በደመወዝ ጭማሬ አናሳ መሆንና ሌሎች መፍትሄ ባላገኙ ተደራራቢ ችግሮች መበራከት ምክንያት ሥራ እስከማቆም የሚደርስ አድማ ለማድረግ በምክክር ላይ መሆናቸውን መምህራን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
በቁጥር በርከት ያሉና ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ መምህራን ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ከሆነ፤ ለትምህርት ሚኒስቴር እና ለኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም በዋነኝነት የደመወዝ ጉዳይ፤ የቤት ኪራይ አበል እንዲሁም በደረጃ እድገት ማስተካከያ ባለማግኘታቸው በሥራቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ተፈጥሯል። ይህን ተከትሎም ሥራ ለማቆም እንደሚገደዱ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ቅሬታው የሚቀርበው በሁሉም የትምህርት ተቋማት ደረጃ በሚገኙ መምህራን ሲሆን፤ ሰሞኑን በተደረገው 750 ብር የደመወዝ ጭማሬ በመነሳት ግን የዩኒቨርሲቲ መምህራን ጉዳዩን ይበልጥ አንገብጋቢ ነው ሲሉ ገልጸውታል።
በዩኒቨርሲቲ መምህራኑ ላይ በመጀመሪያ ደረጃ ቅሬታ ያስነሳው ጉዳይ የደመወዝ ጭማሬ እንዲደረግላቸው ሲጠይቁ ቆይተው የተጨመረላቸው 750 ብር ብቻ በመሆኑ የኑሮ ውድነቱን መቋቋም አለመቻላቸው ነው።
የኑሮ ውድነት በሁሉም ማኅበረሰብ በኩል ፈታኝ መሆኑን ያነሱት መምህራኑ፤ እንደ መምህር የበኩላቸውን ቅሬታ ሲያስቀምጡ፤ “ደመወዝ እንዲጨመር እሺታን አግኝተን እየጠበቅን ከቆየን በኋላ፣ የአንድ አስፔዛ ዋጋ ሰማይ በጠቀሰበት ወቅት 750 ብር መጨመር የንቀትም ጭምር ነው” ብለዋል። መንግሥት የመምህራን ደመወዝን በተመለከተ ጥናት አደርጋለሁ ብሎ የአስፔዛ ዋጋ በሳምንት ሦስትና አራት ጊዜ በሚንርበት ወቅት 750 ብር ብቻ መጨመር ፌዝ ነው ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
የንቀት ሥራ ተደጋግሞብናል ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ደመወዝ እንዲጨመርላቸው ጥያቄ ሲያቀርቡ ቆይተው 400 ብር ብቻ እንደተጨመረላቸው አስታውሰዋል። አሁንም በድጋሚ ተቀልዶብናል ነው ያሉት። የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ከዚህ በፊት በነበረው “አነስተኛ የ400 ብር ጭማሪ” እንደማኅበር ቅሬታ ማንሳት ሲገባው ዝም ብሎ መቅረቱን የጠቀሱት መምህራኑ፤ አሁንም በድጋሚ ሲቀለድብን ምላሽ አልሰጠንም ብለዋል።
በመሆኑም፤ “ማኅበሩ በደመወዝ ወደሚጨቁነው መንግሥት እያጋደለ ነው” የሚሉ ትችቶም በቅሬታ አቅራቢ መምህራኑ ተሰንዝረዋል።
መምህራኑ በኹለተኛ ደረጃ ያነሱት ቅሬታ ለቤት ኪራይ በሚከፈለው አበል ቤት መከራየት እንደማይቻል ነው። መንግሥት ለቤት ኪራይ ብሎ የሚከፍለን አበል 800 ብር ነው ያሉት መምህራኑ፤ ከዚህም ታክስ ሲቆረጥበት 520 ብር ይቀራል። በዚህስ ቤት ተከራቶ መኖር ይቻላልን? ሲሉ ጠይቀዋል።
“ይህን ድርጊት ከፌዝ ሌላ ምን ትርጓሜ ይሰጠዋል? እኛ አገራችን ያለችበትን ሁኔታ ተገንዝበን ዝም አልን እንጂ የሚከፈለን ደመወዝ እጅጉን አናሳ ነው። ሙሉ እድሜውን ትምህርት ላይ ያዋለ መምህር ሥራ ተቀጥሯል ተብሎ የሚቀይረው ልብስ አጥቶ ሀፍረት እስኪያሸማቅቀው ድረስ ከተማሪ ፊት እየቆመ ነው። ጦሙን ወደ ክፍል የሚገባ መምህርም አለ። በሚከፈለን ደመወዝ መተዳደር ካልተቻለ መሥራታችን ትርጉም ስለሌለው ሥራ እናቆማለን።” የሚል ሐሳብም አንስተዋል።
እስከ አሁን በኢትዮጵያ የሚስተዋለው ተደራራቢ ችግር አሳስቦን ዝም ብለን ብንቆይም አሁን ግን በሚከፈለን ደመወዝ ኑሮውን መቋቋም አልቻልንም። ሕዝብ ችግራችንን በይፋ ይወቅልን። መንግሥ ት አፋጣኝ መፍትሄ ይስጠን ሲሉ ተደምጠዋል።
የኹለተኛ እና አንደኛ ደረጃ መምህራን በበኩላቸው፣ “የሚሰጠን ደመወዝ አናሳ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ርዕሰ መምህራን ደመወዛችንን በሰበብ አስባቡ ይቆርጣሉ” ብለዋል።
የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዝዳንት ዮሐንስ በንቲ ለተነሳው ቅሬታ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም። ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑት “አይመቸኝም” ብለው ስልክ በመዝጋት ነው።
የደመወዝ ማነስ የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም ፈተና መሆኑን መምህራን ብቻ ሳይሆኑ በሌሎች የሥራ ዘርፍ የተሰማሩ ሰዎች ሁሉ ሲያማርሩና “የመንግሥት ሠራተኛ መሆን አያስፈልግም” ሲሉ ይደመጣል።
ቅጽ 4 ቁጥር 193 ሀምሌ 9 2014



It is good to expose the questions and burning issues of the time in Ethiopia to the largest media. However, the questions are not limited to the salary. More importantly, the house allowance and the research fund for the PhD students in Ethiopia is by far the ashaming one. How a third degree student, who is expected to bring a research finding for the policy change is given 60,000 ETB? How the government expect the quality and problem solving research findings and the competing researcher by providing the said birr which is even not sufficient to do pre-testing? This should be stressed or seeking for PhD should be stopped.
We have to take into action now