በዋግኸምራ ዞን 74 ሺሕ ሰዎች በተያዘው ክረምት ከመጠለያ ውጪ መሆናቸው ተገለጸ

1
1395

በዋግኸምራ ዞን ከሚገኙ 90 ሺሕ ተፈናቃዮች መካከል በክረምት ወቅት መጠለያ ውስጥ ያሉት ሩብ የማይሞሉ ተፈናቃዮች ብቻ መሆናቸውን የዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳዳር አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መምሪያ ገለጸ።

የምግብና የመጠለያ እጥረት በመከሰቱ 74 ሺሕ የሚሆኑ ተፈናቃዮች በክረምት ወቅት ከመጠለያ ውጭ መሆናቸውን የዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መምሪያ ኃላፊ ሰለሞን ንጉሥ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ኃላፊው በዋግኸምራ ዞን 90 ሺሕ ተፈናቃዮች እንዳሉ የጠቆሙ ሲሆን፤ መጠለያ ውስጥ ያሉት ከጠቅላላው ተፈናቃይ ሩብ የማይሞሉ ናቸው ብለዋል። ከ90 ሺሕ ተፈናቃዮች መካከል በመጠለያ ካምፕ ውስጥ ያሉት 16 ሺሕ ሰዎች ብቻ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የተፈናቃዮች ቁጥር ከነዋሪዎቹ በልጧል ያሉት ኃላፊው፣ በዝቋላ ወረዳ ውስጥ የነዋሪዎች ቁጥር 51 ሺሕ መሆኑን ጠቅሰው፤ 66 ሺሕ ተፈናቃዮች ግን በዚሁ ወረዳ ነው ያሉት ብለዋል። ቀሪዎቹ በፃግብጅ ወረዳ እና ሌሎች ስፍራዎች መሆናቸውም ተጠቅሷል።

ተፈናቃዮቹ ከኦሮሚያ ክልል (ወለጋ)፤ ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል፤ ከትግራይ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች እንዲሁም ከአበርገሌ፤ ከዛታ፤ ከኮረም፤ ከወፍላ፤ ከአላማጣ፤ ከዝቋላ እና ከሌሎች አካባቢዎች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ የተባሉ የሕወሓትና የኦነግ ሸኔ ቡድን በሚያደርሱት ጥቃት ቤታቸውን ትተው የሄዱ መሆናቸውን ሰለሞን አብራርተዋል።

የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ድጋፍ እያደረገ ቢሆንም፣ በቂ እንዳልሆነና በተለይም የምግብና የመጠለያ እጥረት በተፈናቃዮች ላይ ትልቅ ፈተና ስለመሆኑ ኃላፊው ተናግረዋል።

ምንም እንኳ የድጋፍ እርዳታው ቅድሚያ እናት አባት ለሞቱባቸው ሕጻናት፤ ለሚያጠቡ እናቶች፤ ነፍሰጡሮች፤ ለአዛውንቶች፤ በተለያየ ሕመም ምክንያት መድኃኒት ለሚጠቀሙ እንዲሁም ለአካል ጉዳተኞች ቢሆንም ማዳረስ እንዳልተቻለ ኃላፊው ጠቁመዋል።

ከተፈናቃዮቹ መካከል 7 ሺሕ 165 የሚያጠቡ እናቶች፤ 2 ሺሕ 821 ነፍሰጡሮች፤ 2 ሺሕ 375 ወንድና 1 ሺሕ 715 ሴት በጠቅላላ 4 ሺሕ 90 አረጋውያን፤ 829 ወንድና 576 ሴት በጠቅላላው 1 ሺሕ 405 አካል ጉዳተኞች፤ 1 ሺሕ 213 ወንድና  870 ሴት በጠቅላላ 2 ሺሕ 83 አንዱን ወላጅ ያጡ ሕጻናት፤ 284 ወንድና 214 ሴት ጠቅላላ 498 ሕፃናት፤ 705 ወንድና 610 ሴት በድምሩ 1 ሺሕ 315 ከቤተሰብ የተለዩ ሕፃናት እንዲሁም 150 ወንድና 124 ሴት በድምሩ 274 የሚሆኑ ሰዎች የረጅም ጊዜ ሕመም ያለባቸው መሆናቸውን ሰለሞን በዝርዝር ተናግረዋል።

ከ16 ሺሕ ውጭ ያሉት 74 ሺሕ ሰዎች በእጥረት ምክንያት ከመጠለያ ካምፕ ውጭ ለመኖር ከተገደዱት መካከል ከፊሎቹ በዝናብ እየበሰበሱ በረንዳ አዳሪ፤ ከፊሎቹ  ከዘመድ ቤት ተጠግተው የሚኖሩ እንዲሁም ቀሪዎቹ ደግሞ ቤት ተከራይተው የሚኖሩ ናቸው ተብሏል።

ወቅቱ ክረምት መሆኑን ያነሱት ኃላፊው በክረምት ወቅት ደግሞ ከቤት ውጪ ይቅርና ከቤት ውስጥ ተሆኖም ድባቡ እንደማይመች ይታወቃል ብለው፤ ምንም እንኳ 70 በመቶ የሚሆነው እርዳታ የሚሸፈነው በክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ቢሆንም አሁንም እጥረቱ ስለበረታ ሁሉም ሰው የተለመደ ድጋፉን ሳይነፍግ ርብርብ እንዲያደርግ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በሌላ በኩል፣ በዝቋላ ወረዳ ቀዳሚት አካባቢ ሕወሓት ሰሞኑን ዳግም ጥቃት ሰንዝሮ በሚሊሻዎች ርብርብ ወደኋላ እንደተመለሰ እና በዞኑ ስር በሚገኙ ፃግብጅ ወረዳ አጥቃት፤ ሰላምጌ፤ ድንቃይ፤ ጭራ፤ ድቁ የተሰኙ ስፍራዎች እንዲሁም አበርገሌ ወረዳን ሙሉ ለሙሉ አሁንም በታጣቂ ቡድኑ ቁጥጥር መሆናቸውንና በስጋት ቀጠና ውስጥ ስለሆኑ የእርሻ ሥራ ማካሄድ እንዳልተቻለ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳ ከዚህ በፊት፣ በዋግኸምራ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ተከስቶ በነበረ ድርቅና በጦርነቱ ምክንያት እርሻ አለመታረሱን ተከትሎ ርሃብ ተከስቶ እንደነበር መዘገቧ የሚታወስ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 193 ሀምሌ 9 2014

አስተያየት

  1. Please focus on security issues of Oromia Special Zone, North Showa, Wag Hemera.
    In addition, it should be timely and reliable.
    You are working good

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here