በጋምቤላ 500 ሺሕ ብር የሚገመት የኢንቨስተሮች ንብረት በስደተኞች መዘረፉ ተነገረ

0
1489

በጋምቤላ ክልል ኢታንግ ልዩ ወረዳ በመጠለያ ካምፕ የሚገኙና ከዚህ ቀደም ከደቡብ ሱዳን የመጡ ስደተኞች ከ500 ሺሕ ብር በላይ የሚገመት የባለሀብቶችን ኢንቨስትመንቶች መዝረፋቸውን ታማኝ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

ለደኅንነታቸው ሲባል ሥማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ መረጃ አቀባዮች እንደተናገሩት ከሆነ፤ ቦታው ገና በስጋት ቀጠና ውስጥ በመሆኑ በውል ማወቅ ቢያዳግትም በስደተኞቹ የተዘረፈው ንብረት በብር ሲተመን እስካሁን ባላቸው መረጃ መሰረት ከ500 ሺሕ ሊልቅ እንደሚችል ነው ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት።

ዘረፋውን የፈጸሙት ከደቡብ ሱዳን የመጡና ቁጥራቸው ከ10 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ስደተኞች ናቸው የተባለ ሲሆን፤ ስደተኞቹ ጥቃቱን ያደረሱት በጋምቤላ ክልል ኢታነግ ልዩ ወረዳ ሥር በሚገኙ ‹ብቁሌ› እና ‹ሙኘን› ከተሰኙ ኹለት የስደተኞች ካምፕ ገልብጠው ወጥተው ነው ተብሏል። ተዘረፉ የተባሉት ኢንቨስትመንቶቹ በኢታንግ ልዩ ወረዳ የተለያዩ ሥፍራዎች ከ‹ብቁሌ› እና ‹ሙኘን› የስደተኞች ካምፕ በቅርብ ርቀት እንደሚገኙ በምንጮቹ ተመላክቷል።

የዘረፋ ጥቃቱ ሰሞኑን እንደተከናወነ ያመላከቱት መረጃ አቀባዮቹ፣ የኦነግና የጋምቤላ ታጣቂዎች የሚያደርሱትን ጥቃት ተከትሎ ሥፍራው የስጋት ቀጠና ውስጥ በመሆኑ መንግሥትም እስከ አሁን ለሚሰነዘረው ጥቃት እልባት መስጠት አልቻለም ነው የተባለው። ይህን ተከትሎም በአካባቢው ያሉ ሰዎችም ስጋት እንደተጋረጠባቸው ተነስቷል።

ስደተኞቹ ጥቃቱን ለማድረስ ምቹ ሁኔታ የፈጠረላቸው ከኹለት ሳምንት በፊት በጋምቤላና ኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች የአማራ ተወላጅ ኹለት ኢንቨስትመንቶች መቃጠላቸውን ተከትሎ ባለሀብቶቹ ንብረታቸውን ሳያወጡ በመሸሻቸው ነው ተብሏል።

ኢንቨስተሮቹ አንዳንድ ትራክተሮችን ይዘው ከመውጣት ውጪ ሌላው ሙሉ ንብረታቸው በካምፖቻቸው ውስጥ እንደነበርም የአዲስ ማለዳ ምንጮች ያስታወሱ ሲሆን፤ ሰሞኑን ዘረፋ የደረሰባቸው ከመቃጠል በተረፉ ቀሪ ካምፖች ነው።

ከስምንት ዓመታት ወዲህ እየፈለሱ እንደመጡ የሚነገርላቸው ስደተኞቹ ዲማ እና ቦንጋ በሚገኙ ሌሎች የስደተኞች ካምፕ ሲሞሉ ነው ወደ ኢታንግ ልዩ ወረዳ ካምፖች የተከማቹት የተባለ ሲሆን፤ ኢታንግ ልዩ ወረዳ ለቄለም ወለጋ ቅርብ በመሆኑ ታጣቂዎች ያደረሱት ጥቃት ለስደተኞቹ የዝርፊያ በር ሳይከፍት እንዳልቀረ ተጠቅሷል።

ከደቡብ ሱዳን የመጡ ስደተኞች ቁጥር ወደ 500 ሺሕ መድረሱንና የተዘረፈው ሀብት ንብረትነቱ 41 የሚሆኑ የአማራ ባለሀብት ኢንቨስተሮች መሆኑን የአዲስ ማለዳ ታማኝ ምንጮች ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ ከዚህ በፊት በጋምቤላ ክልል ኢታንግ ልዩ ወረዳ በባለሀብት ኢንቨስትመንቶች በቀን ሥራ ተሰማርተው የነበሩ 80 ወጣቶች፣ ራሳቸውን የጋምቤላ ነጻ አውጭ ንቅናቄ ብለው በሚጠሩና በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መታገታቸውን እንዲሁም ኹለት የባለሀብት ኢንቨስትመንቶች መቃጠላቸውን መዘገቧ አይዘነጋም።

በመሆኑም፣ ታጋቾቹ ከታገቱበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን (ይህ ዘጋባ እስከተዘጋጀበት ቀን ድረስ) ያሉበት ሁኔታ እንዳልታወቀ ነው አዲስ ማለዳ ከመረጃ አቀባዮቿ የሰማችው።

ሰሞኑን የኢንቨስተሮች ንብረት መዘረፉን ለአዲስ ማለዳ የገለጹት ምንጮች በተለይም ከኹለት ሳምንት በፊት 80 የሚደርሱት የቀን ሠራተኛ ወጣቶች በታጣቂዎች ከታገቱና ኹለቱ ኢንቨስትመንቶች ከተቃጠሉ ወዲህ ኢታንግ ልዩ ወረዳ በስጋት ቀጠና ውስጥ መሆኗን ጠቁመዋል።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ኦገቱ አዲንግ፣ ስደተኞቹ ላደረሱት ዘረፋ ምላሽ ለማግኘት በተደጋጋሚ ስልክ ቢሞከርም ለማንሳት ፈቃደኛ መሆን አልቻሉም። የአዲስ ማለዳ ምንጮችም ወደ ኃላፊው ደውለው እንደነበርና ጉዳዩን ሰምተው ስልክ እንደሚዘጉባቸውም ጠቁመዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 193 ሀምሌ 9 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here