የኩላሊት ንቅለ ተከላ መቋረጡ ሕሙማኑን ላልተፈለገ ወጪ ዳርጓል ተባለ

0
1648

የኩላሊት ንቅለ ተከላ አገልግሎት በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት መቋረጡና እስካሁን አለመጀመሩን ተከትሎ በርካታ ሕሙማን ላልተፈለገ ወጪ መዳረጋቸውን የኩላሊት በጎ አድራጎት ድርጅት ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

አገልግሎቱ ለዓመታት በመቋረጡና እስከ አሁን ድረስ በመጓተቱ ንቅለ ተከላውን የሚጠባበቁ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ በርካታ ሕሙማን በኩላሊት እጥበት (ዲያሌሲስ) ሕክምና ለከፍተኛ ወጪ መዳረጋቸውን የኩላሊት ሕሙማን በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰለሞን አሰፋ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የተቋረጠውን አገልግሎት የሚጠባበቁ በርካታ የኩላሊት ሕሙማን መኖራቸውን የጠቀሱት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ ንቅለ ተከላው በመቋረጡ ሕሙማኑ ለኩላሊት እጥበት በየሳምንቱ ከፍተኛ ወጪ ለማውጣት ተገደዋል ብለዋል።

ወደ ውጪ አገር ሄዶ የንቅለ ተከላ አገልግሎቱን ለማግኘት እስከ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር እንደሚጠይቅ የጠቀሱት ሰለሞን፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ ሕሙማን ደግሞ ወጪውን ለመሸፈን አቅም እንደማይኖራቸው እሙን ነው ይላሉ። ዋና ሥራ አስኪያጁ የንቅለ ተከላ አገልግሎቱ በተጀመረበት ወቅት ሕሙማኑ፤ የሕሙማኑ ቤተሰቦች እንዲሁም ሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከጭንቀት ተገላግለው እንደነበር አስታውሰው፤ በኮቪድ ምክንያት መቋረጡ ግን ፈታኝ እንደሆነ አብራርተዋል።

በተያያዘም፤ የኮቪድ ወረርሽኝ ትንሽ ጋብ ሲል እንኳ አገልግሎቱ ሊጀመር አልቻለም ብለዋል። የኮቪድ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ የተከሰተው መጋቢት ወር 2012 ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ባለሙያዎች በኩል ሲሰጥ የቆየው የኩላሊት ንቅለ ተከላው በወረርሺኙ ምክንያት ከኹለት ዓመት በላይ መጓተቱን ነው ሰለሞን ለአዲስ ማለዳ ያሳወቁት። የኮቪድ ወረርሽኝ ተፈልጎ የመጣ ባይሆንም፤ ንቅለ ተከላ አገልግሎቱ አሁን መጀመር ነበረበት ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን፤ ጤና ሚኒስቴር ጉዳዩ በሂደት ላይ ነው በሚል እያጓተተው መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም፣ ከኹለት ዓመት በላይ ዲያሌሲስ እንዲያደርጉ የተገደዱ የኩላሊት ሕሙማን የግል ተቋማት እርስ በርሳቸው በመወዳዳር የዋጋ ጭማሪ እያደረጉባቸው መሆኑን ነው ሰለሞን የተናገሩት። በግል ለአንድ የኩላሊት እጥበት ከሦስት ሺሕ ብር በላይ የሚጠየቅ ሲሆን፤ በሳምንት ሦስት ጊዜ እጥበት ማድረግ ያለበት ሰው ዘጠኝ ሺሕ ብር ያስፈልገዋል ተብሏል። የተቋረጠው ንቅለ ተከላ ቢጀመር ግን ወጪውም ሕመሙም ሊቀንስ ይችላል የሚል ሐሳብ ተሰንዝሯል።

በሌላ በኩል፣ የጤና ሚኒስቴር ለንቅለ ተከላ አገልግሎት የሚውሉ 100 ማሽኖችን እንደሚገዛ ከዚህ በፊት ቃል መግባቱን ሰለሞን ለአዲስ ማለዳ ገልጸው፤ እስከ አሁን ግን አልተገዛም ነው ያሉት። 100 ማሽኖች የበርካታ ሕሙማንን ሕመም የመቅረፍ እምቅ አቅም እንዳለው እየታወቀ፤ ማሽኑ ይገዛል ከተባለ ግን ከአንድ ዓመት በላይ ማስቆጠሩን ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

ይገዛል ተብሎ የነበረውን 100 ማሽን በተመለከተም ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብም፣ በሂደት ላይ ነው ከማለት የዘለለ ምላሽ እንዳልተገኘ ነው የተገለጸው። የኩላሊት ሕሙማን በበኩላቸው፣ የተቋረጠው ንቅለ ተከላ ካልተጀመረላቸው ከዚህ በኋላ የኩላሊት እጥበት የማድርግ አቅማቸው እየተዳከመ መሆኑን ይገልጻሉ።

እስከ አሁን እርዳታ የሚያደርጉልን ተቋማትና ድርጅቶች እንዲሁም ቅኑን ማኅበረሰብ ያመሰገኑት ሕሙማኑ የተለመደው ትብብር እንዳይለያቸው ጠይቀዋል። ሕሙማኑ በተያያዘ በሥማቸው ተመሳስለው እየለመኑ ብር የሚሰበሰቡ በርካታ አጭበርባሪ ሰዎች እንዳሉም ጠቅሰው ድርጊቱ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል። አዲስ ማለዳ የተነሳውን ቅሬታ ይዛ ምላሽ ለማግኘት የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ለማግኘት ያደረገችው ሙከራ ስልክ ለማንሳት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ሳይሳካ ቀርቷል።

በኢትዮጵያ በመንግሥት ተቋማት ደረጃ የኩላሊት ንቅለ ተከላ የተጀመረው በ2010 ሲሆን፤ ከኹለት ዓመት ወዲህ ደግሞ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት አገልግሎቱ ተቋርጧል። በሌላ በኩል፣ ‹ሊያና ሄልዝ ኬር› ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የኩላሊት ንቅለ ተከላ በግል ተቋም ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ በ2015 ሊጀምር መሆኑን ከዚህ በፊት ለአዲስ ማለዳ መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፤ ሕሙማኑም በተስፋ እየጠበቁ መሆኑን ገልጸዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 195 ሐምሌ 23 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here