መነሻ ገጽሐተታ ዘ ማለዳያልታደሉት የአዲስ አበባ ቅርሶች

ያልታደሉት የአዲስ አበባ ቅርሶች

ከሦስት ዓመት ገደማ በፊት አንድ ጥንታዊ የሆነ የአንድ አርበኛ ቤት መፍረሱን ተከትሎ፤ አፍራሹ ቅርስ መሆኑን አላውቅም ነበር አለ። ነገሩ በጊዜው ውዝግብና ክርክርን አስነስቶ በኋላ ላይ ጭራሽ ተዘነጋ። ይህም በግልጽ ቅርስ የሆኑ ግንባታዎችን ከማፍረስ የጀመረ ተግባር ቀጥሎ፣ የቅርስ ያህል ዋጋ ያላቸውና የሕዝብ የጋራ ትዝታ የተሸከሙ ግንባታዎችም እንደቀላል እየፈረሱ ይገኛሉ።

ይህም ሕንጻዎቹንና ቦታውን በገዙት በግል ባለሀብቶች የተፈጸመ ነው ቢባልም፤ የፌዴራል መንግሥት ይልቁንም የከተማ አስተዳደሩ ከተጠያቂነት የሚድኑበት እንዳይደለ እሙን ነው። የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ኢትዮጵያ ሆቴል አጠገብ የሚገኘው የበጎ አድራጎት ሕንጻ/ራይቲዮር ሕንጻ መፍረሱን መነሻ በማድረግ፤ የአዲስ አበባ ቅርሶችን ነገር የተለያዩ ባለሞያዎችን በማነጋገርና መዛግብትን በማጣቀስ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጋዋለች።

በአዲስ አበባ በእድሜ ገፋ ያሉ ሕንጻዎች ሊፈርሱ ነው የሚሉ ዜናዎች ሄድ መለስ የማለታቸው ነገር እየተለመደ ነው። በየቀኑ ሕንጻ ይበቅልባታል እስኪባል ድረስ በአዳዲስ ሕንጻዎች ግንባታ ተጠለቅልቃ የነበረችው አዲስ አበባ፣ አሁን ደግሞ በየጊዜው ጥንታዊ የሆኑ ሕንጻዎቿ በአፍራሽ መዶሻ ፈርሰው የሚሰወሩባት ሆናለች። ነዋሪዎቿም አሁን ድረስ በስስት የሚያይዋቸው፤ ትዝታን የተሸከሙላቸውና ‹ይህንንም ያፈርሱት ይሆን!› እያሉ የሚሰጉላቸው ሕንጻዎች በብዛት አሉ።

በቅርቡ ብሔራዊ ቴአትር አካባቢ ኢትዮጵያ ሆቴል አጠገብ የሚገኘው የበጎ አድራጎት ሕንጻ ወይም በሌላ አጠራር ‹ራይቲዮሪ› ሕንጻ የወትሮ ግርግርና ጫጫታው ጠፍቶ ጭርታ ነግሦበት ነበር። ሊፈርስ ነው አይፈርስም የሚል ውዝግብ ከወራት በፊት በተለያየ ማኅበራዊ ድረገጽ ሲዘዋወር መቆየቱ አይዘነጋም። ነገር ግን መረጃው ሐሰት ነው የሚል ዜና ተሰራጨ። ነገሩ ሳይከርም የተገላቢጦሽ ሆኖ፤ አሁን ላይ ግን ሕንጻው እየፈረሰ መሆኑን አዲስ ማለዳ መታዘብ ችላለች።

በዚህም ዙሪያ የተለያዩ የከተማዋ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን እና ሐዘናቸውን በመከፋትና ‹ቀጥሎ ደግሞ የትኛው ይሆን ፈራሽ?› በሚል ስጋትና ጥርጣሬ፤ አቅም በማጣት መንፈስ ሲያጋሩ ተስተውሏል። የልማት ገጽ እነዚህን ሕንጻዎች ለምን መግፋት አስፈለገው? ባሲሊየል ተዋበ መሀንዲስ ናቸው። በግንባታ ዘርፍ ለዓመታት ያገለገሉ ሲሆን አሁን ከሰባት በላይ ሳይቶች ላይ ይሠራሉ።

