ባለፈው ሳምንት ጊቤ የተባለቸው መርከብ የኬንያን ጭነት ከኦማን ሱሐር ወደብ በመጫን ሞምባሳ ወደብ ገብታ በማራገፍ ላይ ትገኛለች ሲል የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት አሰታወቀ።
ከ23 ዓመታት በፊት አድማስ የተባለችው መርከብ ወደ ሞምባሳ ካደረገችው የመጨረሻ ጉዞ በኋላ የጊቤ መርከብ በሞምባሳ መገኘት ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የአፍሪካ አገራትን በንግድ የማስተሳሰር ሥራን በ2010 መጨረሻ የኤርትራን ጭነት ከምጽዋ ወደብ ወደ ቻይና በማጓጓዝ አሐዱ ብሎ የጀመረውን አገልግሎት በማስቀጠል ካለፈው ዓመት ጀምሮ በሶማሌ ላንድ በበርበራ፣ በግብጽ በሳፋጋ እና ፖርት ሳይድ ወደቦች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አመላክቷል።
በዚህም ድርጅቱ አፍሪካን ከሌላ አኅጉር በንግድ የሚያገናኝ የመጀመሪያውና ብቸኛው አፍሪካዊ የመርከብ ኩባንያ በመሆን የቀጠለ ሲሆን፣ የአገሪቱን የገቢ ወጪ ጭነት ከማጓጓዝ በተጨማሪ በቀጠናው ላሉ አገራት አገልግሎት በመስጠት ተደራሽነቱን እያሰፉ ተጨማሪ ገቢ እያስገኘ መሆኑ ተጠቅሷል።
ድርጅቱ በባሕር ትራንስፖርት አገልግሎት ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በተሻገረ ጉዞው በዘርፉ ያለውን ከፍተኛ ውድድር በጥንካሬ በመወጣት አገሪቱ ለዘርፉ በሰጠችው ትኩረትና ድጋፍ ከአፍሪካ ብቸኛው የአገርን ሠንደቅ ዓላማ በባሕር ላይ የሚያውለበልብ ሆኖ በመቀጠል የአገሪቱ ኩራት ሆኗል ነው የተባለው።
ቅጽ 4 ቁጥር 194 ሐምሌ 16 2014


