በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል የሚገኙ 10 ዞኖችና 6 ልዩ ወረዳዎች በክልል የመደራጀት ጥያቄን ለፌደሬሽን ምክር ቤት አቅርበዋል።
የደቡብ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ክፍሌ ዋና ሰሞኑን በክልል የመደራጀት ጥያቄ ያቀረቡ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በኹለት ክልል ለመደራጀት ያቀረቡትን ጥያቄ ሰነድ ለፌደሬሽን ምክርቤት አስረክበዋል።
የሚደራጁት ክልሎች የህዝቦችን አንድነት እንዲሁም የጋራ እሴቶችን በሚያጎላ መልኩ ሊሆን እንደሚገባ በምክርቤቶቻቸው የጋራ አቋም መያዛቸውን ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ጌዴኦ ዞኖች፣ እንዲሁም ደራሼ፣ ባስኬቶ፣ ኸሌ፣ አማሮ እና ቡርጂ ልዩ ወረዳዎች አንድ ላይ በክልል እንደራጃለን በማለት በየምክር ቤቶቻቸው በማጽደቅ መወሰናቸው ነው የተገለጸው፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ስልጤ፣ ከምባታ ጠምባሮ፣ ሀዲያ፣ ሀላባ፣ የም ልዩ ወረዳ በአንድ ላይ በመሆን ክልል ለመመስረት በምክር ቤቶቻቸው በማጽደቅ የጋራ አቋም መያዛቸውንም ተጠቁሟል፡፡
የፌደሬሽን ምክር ቤት በህገ መንግስቱ የተሰጠውን ስልጣን መሰረት በማድረግ በሚወስነው ውሳኔ መሰረት ክልል ለመሆን መወሰናቸውን መግለጻቸውን የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል።
የፌደሬሽን ምክር ቤት ኹሉም ምክር ቤቶች ያስተላለፉት ውሳኔ የህዝቦችን ውክልና ያሳየ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ በዚህም መሰረት 10 ዞኖች እና 6 ልዩ ወረዳዎች በኹለት ክልል ለመደራጀት ያቀረቡትን ጥያቄ ምክር ቤቱ መቀበሉን አረጋግጧል፡፡
ቅጽ 4 ቁጥር 196 ሐምሌ 30 2014


