ለተወካዮቻችን!

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

የተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት ጥያቄ አቅርበው መልስ የሚጠይቁበት መድረክ የብዙዎችን ቀልብና ጆሮ ያገኛል። ተስፋ ነውና ሰውን የሚያኖረው፣ አንዳች ደኅና የሆነ ነገር እንሰማለን ብሎ ብዙ ሰው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉባኤያት ጆሮውን ይሰጣል።

አንዳንዴ ውሃ ያነሳሉ የሚባሉ ጥያቄዎች ሲቀርቡ፣ አንዳንዴ ደግሞ ‹ምን ዐይተን ነው የመረጥናቸው!› የሚያሰኙ ዋጋቸው የወረደ ጥያቄዎች ይቀርባሉ። በዛ ቦታ ላይ የሚገኙ የምክር ቤቱ አባላት ከተለያየ ማኅበረሰብ ተወክለው የቀረቡ መሆናቸው እሙን ነውና፤ የወከሉትን ማኅበረሰብ ድምጽና ቅሬታ በአግባብ ያሰማሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከጥቂቶቹ በቀር ግን ይህን ሲያደርግ የሚታይ የለም።

በተለይ ሴት የተወካዮች ምክር ቤት አባላት፤ በበኩሌ ቅር ያሰኙኛል። ይወከሉ፣ ቦታ ይሰጣቸው፣ ድምጽ እንሁንና ይመረጡ ወዘተ እየተባለ ሲዘመርላቸው፤ የተመረጡበት አካባቢም እልል ሲልላቸው እንደነበር አያጠራጥርም። ግን ቢያንስ ስለእናቶች ሐዘንና ሰቆቃ እንኳ አቤት ሲሉ አይሰማም።

ይህን ስል ከባለሥልጣን ወይም ተሿሚ ወይም ተወካይ ሴቶች ከወንዶች የበለጠ ይጠበቅባቸዋል፤ ትንሽ ደንቀፍ ቢሉም መወቀስ አለባቸው ለማለት አይደለም። አልያም ያንን ከመሰለ ዕይታ የመነጨ አይደለም። ነገር ግን ምክር ቤት ላይ ጥያቄ ሲነሳ፤ ወንዶቹ ቢቀር እንዴት ሴቶቹ ለእህቶቻቸው ሰቆቃ አንድ ጥያቄ እንኳ አያነሱም?

‹ምን ዋጋ አለው?› የሚል አይጠፋም። ጥያቄ መጠየቅ ብቻ መፍትሄ ያመጣል ማለት አለመሆኑን አሁን በሚገባ ሳንረዳ አልቀረንም። ግን ቢያንስ ተወካዮቻችን ሆነው ወንበር ላይ መሆናቸውን የሚያስታውሰንን አንድ ሥራ እንኳ እንዴት አይሠሩም? ‹ትንሹ›ና የእነርሱ ሥራ ‹‹ሴቶች በየቦታው ለመከራና ስቃይ ተዳርገዋል። መኖርም ሆነ መሞት፤ ከኹለቱ የተሻለ የትኛው ነው ብሎ መጠየቅ እንኳ የሚከብድበት ጊዜ ላይ ነን። ፍትህ ይሰጣቸው፤ ተዉ!›› ማለት እንዴት ይቸግራቸዋል?

እንደ ማኅበረሰብ ሊያግባቡ የሚችሉ እሴቶቻችንን ሁሉ ፖለቲካ መጫወቻ ካደረጋቸው ሰነባብቷል። ሀይማኖት ነበር፤ እሱም በተቋማቱ በኩል ተደነቃቅፎ የራሱን ሕመም እያባበለ ነው። ሁሉም ለብሔሩ ነው የሚጮኸው። እናስ ምን አለበት ሴቶችስ ስለሴቶች ድምጽ ቢያሰሙ?

መቀሌም ሆነ ወለጋ፤ ጎንደርም ሆነ ሐዋሳ፣ ዲላም ሆነ አሶሳ የምትገኝ ሴት፤ መከራዋ አንድ ነው። ረሀብ ይሁን ጦርነት፣ መፈናቀልም ሆነ ግድያ፤ ለእናት ሁሉም ሕመም አንድ ነው። እንኳን ያን የሚያህል መከራ ቀርቶ ከባድ ዝናብ ለእናት ስጋት ነው። የአንዱ ክልል እናት ስታለቅስ የሌላው ክልል ልትስቅ አትችልም፤ እናት ነግ በእኔን ታውቃለችና። እናስ ምን አለበት ስለእናቶች፣ ስለሴቶች አቤት ቢሉ፤ ቢሞግቱና ቢታገሉ። ምንስ እየሠሩ ነው?

መቅደስ ቹቹ


ቅጽ 4 ቁጥር 193 ሀምሌ 9 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች