የአገራዊ ምክክሩን ሂደት የሚከታተል ቡድንን የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት አቋቋመ

0
591

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የአገራዊ ምክክሩን ሂደት የሚከታተል ቡድን ማቋቋሙን የገለጸው ሊካሄድ የታሰበው አገራዊ ምክክርን አስመልክቶ ከሲቪል ማህበራት እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በተወያየበት ወቅት ነው።

በመጪው ህዳር ወር ሊጀመር በታሰበው በዚሁ አገራዊ ምክክር ላይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማስቻል ያለመ ውይይት መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ሔኖክ መለሰ እንደተናገሩት፤ የሲቪል ማኅበረሰቡ አባላት ለአገራዊ ምክክሩ ስኬት ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ነው።

ዘርፉን እንዲወክል በተሰጠው ሥልጣን መሰረትም የሲቪል ማኅበረሰቡን በማንቀሳቀስ በምክክሩ በእውቀት ላይ የተመሰረተ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ምክር ቤቱ እየሰራ መሆኑንም ተነግሯል።

ምክር ቤቱ በአሁኑ ወቅት ከሲቪል ማኅበረሰቡ የተውጣጣና አገራዊ የምክክር ሂደቱን የሚከታተል ወይም የ’ሪፈረንስ’ ቡድን ማቋቋሙ የተገለፀ ሲሆን፣ ከአገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች ጋር በመወያየት የሲቪል ማኅበረሰቡ አባላት በምክክሩ ሂደት ውስጥ ሊኖራቸው የሚችል ሚናን መለየት መቻሉን አሳውቋል።

ምክክሩ የአገሪቱ ዋነኛ አጀንዳ እየሆነ መምጣቱን የተናገሩት የምክር ቤቱ የፕሮግራም እና ልማት አማካሪ ዶክተር ሞገስ ደምሴ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በዚህ አገራዊ ምክክር ላይ ለመሳተፍ እና የመፍትሔ አካል ለመሆን ፍላጎት ማሳየታቸውንና

ድርጅቶቹም ለተለያዩ አገራዊ ችግሮች የመፍትሔ ሀሳቦችን በማቅረብ አስተዋጽኦ ለማድረግ እየተጉ እንደሚገኙ አሳውቀዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 196 ሐምሌ 30 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here