ከሰሞኑ ነው ‹ግንባታ› የተሰኘ በግንባታ ዘርፍ ላይ ለሚገኙ ሙያተኞች ልምድ ከመጨመርና አቅጣጫ ከመስጠት አንጻር ዋጋ እንዲጨምር የሚጠበቅ መጽሐፍ ለአንባብያን ያደረሱት። የእርሳቸውን ሙያዊ ዕይታ ጠይቀናል። ሐሳባቸውን ሲያካፍሉም ታሪካዊ ግንባታዎችና አካባቢዎች ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።

እንደ ሕንጻ ባለሞያም እንዲያ ያለ ዋጋ ያላቸውን ቦታዎች የመጠበቅ ግዳጅ እንዳለ ጠቅሰዋል። በጣም ግድ ካልሆነ በቀር ታሪካዊ ቅርሶች ባሉባቸው አካባቢዎችም ሌላ ግንባታ ማካሄድም እንደማይመከር ነው የጠቀሱት። በአደጉ አገራት እንዲህ ያለ ነገር ሲፈጠርና ቅርሶች ያረፉበት ቦታ አማራጭ በሌለው ሁኔታ ተፈላጊ ሲሆን፣ አማራጭ ቴክኖሎጂዎች እንዳሉ ነው ያነሱት።

አንደኛው አሁን ላይ በቻይና የሚታየው ሕንጻዎች ሳይፈርሱ ነቅሎ ቦታ መቀየር ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በስሪ ዳይሜንሽ (3D) አንስቶ፣ ለታሪክና ለትውልድ በዛ መልክ አቆይቶ ማፍረስ ነው። በእነዚህ አማራጮች ታሪካዊና ጥንታዊ ሕንጻዎች ቢነሱ እንኳ ጉድለቱን መሙላት ይቻል ነበር ብለዋል።

የሆነው ሆኖ ግን፤ በአዲስ አበባ ያሉ ሕንጻ ግንባታዎች ከጥንት ጀምሮ እስከ አሁን የከተማዋን የኪነ ሕንጻ እድገትና ለውጥ የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል። ምንም እንኳ ከውጪ አገራት በቀጥታ የመጡ የሚመስሉ የግንባታ መልኮች ቢኖሩም፣ የአገር ሰው ሐሳብና ፍላጎት ሲታከልበት ኢትዮጵያዊ እንደሚሆን ገልጸዋል። በዚህም በከተማዋ የሚገኙ ታሪካዊና ጥንታዊ ሕንጻዎችም አንድ የታሪክ ገጽ መሆናቸውን አንባቢ ይረዳል።

ቅርስ በከተማ
አቤል አሰፋ የቅርስ ኮንሰርቬተርና አርኪዮሎጂ ባለሙያ ናቸው። በአዲስ አበባ ቅርሶች ዙሪያም ጥናት ያደረጉ ሲሆን፣ እንደ አዲስ አበባ ልጅና ነዋሪ የከተማዋ የቅርስ ጉዳይ በእጅጉ ያሳስባቸዋል፤ ያሳሳቸዋልም። እንደ እርሳቸው ሙያዊ ገለጻ፤ በከተሞች የማኅበረሰብ እሴትነት ያላቸው ቅርሶች ትልቅ ዋጋ አላቸው።

በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ለትዝታ ልዩ ቦታ የሚሰጥ ማኅበረሰብ ሲሆን፣ ማኅበራዊ እሴትነት ያላቸው ቅርሶች ዋጋቸው ይጨምራል። አዲስ አበባም የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም መዲና፣ ምሥረታዋ ከአደዋ ድል ማግስት የሆነ በቅኝ ያልተገዛች ከተማ ከመሆኗ አንጻር በርካታ ታሪካዊ ቤቶችና ቅርሶች አሏት። ችግሩ ግን ቅርሶቹ እነማን ናቸው የሚለው ተብራርቶ አለመቀመጡ ነው ይላሉ።

በዛም የተነሳ ቅርስ ምዝገባ ላይ ችግሮች ይታያሉ።‹‹ትልቁ ችግር እየተፈጠረ ያለው የአዲስ አበባ ቅርስ ስንል የትኛው ነው? በምን መስፈርት ሊመዘን ይችላል? የሚለው አጨቃጫቂ መሆኑ ነው። በዛ ምክንያት ቅርሶቹ ደረጃ አልወጣላቸውም። እናም አልተዘመገቡም የሚለው ጉዳይ ለአንዳንድ ቅርሶች መውደም እንደ ምክንያት ይጠቀሳል።

እንደምናየው ደግሞ አንዳንዴ ቅርሱ የተመዘገበ ቢሆንም፣በጣልያን ጊዜ የተሠራ ነው ወይም የእገሌ ቤት በሚል ምክንያት ሌላ ጉዳይ መለጠፍ አለ።›› ሲሉ አስረድተዋል። ይህም ሁሉ ሆኖ ግን ሁሉም የሚፈርስ ቤት ደግሞ ቅርስ እንዳይደለ ሳይጠቁሙ አላለፉም። በአዲስ አበባ አምስት ጊዜ በተካሄደ የቅርስ ምዝገባ፤ ቅርስ ሆነው ለመመዝገብ ስላልበቁ ያልተመዘገቡ ቤቶች ቅርሶች ናቸው የሚል ጭቅጭቅ ይነሳ እንደነበርም አስታውሰዋል።

ኹለቱ ጉዳዮች አለመጣጣማቸውም ፈታኝ እንደሆነ አንስተዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ቅርሶች እንደ ቅርስ መመዝገብ የጀመሩት በ1982 ነው።እነዚህ ቅርሶች ትኩረት ውስጥ ገብተው በብዛትም አደጋ ላይ የወደቁት ከመልሶ ማልማት፣ ከመሬት ዋጋ ንረትና ለቅርስ ከተነፈገው ትኩረት አንጻር እንደሆነ ይታመናል።

በአዲስ አበባ በአሁኑ ሰዓት ተመዝግበው አሉ ከሚባሉ 400 በላይ ከሚሆኑ ቅርሶች ውስጥ በግለሰብ ይዞታ ስር ያሉት በቁጥር 72 ገደማ ናቸው። አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም በሠራቻቸው ዘገባዎች ላይ በተሰጡ አስተያየቶች፤ ከእነዚህ ብዙዎች የግል ባለይዞታዎች በውርስ የተቀበሉትንና በግል ይዞታቸው ስር ያሉትን ቅርሶች ለማስተላለፍ ፈቃደኛ አይሆኑም።

በተጓዳኝ አዲስ አበባ ላይ የቅርስ ቤት መያዝ ዕዳ ነው የሚል ዕይታ ያለ ሲሆን፣ ባለይዞታዎች በገንዘብ ተጠቃሚ ካለመሆናቸው በላይ በቅርሱ ኩራት የሚሰማቸው አይደሉም። በአዲስ አበባ ያሉ ታሪካዊ ሕንጻዎች እና ግንባታዎች ለአዲስ አበባ የከተማ ልማት ያላቸውን አስተዋጽኦ በሚመለከት በሰላም ተወልደብርሃን የተሠራ አንድ ጥናት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥናት ካታሎግ ውስጥ አገኘን። በዚህም ላይ አጥኚዋ እንዳስቀመጡት፣ ታሪካዊ ሕንጻዎች ለከተማ ልማት ትልቅ ድርሻ አላቸው።

- ይከተሉን -Social Media

ይህም የከተሞችን የኖረ የድሮ መልክ በማሳየት ለውጦችን እንደ መጽሐፍ ለማንበብ የሚያስችሉ ሲሆን፣ በተጓዳኝ ትውልድ የነበረውንና የቀጠለውን ለውጥ ከአካባቢው ዐይቶ ወደፊት እንዲራመድ ያግዛሉ የሚል ነው። በሌላ በኩል ከጎብኚዎች የቱሪዝም ገቢን ሲያስገኝ፣ ከዛም ሲልቅ የኪነሕንጻው ውበት ዋጋ አለው።

በዚህ ጥናት ከተካተቱ በአዲስ አበባ የሚገኙ 34 ቅርሶች ውስጥ አብዛኞቹ በግንዛቤ፣ በአቅምና ትኩረት እጥረት የተነሳ በአግባቡ የተያዙ እንዳልነበሩ ተጠቅሷል። ከዛም ውጪ ማንም ሰው ጥገና ለማድረግና ለመንከባከብ ጥረት እንዳላደረገ በጥናቱ ተጠቅሷል። የገንዘብ ድጋፍም ከሚመለከተው አካል ያገኘ የግል የቅርስ ባለይዞታ የለም።

ከዛም አልፎ በግል ይዞታ ስር ያሉ ቅርሶችን የሚከታተሉ ክፍለ ከተሞች ለተረከቡት ሰዎች ምንም ዓይነት ግንዛቤ አይሰጡም/አልሰጡም። እናም ምንም እንኳ ጥንታዊ የሆኑ ግንባታዎች ለአዲስ ከተማ ግንባታ ትልቅ ግብዓት መሆን የሚችሉና የሚያግዙ መሆኑ እሙን ቢሆንም፣ በእነዚህና በብዙ ምክንያቶች ግን በአዲስ አበባ የሚገኙ እነዚህ ቅርሶች የሚገባቸውን ያህል አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ እድሉ አልተሰጣቸውም።

ምን ታዘብን?
ቅርሶች ዋጋ የሚኖራቸው ማኅበረሰብ በሚሰጣቸው ዋጋ ነው። ስለዚህም ሚዛኑ ቅርስ ተብለው መመዝገባቸው ብቻ አይደለም።ደግሞ በግልጽ እንደሚታየው ቅርስ ተብለው መመዝገባቸው ከጥፋት አላዳናቸውም። መለስ ብለን ስናወሳ፤ ከሦስት ዓመት ገደማ በፊት በአዲስ አበባ ገነተ ኢየሱስ ቤተክርስትያን ከፍ ብሎ ‹የራስ ካሳ ሰፈር› ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የፈረሰው የደጃዝማች አበራ ካሣ ቤትን እናገኛለን።

ቤቱን ያፈረሰው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ‹ቤቱ በቅርስነት ስለመመዝገቡ ምንም ዓይነት መረጃ የለኝም› የሚል ምላሽ መስጠቱም የሚታወስ ነው። ልክ እንደዛው ሁሉ አሁንም እየፈረሰ ያለውና ኢትዮጵያ ሆቴል አጠገብ የሚገኘው የበጎ አድራት ሕንጻ በቅርስነት የተመዘገበ ነው። ሕንጻው በጣልያን ጊዜ የተሠራ ሲሆን፣ የበጎ አድራጎት ሕንጻ የተባለው ጣልያኖች ኢትዮጵያን ወርረው በቆዩበት አምስት ዓመታት ከሠሩት ግፍ አንጻር እንደ ካሳ እና የእርቅ አካል ተደርጎ የሚታሰብ በመሆኑ ነው።

ከዛ ጋር ተያይዞ ሕንጻው ታሪካዊ ዋጋ አለው ያሉት አቤል፤ ከዛ በዘለለ የኪነ ሕንጻ እሴትነቱ ሲታይ፤ አዲስ አበባ እንደ ከተማ ያሳለፈችውን ታሪክ የሚያሳይ ነው ብለዋል። በተለይ ብሔራዊ ቴአትር አካባቢ ያሉ የተለያዩ ሕንጻዎች የከተማዋን እድገት የሚያሳዩ ናቸው፤ ይህም ሕንጻ አንዱ በመሆኑ እንደተመዘገበ ነው የጠቀሱት።

የታደሉ አገራት የማኅበረሰብን ትውስታ እና ታሪክ ለማቆየት ሲባል የማይነኩ፤ እድሳት ካስፈለጋቸውና መሠረተ ልሟት ሊሟላላቸው ከተገባም በጥንቃቄ የሚደረግላቸው አካባቢዎች/ ሰፈሮችና ከተማዎች እንዳሉ አቤል ይጠቅሳሉ። ቅርሶቹ ላይ አደጋ የሚጥል አካል ቢመጣም፣ ‹የለም አትነኩም!› ብለው የሚሞግቱ፣ ፖለቲካዊ ንክኪ የሌላቸው ሲቪል ሰዎች፣ በከተማ ምክር ቤት ሳይቀር ቦታ አግኝተው እንደሚሞግቱ ይናገራሉ።

‹‹እኚያ ሰዎች ኃላፊነታቸው ከማኅበረሰባዊ እሴት አንጻር ያሉ ጉዳዮችን በማንሳት በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ድልድይ መሆን ነው።እኛ ግን አልታደልንም፤ ይህ ነገር የለንም።›› ሱሉ አክለዋል። ሚድል ኢስት ኦንላይን የተባለ የዜና አውታር ‹Addis Ababa’s history bears the brunt of development› በሚል ርዕስ ባሰፈረው ጽሑፍ፣ አዲስ አበባን ወጣት ከተማ ሲል ይጠቅሳትና ግንባታዎቿ በመንግሥታት ለውጦች ውስጥ ታሪክ ተጽፎባቸው የሚገኙ ገጾች ናቸው ይላቸዋል።

- ይከተሉን -Social Media

ዘገባው ያብራራል፤ አፄ ምኒልክ አዲስ አበባን ሲገነቡ አርመናዊያን የከተማ መሀንዲሶችን ለግንባታ ያሰማሩ ነበር። ከሕንድ እና የመን በርካታ ነጋዴዎች እየመጡም በእነዚህ ቤቶች ይኖሩ ነበር። በኋላም የጣልያን ወረራ በርካታ የግንባታ አሻራዎችን አሳረፈ። በደርግ ዘመነ መንግሥትም በርካቶቹ ቤቶች ለነዋሪዎች ይታደሉ ነበር።

ቤቱ የተሰጣቸውም በኑሮ ደረጃ ዝቅ ያሉ ስለነበሩ ቤቶቹ የነበራቸውን መልክ ይዘው እንዲቆዩ የማድረግ አቅም አልነበራቸውም። በኋላ ደርግ ወድቆ ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲቀበል፣ የግንባታ ሥራዎች አብዛኛው በቻይና በኩል የሚከናወኑ ሆኑ። በዚህም ሂደት ውስጥ ታሪክና የርዕዮተ ዓለም ለውጦች በሕንጻዎች ላይ ተመዝግበው ይገኛሉ። ታድይ ይኸው ዘገባ የአርክቴክት ማኅደር ገብረመድኅን ዕይታን አካፍሏል።

ማኅደር እንዳሉት፤ በእድሜ የገፉ ሕንጻዎች ቸል እንዲባሉ የሆኑት ለማደስ ከሚፈልጉት ወጪ አንጻር ነው። ደግሞም ካለው የርዕዮተ ዓለም ለውጥ የተነሳ እነዛን ሕንጻዎች ይዞ የማቆየት ፍላጎት አልነበረም። ዘገባው ምንም እንኳ ታድሰው ሙዝየም ሆነው እያገለገሉ ያሉ ጥንታዊ ሕንጻዎች ቢኖሩም፤ በከተማዋ የተመዘገቡ ከ440 በላይ የሚሆኑ ቅርሶች ግን እየወደሙ መሆኑንና የከተማ አስተዳደሩም ይህን እንደሚያምን ጠቅሷል። እናድስ ለሚሉም ቢሮክራሲው የማያስቀርብና አስቸጋሪ እንደሆነ ያናገርኳቸው ሰዎች ነግረውኛል ብሎ አክሏል።

መዝጊያው ላይ ታድያ ‹‹በአዲስ አበባ ያሉ ቅርሶች ተክደዋል።›› ይላል፡፡ ከእነዚህ አስተያየቶች መረዳት እንደምንችለው፤ ጥንታዊ ግንባታዎች ለማደስ ውድ ናቸው። እንደ ከተማ አዲስ አበባ ላይ ብቻ ሳይሆን እንደ አገር ኢትዮጵያም የግል ባለይዞታዎችና ባለሀብቶች ቅርሶችን ባሉበት ጠብቀው እንዲያቆዩ ለማስቻል የሚያግዝና በሌሎች አገራት የተለመደው ልዩ ማበረታቻ የለም።

ላድስ ለሚሉም ሂደቱ ብዙና አሰልቺ ነው። ቅርስ መሆናቸው የተለየ ክብደት የሚሰጣቸው ሆኖ ሳለ፤ በድምሩ ጥንታዊ ሕንጻዎችን መጠበቅ ግን ምን ዋጋ አለው ስትል አዲስ ማለዳ ጠይቃለች። ሳሺ ኖቼራ የተባሉ ኪነሕንጻ ላይ የሚሠሩ ባለሞያ ባስነበቡት አንድ ጽሑፍ፣ ይህን ተመሳሳይ ጥያቄ አንስተዋል።

ሲመልሱም እንዲህ ይላሉ፤ ለታሪካቸውን ለትዝታቸው የሚሳሱ፣ አልፎም ቅርሶችን የቱሪዝም የገቢ ምንጭ አድርገው የሚንቀሳቀሱ አገራት በእድሜ የገፉ ሕንጻዎቻቸውን ይንከባከባሉ። ለዚህም ለአልሚዎች የግብር ማበረታቻና ሌሎች የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ፣ አንድን ጥንታዊ ሕንጻ አፍርሰው አዲስ በመገንባት ከሚያገኙት ጥቅም የተሻለውን እንዲያገኙ ያደርጋሉ ብለዋል።

አያይዘውም፣ እንዲህ ያሉ ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶችን መጠበቅና አቆይቶ መጠቀም ውድ መሆኑን ሳይጠቀሱ አልቀሩም። ‹‹ነባሩን አርፍሶ አዲስ ሕንጻ መሥራት የተሻለ አዋጭ ሆኖ ሊያዝ ይችላል። ነገር ግን፣ ለአጭርና ለረዥም ጊዜ ኢኮኖሚያው ጥቅም ታሪክን ታሳቢ አድርጎ ነገንም አሻግሮ ማየት አስፈላጊ ነው። ጥንታዊ ሕንጻዎችን ጠብቆና መልሶ ለጥቅም እንዲውሉ ማድረግ ቢዝነስን ከፍ ሊያደርግና የቱሪዝም መዳረሻና ማረፊያ መሆንንም ሊያግዝ ይችላል።›› ሲሉ ለሚኖሩባት ኒውዮርክ ከተማ ሰዎች መክረዋል። ይህ ለአዲስ አበባም የሚሠራ መልዕክት ነው።

ያንን ብቻ ሳይሆን አያይዘውም ምንም እንኳ ዘመነኛው ነገር ተፈላጊ ቢሆንም፣ ማኅበረሰብ መለስ ብሎ እሴቶቹን የሚቃኝበት ወቅት ላይ እንደምንገኝ አስታውሰዋል። እንዲህ አሉ፤ ‹‹ጥቅጥቅ ያሉ፣ በእግር ለመሄድ ምቹ የሆኑ፣ ብዙ ታሪክ እና ውበት ያላቸው ከተሞች ውስጥ መኖርና መሥራት አሁን ላይ በጣም ዝነኛ እየሆነ ነው። ታሪካዊ ኪነ ሕንጻ ያለባቸው ከተሞች፣ በተለይ ሌላውን መሠረተ ልማት አሟልተው የተገኙት በጣም ተፈላጊ እየሆኑ ነው።›› ብለዋል።

- ይከተሉን -Social Media

ታድያ ግን እነዚህ ቅርሶች ወደ ግል ይዞታ ሲዞሩ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ሊከታተላቸው መብት የለውም ወይ? ሊጠብቃቸውስ ግዴታ የለበትም? ስለሥልጣን ሲነሳ… አቤል ይህን ጉዳይ አንስተው ሲያስረዱ፤ የአዲስ አበባ ቅርሶች በተለያዩ ባለይዞታዎች ስር እንዳሉ በማውሳት ጀምረዋል። በመንግሥት ስር የቤቶች ኮርፖሬሽን እና ቀበሌ የሚያስተዳድራቸው፤ ብሎም በመንግሥት ልማት ድርጅት ስር የሚገኙ አሉ።

ከዛ ባሻገር ደግሞ በግለሰብ ይዞታ ያሉ አሉ። 80 በመቶ ገደማ የሚሆኑት በቅርስነት የተመዘገቡ ሕንጻዎች በፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ስር እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ። ታድያ ቅርሶች ከመንግሥት ወደ ግል ይዞታነት ሲሻገሩ ጥንቃቄ እንደሚደረግና የባለይዞታ መብቶች ላይ የሚቀመጡ ነጥቦች እንዳሉ ጠቁመዋል።

በዚህ ላይ ክፍተት ሲኖር ግን፤ ልክ አሁን በበጎ አድራጎት ሕንጻ ላይ የሆነው ዓይነት ክስተት እንደሚፈጠር ነው ያስረዱት። እንዲህ ያለው ክስተት በውስጡ ያለውን ጉዳይ በውስጥ ሥራውን የሠሩት የሚያውቁት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በውጪ ሆኖ ለሚታዘብ ግን በሚመለከታቸው አካላት መካከል የመናበብ ክፍተት መኖሩን መታዘብ እንደሚችል አቤል ተናግረዋል። እንዲህም በዝርዝር አስቀመጡ፤ ‹‹የአዲስ አበባን ቅርስ የሚያስተዳድረው የአዲስ አበባ ቱሪዝም ነው። የአዲስ አበባ መሬትን የሚያስተዳድረው መሬት ባንክ ነው።

የአዲስ አበባን አዳዲስ ግንባታ የሚያስተዳድረው የአዲስ አበባ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ጽሕፈት ቤት ነው፤ የአዲስ አበባን ኢንቨስትመንት እየሰጠ ያለው የኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት ነው። እነዚህም ሁሉ በአንድ ካቢኔ ስር በአንድ ጠረጴዛ ቁጭ ብለው የሚመክሩ ባለድርሻዎች ናቸው።›› ታድያ እንደተጠቀሰው፤ ለግል ይዞታ የሚሰጡ ቅርሶች ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባትና እንዳይፈርሱና ጉዳት እንዳይደርስባቸው የመጠበቅ ኃላፊነት በከተማ አስተዳደሩ ላይ አለ።

እንኳን ማፍረስና ማደስ ሲያስፈልግ ራሱ ፈቃድ መጠየቅ እንደሚገባና፤ ይህም ቀጥታ ከክፍለ ከተማ ሳይሆን ከአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ በቅድሚያ የሚገኝ ፈቃድ ነው። ‹‹አንድ ባለሀብት ላለማ ነው ሲል ይዞታው ቅርስ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ላይ አስተያየት ስጡ ተብሎ ለሚመለከተው አካል መቅረብ አለበት።›› ሲሉም አካሄዱን ገልጸዋል። አዲስ ማለዳ በፍጥነት ምላሽ ያገኘች ባይሆንም፣ በእርግጥ ቢሮው ዐይቶ ወይም ተነግሮት ነበር ወይ የሚለውን ጥያቄ በይደር አቆይታዋለች።

ማን ይጠየቅ?
‹‹እኔ ትልቅ ኃላፊነትና ተጠያቂነት አለ የምለው የከተማ አስተዳደሩ ላይ ነው። ምክንያቱም ልማትን የሚጠላ ግን ደግሞ ቅርስ እንዲወድምም የሚፈልግ የለም። እና ይህን የማጣጣም ኃላፊነት ተሰጥቷቸው መንግሥት በጀት እየመደበ ባለሙያ ቀጥሮ እያሠራ ነው። እና በምን ተአምር ነው ይህ ነገር ሁሌ የሚከሰተው?›› አቤል ይጠይቃሉ።

ሥሙ ቀጥታ የሚገናኘው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በ1992 አሁን ባለው መጠሪያ ከተቋቋመ ጀምሮ በርካታ ኃላፊነቶች ተረክቧል። በአዋጅ በ209/1992 ከተቀመጡ ሥልጣንና ተግባራት መካከል ቅርስ ምዝገባና ቁጥጥር፣ ጥናትና ምርምር፣ ቅርስ ማሰባሰብ ብሎም ጥበቃና እንክብካቤ ማድረግ፣ የማይንቀሳቀሱ ቅርሶችን አልምቶ ለቱሪስት ተደራሽ ማድረግ፣ እንዲሁም የተንቀሳቃሽ ቅርሶች ልማትና አውደ ርዕይ የማቅረብ ኃላፊነቶች አሉበት።

በአዲስ አበባ በቅርሶች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥፋት በተመለከተ፤ አዲስ ማለዳ እንደተረዳችው፤ ባለሥልጣኑ የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ከአቅሜ በላይ ነው ካላለ በቀር ጣልቃ አይገባም። ከዛም አልፎ እንደአገር ካለው የቅርስ ብዛትና ስፋት አንጻር ባለሥልጣኑ ለሁሉም ተደራሽ መሆን አለመቻሉ እንደ ነጥብ ከቀረበ፣ በአዲስ አበባ ጉዳት የደረሰባቸውን ቅርሶች በተመለከተ ሙሉ ኃላፊነቱ የአዲስ አበባ የባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ነው ማለት ነው። አሁንም መለስ ብለን አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም በጉዳዩ ላይ የሠራችውን ዘገባ እናውሳ።

በወቅቱ በአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ውስጥ ከቅርስ ጋር በተገናኘ የሚሠሩ ባለሞያዎች ሲናገሩ፤ በቢሮው ለቅርስ ክፍሉ የሚሰጠው ትኩረትና አመለካከት በእጅጉ አነስተኛ ነው ብለዋል። ከዛም በተጓዳኝ በአዲስ አበባ በዝንጋኤና ቸልተኝነት ምክንያት የሚመለከታቸው የመንግሥትና የከተማ አስተዳደሩ ክፍሎች ለቅርሶች የሚያደርጉት ጥበቃ ውስን ነው። አዲስ አበባ ላሉ ቅርሶች የሚሰጠው ትኩረት እጅግ አነስተኛ ሲሆን ስለቅርስ በቂ ግንዛቤና ተቆርቋሪነት የሌላቸው ሰዎች ተቋማቱ ውስጥ ይገኛሉ ብለው ነበር።

