ለጅቡቲና ሱዳን ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ከ95 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

0
983

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለጅቡቲና ሱዳን ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ከ95 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኤሌክትሪክ ሽያጭ ለአገር ውስጥና ለውጭ አገራት ደንበኞች በጅምላ የሚያቀርብ ሲሆን፣ በተጠናቀቀው የ2014 በጀት ዓመትም ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ለከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች እንዲሁም ለሱዳንና ጅቡቲ ኃይል በሽያጭ በማቅረብ ገቢ መሰብሰብ እንደቻለ ተመላክቷል።

በዚህም ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት 9 ሺሕ 472 ጊጋ ዋት ያቀረበው ተቋሙ፣ ለከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች የእቅዱን 90 በመቶ እንዲሁም ለኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር የእቅዱን 116 በመቶ ኃይል ማቅረብ መቻሉን ነው ለማወቅ የተቻለው።

ተቋሙ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለጅቡቲ 527 ጊጋ ዋት ኃይል ለማቅረብ አቅዶ 611 ጊጋ ዋት ማቅረብ መቻሉ ተጠቅሷል።

ለሱዳን ደግሞ 1 ሺሕ 93 ጊጋ ዋት በሰዓት ያቀረበ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ተቋሙ በበጀት ዓመቱ ለአገር ውስጥና ለውጭ አገራት 12 ሺሕ 30 ጊጋ ዋት ኃይል ማቅረቡ ተገልጿል።

ተቋሙ ለጅቡቲና ሱዳን ካቀረበው የኃይል ሽያጭ ያገኘው 95 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ፣ ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀርም የ4 ነጥብ 9 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወይም የ5 ነጥብ 4 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ነው የተገለጸው።

ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ካቀረበው ኃይል 11 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ከኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ደግሞ 364 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉም ተመላክቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 194 ሐምሌ 16 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here