተነሳ ነው። ‹ቤታቸውን ክፍት እያደረጉ እኛን ሌባ ይላሉ› እንዳለች ድመት፤ ማኅበረሰብም በቀላሉ የመሸወድ አመሉ የተነሳ ለሸዋጆች ሥራ አያበዛባቸውም። ይቅርታ ብለው ኹለት የፍቅር ቃላትን ከእንባ ጋር ካቀበሉ፤ አመስጋኛቸው ብዙ ነው፤ አበቃ!

የሥነ ልቦና ወይም ሥነ አእምሮ ተማሪ ባለመሆኑ፤ በጉዳዩ ላይ ምን ተባለ ብዬ የተለያዩ ገጾችን አገላብጫለሁ። በአንዱ ላይ ለውሳኔ መፍጠን (Jumping to Conclusion) በሰዎች ላይ በብዛት የሚታይ አመል እንደሆነ ይገልጻል። በአገራችን በጉዳዩ ላይ የተባለውንና የሚባለውን ባላውቅም፤ ራሴን ጨምሮ እንደ ማኅበረሰብ በዙሪያዬ ያሉ ሰዎችን መመዘን ያስቻለኝን አንድ ንባብ ልጠቅስ ወደድኩ።

በዚህ ጽሑፍ ላይ ሰዎች ለውሳኔ የሚፈጥኑባቸው የተለያዩ መንገዶች ተዘርዝረዋል። አንደኛው ዝርው ወይም በወረደ አገላለጽ ‹ዝም ብሎ› መላምት ነው። ቀልቤ ነገረኝ ዓይነት ማለት ነው። ጽሑፉ ለምሳሌ የሚጠቅሰው አንድ ሰው አንድ መስኮቱ የተሰበረ ሆቴልን ዐይቶ፤ በዛ የተነሳ ብቻ ‹እዚህ ቤት የሚያቀርቡት ምግብ መጥፎ ነው የሚሆነው› ብሎ ሊያምን ይችላል።

በተመሳሳይ ምክንያታዊ የሆንን መስሎን በችኮላ እርግጠኛ የምንሆንባቸው ነገሮች አሉ። ጽሑፉ ይህን ሲገልጽ፤ አንድ የዘመኑ ምርጥ የሚባል መኪናን የያዘ ሰው ዐይቶ ‹ይህ ሰው ባለሀብት ነው› የሚል አስተያየት መስጠት ነው ይለዋል። ነገር ግን ውድ የሆነ መኪና የሚነዳ ሰው ነው ያየነው እንጂ ያ ሰው ሀብታም ይሁን ዐይሁን በዛ ማወቅ የሚቻል ሆኖ አይደለም። መኪናውን ለመኪናው ባለቤት የሚያደርስ ሾፌር ቢሆንስ?

እነዚህ ኹለቱ እንደ ማሳያ ያነሳኋቸው ቀላልና በየእለት ሕይወታችን ውስጥ የምናደርጋቸው ናቸው። አስበን ወይም ጥፋት ያመጣል ብለን ሳይሆን፣ ሳናውቀው በውስጣችን እነዚህን ዕይታዎች አሳድገናል። እነዚህ ታድያ ከፍ ሲሉ ነው እየጎሉ የሚታዩት።

ለምሳሌ አሁንም ከዛው ከንባቤ ያገኘሁትን ላውሳ። ጽሑፉ ‹Extreme extrapolation› ይለዋል። ይህም ጥቃቅነ ነጥቦችን ይዞ ወደ ውሳኔ የመፍጠን አመል ነው። ለምሳሌ ራቅ ካለ አንድ ቤት ውስጥ ጭስ ስናይ ‹ቤቱ እየተቃጠለ ነው› ብለን ልንገምት እንችላለን። ይህ ምንአልባት ቤትን ከእሳት ለማዳን ሊረዳ ይችላልና ምሳሌ ፍጹም እንዳይደለ ያዙልኝ፤ ግን ይህ ለውሳኔ የሚያፈጥን አመል ከዚህ ከፍ ሲል ፍረጃ እና መበየን ላይ ይደርሳል።

በማጣቅስላችሁ ጽሑፍ ላይ ይህን ነጥብ ‹Overgeneralization› እና ‹Labeling› ብሎ ያስቀምጠዋል። ኹለቱም በአንድ ወይም በጥቂት መረጃዎች መነሻነት ጠቅልሎ በመየንና መፈረጅን ይመለከታሉ። ዛሬ ላይ ወንዶች እንዲህ ናቸው፤ ሴቶች እንደዛ ናቸው የሚለው ቀላል የሚመስል ፍረጃ ከዚህ አመል የሚመነጭ ነው። ይህም እንደ እንቁላል ሐሳብ ቸል ተብሎ፤ ዛሬ ‹እገሌ ብሔር እንደዛ ነው፤ እነ እገሌ እንዲህ ናቸው› የሚል ፍረጃ ላይ አድርሶናል።

ልብ በሉልኝ! በችኮላ የሚመጣ ፍረጃችንና ብያኔያችን ለመውቀስ ብቻ ሳይሆን ለማመስገንም የሚውል ነው። በኹለቱም ወገን ግን ጠቅሞን አያውቅም። ወቀሳችን አሳዝኖን ምስጋናችንም አሳፈሮን ያውቃል። ከራሳችን ብሂል ጋር ሳይቀር ተስማምተን አናውቅም፤ ከ‹ቀድሞ ለማመስገን ኋላ ለሐሜታ አይመችም!› ጋር። በእርግጥ ይህም በራሱ አውድ እንከን ያለው ነውና በእኔ አንጻር ብቻ እንድታዩልኝ አደራ እላለሁ!

ሰዎች ለውሳኔ እንዲቸኩሉ የሚሆኑበት ሥነልቦናዊና አእምሮአዊ ትንታኔ አለው። ይህን እኔ ማብራራት ሥልጣን ስለሌለኝ፤ ለምንድን ነው የሚለውን ጥያቄ በየአውዳችሁ እንድትጠይቁ እጋብዛለሁ። በትክክል በቀላሉ ልንረዳው የምንችለው ግን ምክንያታዊ የመሆን አቅም መቀነስ አንዱ ለውሳኔ የሚያስቸኩል ምክንያት መሆኑን ነው።

ይህ አመል የሕክምና ባለሞያዎች ላይ ቢኖር በላችሁ ለአፍታ አስቡትማ! አንዲት ሐኪም ገር ቀርባችሁ ‹ራሴን ያመኛል ሆዴን ይቆርጠኛል› ስትሉ፤ ‹ይህማ እገሌ የሚባለው ቫይረስ ነው። ዐይነ ውሃዎትን ሳየው ገለመሌ የሚባለው ሕመም የሚይዞት ዓይነት ይመስላሉ› ብትላችሁ?

ኑሮን ከሕክምና ቀላል አድርገን ሳናስበው አልቀረንም። ለዛም ነው ለውሳኔ የምንቸኩለው፤ ዙሪያ ገባውን ለማየት ጊዜና ፋታ የማንሰጠውና ከውሳኔ በፊት ባለን ጊዜ ልብ ብለን ምክንያታዊ ለመሆን የማንሞክረው። ይህ እንደማኅበረሰብ ብዙ አስከፍሎናል ብዬ አምናለሁ።

እንደ አገር እንዲህና እንዲያ ብዬ ለውሳኔ (ለማመስገንም ይሁን ለመንቀፍ) መቸኮላችን ይህን አምጥቶብናል ብዬ እኔም ልፈርጅ አልደፍርም። ግን በአንድ በቀረበኝ ምሳሌ ነገሬን ልቋጭ።

አዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ በብዛት የሚታዩት የኪስ ፈታሽና የሞባይል ቀበኛ የሆኑ ነጣቂዎች የሚያደርጉትን አስታውሱ። በየጊዜው የሚሰርቁበትን መንገድ ይቀይራሉ። ይህም የማኅበረሰቡ ዕይታ ላይ መሠረት ያደረገ ነው። አንድ ሰሞን ትዝ ይለኛል የሥራ ቦርሳ ይዘውና ጥሩ ልብስ ለብሰው ነው የሚንቀሳቀሱት። ታድያ አንድ ሰው ሞባይሉን ከኪሱ ሲነጠቅ ዞሮ ሌባ ይፈልጋል። በአንጻሩ የእውነት የሰረቀውንና ‹ደኅና› ልብስ የለበሰውን ሰው አፋላጊ ያደርገዋል፤ አይጠረጥረውም።

ለምን? ሌባ መልክ ያለው ያህል ለሌባ አንዳች ገጽታ ሰጥቷልና ነው። ‹ደኅና› መልበስም በዛ ልክ ታማኝ ተደርጎ ተሰይሟል። ያው አሁን እንኳ በሚገባ የተነቃ ይመስለኛል፤ እጅግ ብዙ ሰው ከተሰረቀ በኋላ ማለት ነው!  በጥቅሉ የሚበጀው ግን፤ ሌባ ከየትም ሊመጣ ስለሚችልና የተለየ መልክና ቁመና የሌለው ስለሆነ፤ ኪስን መጠበቅ ነበር!

እስቲ አንቸኩል! ቀድመን ማመስገን በኋላ ለሐሜት ስለማይመች ብቻ ሳይሆን፣ በድምሩ ጠቅሞን አያውቅም። ከቻልን ይህን አመል ለመቀየር ልብ ብለን ምክንያታዊ በመሆን ልንቀይረው እንሞክር። ከፈተና ያውጣን እንጂ፣ ቀድመን እንድናመሰግን አልያም እንድንወቅስ የሚገፋፋንና ቀጣይ የሚፈትነንን ማን ያውቃል!


ቅጽ 4 ቁጥር 193 ሀምሌ 9 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here