እነዚህ ችግሮች አሁን ላይ ምን መፍትሄ አግኝተው እንደሆነ ባይታወቅም፤ አሁንም ግን ቅርሶች እየፈረሱ ነው። ከፈረሱትም በላይ በዚህ ከቀጠለ ቀጣይ የሚሆነውም አሳሳቢ ነው። አቤል ደግሞ አሁን ላይ የአዲስ አበባን ቅርስ የሚያስተዳድረውስ ማን ነው ብለው ይጠይቃሉ። በዚህም በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ሳይቀር የሚጣረሱ ነጥቦች እንዳሉና፤ በአንድ ጎን የፌዴራል መንግሥት የተፈጥሮ ሀብቶችንና ቅርሶችን ያስተዳድር ሲል፤ በክልልና ከተማ አስተዳደር ደረጃም በተመሳሳይ ክልሉ እንዲያስተዳድር ሥልጣኑን ይሰጣል። ይህም ግልጽ ያልሆነና የሚጋጭ ሲሆን፣ አዲስ አበባን በሚመለከት የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ሥራ ምን እንደሆነ በአግባቡ መጤን አለበት ብለዋል።

የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ሥራ ምንድን ነው? እስከ ምን ድረስስ መግፋትና መሥራት የሚለውም መታየት እንዳለበት አሳስበዋል። ‹‹እኔ የሚታየኝ የአዲስ አበባ ቅርሶች ባለቤት አልባ የሆኑ ትልቅ ሀብቶች እንደሆኑ ነው። ሁሌ ቱሪዝም ይባላል ግን አልተሠራበትም።›› ብለዋል። እንዲሁም በአንድ ጎን ቱሪዝም ላይ መሥራት እየታሰበ በሌላ በኩል ለቱሪዝም የሚያግዙ ጥንታዊና ታሪካዊ ሀብቶችን ማውደም እርስ በእርሱ የሚጋጭና የሚጣረስ መሆኑን ጠቁመዋል።

እናም እስከ አዋጅ ድረስ መቀየር የሚያስችልና አዳዲስ ተቋማት መገንባት ካለባቸውም እዛ ድረስ የሚዘልቅ እርምጃ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። በመጨረሻም ይህን አሉ፤ ‹‹አሁንም በዘላቂነት በንግግር ካልተፈታ ወደፊትም ይቀጥላል [ቅርስ መፍረሱ]። በዚህ ብቻ የሚገደብ አይደለም። 15 ዓመት ቢያንስ የመጀመሪያው እድገትና ትራንስፎርሜሽን በ2002 ከመጣ ጀምሮ በልማት ሥም የሚደረጉ ትላልቅ የቅርስ ወንጀሎች አሉ፤ ከከመሬት ጋር የሚያያዙ ጉዳዮችም አሉ።

እነዚህ እንዴት ይፈታሉ የሚለው አስቀድሞ የጠቀስናቸው የተለያዩ የመንግሥት አካላት ቁጭ ብለው ካልተወያዩ ችግሩ ወደፊትም የሚቀጥል፣የሚያሳዝን እና ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ነው።›› ማን ይጠየቅ ስንል አንድም መፍትሔው አፈላልጎ ብሎም የተሰጠውን ሰምቶ ማን ይተግብር እያልን ነው። ሰላም ተወልደብርሃን በሠሩት ጥናት ባስቀመጡት ምክረ ሐሳብ ላይ፤ ፖሊሲ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ መክረዋል።

እንዲሁም ብቁ ባለሞያዎችን መቅጠር፣ በየጊዜው ተከታታይነት ያላቸው ጥናቶችን ማድረግ ግንባታዎቹን ለመጠበቅ ያግዛል ብለዋል። ሕንጻዎቹን ጠብቁ ብሎ ድምጽ ከማሰማት በተጓዳኝ የተለያዩ ገቢ አስገኚ ዝግጅቶችን በማድረግ ሕንጻዎቹ ለማቆየትና ለመንከባከብ ጥረት ማድረግንም እንደ ሐሳብ አቅርበዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 195 ሐምሌ 23 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች