በፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ከ79 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች ለብክነት መጋለጣቸውን የመንግሥት ግዢና ንብረት ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
የመንግሥት ግዢና ንብረት ባለሥልጣን የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሰጠኝ ገላን ለአዲስ ማለዳ እንዳሳወቁት፣ ባለሥልጣኑ በኢትዮጵያ በሚገኙ በፌዴራል መሥሪያ ቤቶች እና በከፍተኛ የመንግሥት የትምህርት ተቋማት በሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ለብክነት የተጋለጡ ብረታ ብረቶችን ለይቶ በገንዘብ ተምኖ አስቀምጧል።
ዳይሬክተሩ አክለውም፣ ለብክነት የተጋለጡ ንብረቶችን መለየት የተቻለው በሦስት ወራት ውስጥ በተደረገው የዘመቻ ሥራ መሆኑን እና በዚህም 79 ሚሊዮን 638 ሺሕ 243 ብር ግምት ያላቸው ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች ለብክነት እንደተጋለጡ ማረጋገጣቸውን ጠቁመዋል።
ለዚህም 1 ሚሊዮን 345 ሺሕ 841 ኪሎግራም የሚመዝን ስቲል ብረት፣ 1 ሚሊዮን 255 ሺሕ 148 ኪሎግራም የሚመዝን አልሙኒየም ብረት፣ 105 ሺሕ 120 ኪሎግራም የሚመዝን ነሐስ ብረት፣ 174 ሺሕ 460 ኪሎግራም የሚመዝኑ የተለያዩ ያገለገሉ የተሽከርካሪ መለዋወጫ ብረታ ብረቶች፣ በአጠቃላይ አምስት ዓይነት የቁርጥራጭ ብረታ ብረት ዓይነቶች መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ከላይ የተጠቀሱት ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች በዋናነት ብዙ በሚባል ደረጃ ከሚገኙባቸው ተቋማት መካከል፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ አርሲ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም መዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ተጠቃሽ ተቋማት ናቸው።
የመንግሥት ግዢና ንብረት ባለሥልጣን ሁሉም የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች በተቋማቸው የሚገኙ ያገለገሉ እና የተከማቹ ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶችን በቀጣይ ሦስት ወራት ውስጥ ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ተነጋግረው ለሽያጭ እንዲያቀርቡ ብሏል።
ተቋማት ከሽያጭ የሚያገኙትን ገቢ በወቅቱ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ገቢ እንዲያደርጉ ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል።
በተጠቀሱት ወራት የቁርጥራጭ ብረታ ብረቶችን ለሽያጭ የማያቀርቡ እና ገቢውን የማያስገቡ ተቋማት ላይ ገንዘብ ሚኒስቴር ራሱን የቻለ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወስድና በሕግ ተጠያቂ እንደሚያደርግም ተነግሯል።
በመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን አስተባባሪነት በሁሉም የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ያገለገሉ እና የተከማቹ ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች፣ ተሽከርካሪዎች እና ማሽነሪዎችን ከሚያዝያ 4/2013 ጀምሮ ምዝገባ እንዲከናወን ተደርጎ የንብረቶች ዓይነት እና ብዛት ያካተተ ዝርዝር ሪፖርት ለባለሥልጣኑ መቅረባቸውም አይዘነጋም።
ከዚህ በተጨማሪ ወደ መንገድ ገብተው አገልግሎት የማይሰጡ ተሽከርካሪዎች እና ማሽነሪዎችን፣ ተቋማቱ ከቀድሞው ከብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ጋር በጋራ በመሆን የተለዩት በስክራፕ መልክ እንዲወገዱ መወሰኑ ይታወቃል።
በዚህ መሠረት ከላይ የተጠቀሱት እና ሁሉም ቁርጥራጭ ብረታ ብረት ያላቸው ተቋማት ንብረታቸውን በሽያጭ እንዲያስወግዱ ተጠይቋል።
የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን በተጨማሪ በፌዴራል ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ከሚመለከታቸው የመንግሥት ባለድርሻ አካላት ጋር ተነጋግረው የኬሚካል እና የኤሌክትሮኒክስ ዌስት አወጋገድ ስርዓት ዝርጋታ ሂደት እስኪጠናቀቅ ድረስ፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከጥቅም ውጭ የሆኑ ኬሚካሎች እና የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶች ላይ ጥንቃቄ እና ጥበቃ ከማድረግ ባለፈ የአሠራር ማሻሻያ ሰርኩላር እንዲደርሳቸው መደረጉ ተነግሯል።
ቅጽ 4 ቁጥር 193 ሀምሌ 9 2014



