ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ በስደተኞች ላይ በደረሰ ጉዳት ወደ 300 የሚጠጉ የኤርትራ ስደተኞች ገና ያሉበት አልታወቀም ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ገለጸ።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ ስደተኞችና ፍልሰተኞች መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር እንጉዳይ መስቀሌ፣ ባለፈው ኅዳር ወር ላይ በወጣው ጣምራ ምርመራ ግኝት በትግራይ ክልል የነበሩ ኤርትራውያን ጉዳት ማስተናገዳቸውን ተከትሎ፣ የተወሰኑት ወደመጡበት በግድ ሲመለሱ ሌሎች ደግሞ መበታተናቸውን አውስተው፣ ከዚያ ውስጥ 300 የሚጠጉት ያሉበት እንደማይታወቅ በሪፖርቱ ተገልጾ ነበር ብለዋል።
ሆኖም በወቅቱ መጥፋታቸው ስለተገለጸው ስደተኞች እስከ አሁን የተገኘ አዲስ መረጃ ባለመኖሩ ኮሚሽኑ ካለፈው ዓመት ሰኔ እስከ አሁኑ ዓመት ሰኔ ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት ላይም ተካቷል ነው ያሉት።
ዳይሬክተሯ የኤርትራውያን ስደተኞችን አስመልክቶ ኮሚሽኑ በዓመቱ በአብዛኛው ሲቀበል የከረመው ጥያቄ መሆኑን አንስተው፣ ይሁን እንጂ ትግራይ ክልል ውሰጥ ሥራውን መሥራት የማይችል በመሆኑም መረጃ ማግኘት አይችልም ብለዋል።
ጠፉ የተባሉት ስደተኞች ወደ ኤርትራ ሄደው እንደሆነ በኤርትራ መንግሥት በኩል የማጣራት መኩራ ተደርጎ እንደሆነ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም፣ ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተውን ጉዳይ ብቻ ነው የማጣራት ኃላፊነት ያለው ሲሉ ገልጸዋል። ከዚህ ውጪ ያለው የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ተግባር እንደሆነ አንስተዋል።
አክለውም፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስፈጻሚ አካል ባለመሆኑ የደረሰባቸውን ጉዳት ካሳወቀን በኋላ፣ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እንዲከታተለው በተደጋጋሚ መድረኮችን በማዘጋጀት አስገንዝበናል ሲሉ ገልጸዋል።
በስደተኞች ላይ ከደረሰው ከፍተኛው የሰብዓዊ መብቶች አደጋ የተከሰተው በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ እንደመሆኑ፣ በክልሉ የነበረው የኤርትራውያን ስደተኞች የመጠለያ ጣቢያ መውደሙን ጨምሮ፣ በመጠለያ ጣቢያው በተሰነዘረው ጥቃት በደረሰው ሞት፣ የስደተኞች መበትንና በግድ ወደመጡበት እንዲመለሱ መደረግ ነው ተብሏል።
ኮሚሽኑ በዚህ ወር መጀመሪያ ይፋ ባደረገው ዓመታዊ ሪፖርቱ፣ በተጨማሪም በቤንሻጉል ጉምዝ ክልል ይኖሩ የነበሩ የሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ስደተኞች በክልሉ በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ ለመፈናቀልና ለመብት ጥሰቶች ተዳርገዋል ነው ያለው።
እንዲሁም በሶማሌ ክልል የሚኖሩ ጥገኝነት ጠያቂዎች የስደተኝነት አወሳሰን ሳይደረግላቸው ለረዥም ዓመታት መቆየታቸውን ጠቅሶ፣ በጋምቤላ ክልልም በስደተኞችና በተቀባይ ማኅበረሰብ መካከል በሚነሳ ግጭት የደኅንነት ስጋት ላይ መውደቃቸውን አመላክቷል።
ከመንግሥት ውስንነትና ከዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች የሚቀርበው ሰብአዊ እርዳታና አገልግሎት የተሟላ ባለመሆኑም፣ ስደተኞችን ለድጋፍ አቅርቦት እጥረት በማጋለጡ ጉዳዩ አሳሳቢ ነው ተብሏል። ኢትዮጵያ በ2010 በተቀበለችው የተሟላ የስደተኞች ምላሽ ማዕቀፍ ፍኖተ ካርታ መሠረት የተገቡት ዘጠኙ ቃል ኪዳኖች በሚገባ ተግባራዊ አለመሆናቸውም ተጠቅሷል።
በተለይም ከአጠቃላዩ የስደተኞች ማኅበረሰብ መካከል ዐስር በመቶ ለሚሆኑት ከካምፕ ውጪ እንዲኖሩ የማድረግ ዕቅድ ተግባራዊ እንዳልሆነ ነው የተገለጸው።
ኢትዮጵያ 850 ሺሕ የሚጠጉ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን በማስጠለል በአፍሪካ ስደተኞችን ከሚቀበሉ አገሮች አንዷ መሆኗ የታወቀ ሲሆን፣ ለስደተኞች በሚቀርቡ አገልግሎቶች ላይ ልዩ ልዩ ችግሮች ስለመኖራቸው ተመላክቷል።
ቅጽ 4 ቁጥር 193 ሀምሌ 9 2014



