ከአምናው በእጥፍ ጨምሯል
በ2014 በጀት ዓመት 50.1 ሚሊዮን ብር በሚያወጡ በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ ዝርፊያ ተፈፅሞብኛል ሲል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር በቀለ ክፍሌ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በ2014 በጀት ዓመት ማለትም ከሐምሌ 1/2013 እስከ ሰኔ 30/2014 ድረስ ባሉት ጊዜያት በተደራጁ አካላት እና በግለሰቦች በኩል 50 ነጥብ 1ሚሊዮን የሚያወጡ የተቋሙ መሠረተ ልማቶች ላይ ዝርፊያ ተፈፅሟል ብለዋል።
በዚህም 26 ሚሊዮን ብር የባቡር ኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ ከ 24 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሁ በኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ፣ በሕገወጥ መስመር ዝርጋታ እና በሌሎች ምክንያቶች በአጠቃላይ 50 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በተቋሙ ላይ ዝርፊያ መፈፀሙን የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።
ዝርፊያው የተፈፀመው የባቡር መስመር በተዘረጋባቸው በለሚ ኩራ፣ በየካ፣ በቦሌ፣ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ እና በሁሉም ክፍለ ከተሞች የመስመር ዝርጋታ በተዘረጋባቸው መስመሮች ላይ ነው።
በባለፈው በጀት ዓመት በተመሳሳይ ወቅት በባቡር ኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ዝርጋታ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን፣ በኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ እና በሌሎች ዘርፎች ላይ እንዲሁም 24 ሚሊዮን የሚጠጋ ንብረት ላይ በድምሩ 26 ሚሊዮን ብር የሚገመት የመሠረተ ልማት ላይ ዝርፊያ የተፈፀመ ሲሆን፣ ይህም ከ 24 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው ተብሏል።
ለዚህም ዝርፊያ መጨመር በአዲስ አበባ ከተማ የተደራጁ እና ያልተደራጁ ሕገ ወጥ ዘራፊዎች መበራከታቸው በምክንያትነት እንደሚጠቀስ የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከፀጥታ አስከባሪ አካላት ጋር በጋራ በመሆን በኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ላይ የሚፈፀውን ዝርፊያ ለመቆጣጠር እየተሠራ ነው ተብሏል።
በተጨማሪ፣ የከተማዋን ነዋሪ በማጭበርበር ሕገ ወጥ የመስመር ዝርጋታ የሚዘረጉ አካላት እንዳሉ ተቋሙ ደርሶበታል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ከዚህ ሕገ ወጥ አሰራር ኅብረተሰቡ እንዲቆጠብ አሳስበዋል።
ዳይሬክተሩ አያይዘውም፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ችግርን ለመቅረፍ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ በ50 ኪ.ሜ ራዲየስ በሚገኙ ከተሞች ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ተደርጎ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም በመዲናዋ እና አካባቢው የሚስተዋለውን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ችግር ለመፍታት በ85 ሚሊዮን ዶላር የመልሶ ግንባታና የአቅም ማሳደግ ፕሮጀክት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑም ተነግሯል።
ፕሮጀክቱ በኤሌክትሪክ ማሰራጫ መስመሮች እርጅና ምክንያት የሚስተዋለውን የኃይል መቆራረጥና መዋዠቅ ችግር ለመፍታት የሚተገበር መሆኑ ተገልጿል።
በዚህም የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት የተለያዩ ማስተላለፊያና ማሰራጫዎች መልሶ ግንባታና አቅም ማሳደግ ፕሮጀክቶችን ነድፎ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል ተብሏል።
ፕሮጀክቱ ቻይና ኤሌክትሪክ ፓወር ኢኩፕመንት ቴክኖሎጂ እና ቻይና ናሽናል ሄቪ ማሽነሪ ኮርፖሬሽን በተባሉ የቻይና ተቋራጮች እየተገነባ ነው።
ቅጽ 4 ቁጥር 193 ሀምሌ 9 2014


