ክብር ለእናቶች!

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ከሰሞኑ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ከአትሌቶች ድል በተጓዳኝ የእናቱን ሸክም ተሸክሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ዋና በር ላይ ፎቶ ስለተነሳ አንድ ተመራቂ ወጣት በብዛት ሲነጋገሩ ነበር። በጉዳዩ ላይ የተነሳው ሌላው ዝርዝር ሐተታና ውዝግብ ይቆየንና፤ የእናትን ሸክም በመሸከም ውስጥ ስንት ዐይን እና ትኩረት እንደሚገኝ ልብ በሉልኝ።

ለውጥን ለማምጣት አካሄድ ወሳኝ መሆኑ እሙን ነው። አካሄድም ደግሞ በብልሀት ሊገራ ይገባል። እንዲህ ነው እንዲያ ነው ብሎ ከመናገር ይልቅም በተግባር ማሳየት ምን ያህል ተጽእኖ መፍጠር እንደሚችል በዚህ ማወቅ ይቻላል። ያም ብቻ አይደለም፤ በአደባባይ ወጥተን ስንናገር ‹ይህ መሆን አለበት! እንዲህ ቢሆን ይሻላል!› የምንለውንና የምንጠይቀውን፤ እንዲከበር የምንለውን ሕግና ስርዓት ሳይቀር በቅድሚያ እኛው ራሳችን ልናከብረው ይገባል። ይህም ለውጥን ለማምጣት ካለው አካሄድ መካከል አንደኛው ነው።

ታድያ ይህን ኹነት ስመለከት የገባኝ አንድ ነገር፤ ይህንና ያንን አድርጉ አታድርጉ ከማለት በላይ በተግባር አንዳች ነገር ማሳየት ምን ያህል ተጽእኖ ፈጣሪ እንደሚሆንና ተገቢም እንደሆነ ነው።

እዚህ ላይ፤ ለሴቶች የሚሞግቱ ሰዎች ራሳቸው ለሴቶች ምን ያህል ክብር ይሰጣሉ የሚለው ሁሌ ጥያቄ የሚፈጥርብኝ ጉዳይ ነው። ይህን ሐሳቤን በጥሩ ሁኔታ የሚገልጽልኝን አንድ ገጠመኝ ላውሳ፤ ይህም በሥም የማላስታውሳት አንዲት ብዕረኛ በማኅበራዊ ገጿ ጽፋ ያስነበበችው ነው።

እንዲህ ነው፤ አንዲት የሴቶች መብት ጉዳዬ ነው ብሎ የሚሠራ ተቋም ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት የምትሠራ ሴት ናት። በተቋሙ ባላት ድርሻ በተለይም ሴቶች ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱና ትምህርት በያሉበት ተደራሽ እንዲሆን ለማድረግ ከፍተኛውን ኃለፊነት ወስዳ ትሠራለች። ያለእድሜ ጋብቻ፣ የጉልበት ብዝበዛና የቤተሰብ የግንዛቤ እጥረት ሴቶችን ከትምህርት ገበታቸው እንዳያስቀር ስትል፤ በየሚድያው ቀርባም ‹ትምህርት ለሴቶች› እያለች ስለፍትህ ትጠይቃለች፤ ታሳውቃለች።

እናም አንድ ቀን ይህች ሴት ወደ ብዕረኛ ጓደኛዋ ትደውላለች። ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላም ቤቷ ውስጥ ምን ያህል ሥራ እንደበዛባትና እንደተቸገረች ትነግራታለች። ቀጥላም ‹‹ቤት ውስጥ በሥራ የምታግዘኝና ቢያንስ ቀን ልጆቼን የምትጠብቅልኝ አንዲት ትንሽ ልጅ ባገኝ ደስ ይለኛል። እባክሽን ለሚያውቁ ሰዎች ብትነግሪልኝ›› ትላታለች። ይህ ጥያቄዋ ባልከፋ፤ ቀጥላም ይህን አለች ‹‹ግን የምትማር እንዳትሆን አደራ!››

ይህቺ ሴት ታድያ ሴቶች ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ የምታደርገው ትግል ምን የሚሉት ነው? ምን ያህልስ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል? ለውጥ የሚመጣው ከንግግር ያለፈ ተግባር ሲኖር ነውና እርምጃና አካሄድን ማጤን ተገቢ ነው ለማለት ነው።

መቅደስ ቹቹ


ቅጽ 4 ቁጥር 194 ሐምሌ 16 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች