‹የድሃ ድሃ› የተባሉ አንድ ሺሕ በላይ ሰዎች ለመንግሥት የቤት ኪራይ ለመክፈል መቸገራቸውን ገለጹ

0
770

በአዲስ አበባ ከተማ 11 ክፍለ ከተሞች ተበታትነው የነበሩና ‹የድሃ ድሃ› ተብለው መንግሥት በኮየ ፈጬ ቤት ተከራይተው እንዲኖሩ ያደረጋቸው አንድ ሺሕ በላይ ሰዎች ለመንግሥት የቤት ኪራይ የሚከፍሉት ይቅርና ለእለት ምግብ መቸገራቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

መንግሥት የተለያዩ የአካል ጉዳት ያለባቸው እና አቅመ ደካማ ሰዎችን ‹የድሃ ድሃ› ብሎ በማሰባሰብ በኮየ ፈጬ አስቀምጦ 315 (ሦስት መቶ አስራ አምስት) ብር የቤት ኪራይ እያስከፈላቸው መሆኑን የገለጹት አቅመ ደካሞቹ፤ አሁን ግን የሚከፍሉት ይቅርና የሚመገቡት እንደቸገራቸው ተናግረዋል።

በኮየ ፈጬ ቤት እንዲከራዩ ከተደረጉት ሰዎች መካከል 17 የሚሆኑት ዐይነ ስውር መሆናቸው የተጠቀሰ ሲሆን፤ የዕለት ምግብ እንኳ ማግኘት ስላዳገታቸው ርሃብ እንደተጋረጠባቸው ነው የተናገሩት።

ከዐይነ ስውራን በተጨማሪ በርካታ የእግርና እጅ አካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች ያሉ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ ደግሞ አቅመ ደካሞች ናቸው ተብሏል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ከ10 በላይ የሚሆኑ ችግር የተጋረጠባቸው ሰዎች እንደገለጹት ከሆነ፤ ከሚመገቡበት ቀን ይልቅ ጦም የሚያድሩበት የሚበረክት ሲሆን፤ ምግብ አገኘን የሚሉትም እጸድቅ ያሉ ሰዎች እፍኝ ባቄላ ቆንጥረው ሲሰጧቸው መሆኑን ይናገራሉ።

ሠርተው መብላት እንደማይችሉ በተደጋጋሚ የሚናገሩት እርዳታ ፈላጊዎቹ አሁን ባሉበት ሁኔታ በዋነኝነት በሦስት ችግሮች ውስጥ እንደሚገኙ ነው የገለጹት።

ርሃብ ሰዎቹን ጠፍሮ የያዘ የመጀመሪያው አፋጣኝ መፍትሄ የሚሻ ጉዳይ ነው ብለዋል። በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ከተማዎች የሚገኙ ሠርተው መብላት የማይችሉ አካላት ለምነው ይገባሉ ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ እነርሱ ግን ያሉበት አካባቢ ለልመና እንኳን አመቺ አለመሆኑን ነው የጠቀሱት።

በከተማዋ ዳርቻ በኮየ ፈጬ መኖራቸው መጠለያ እንዲያገኙ መልካም አጋጣሚ ቢሆንም፤ አካል ጉዳተኛ መሆናቸው ደግሞ ለምነው ማግኘት ወደሚችሉብት ሥፍራ እንዳይንቀሳቀሱ አድርጓቸዋል ነው የተባለው።

የወቅቱን ክረምት ቅዝቃዜ ለመቋቋም የሚያስችል የአልባሳት ችግር በኹለተኛ ደረጃ በሰዎች ላይ ፈተና የሆነ ጉዳይ ነው። ላስቲክ ለብሰው ጎዳና ላይ ከሚያድሩት ሰዎች ለየት የሚያደርጋቸው ቤት ውስጥ ውለው ማደራቸው እንጂ አብዛኛዎቹ ሰዎች አልባሳት እንደሌላቸው ነው የተመላከተው።

በሦስተኛ ደረጃ የተነሳው ችግር የቤት ኪራይ ክፍያ አለማግኘት መሆኑን ማወቅ ተችሏል። ሰዎቹ በየወሩ ለመንግሥት 315 ብር የሚከፍሉ ሲሆን፤ ምንም እንኳ ብሩ አናሳ ቢሆንም መክፈል አቀበት እንደሆነባቸው ነው የተገለጸው።

ለእለት ምግብ፤ ለቤት ኪራይ፤ ለአልባሳት እንዲሁም ሌሎች መሰል ነገሮችን ማሟያ የተቸገሩት  ሰዎቹ፤ ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ ከተማ ስር በሚገኙ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች እንደነበሩ ገልጸዋል።

ሰዎቹ የእለት ምግባቸውን የሚያገኙት በተለያዩ የእምነት ተቋማት እየተለመነላቸው መሆኑን በቅርብ ርቀት ሆነው የሚረዷቸው መንበረ ማርያም የተባሉ እናት ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

መንበረ እንደሚሉት ከሆነ፤  ሰዎቹ ከየክፍለ ከተማው ተሰባስበው ወደ ኮየ ፈጬ የሄዱት ከአራት ዓመት በፊት ነው። ምንም እንኳ እስከዛሬ ድረስ እየተለመነላቸው ከዚህ ቢደርሱም አሁን አሁን ግን ለምኖ ማግኘትም አልተቻለም ነው ያሉት።

ብዙ ሰዎች እየደወሉ ሰዎቹ ስላሉበት ሁኔታ መረጃ ይጠይቃሉ ያሉት መንበረ፤ ይሁን እንጂ ወደ ቦታው ጎራ ብሎ እርዳታ ያደረገላቸው ሰው እንደሌለ ነው የገለጹት። የሰዎቹ ብዛት ከአንድ ሺሕ በላይ ነው ያሉት መንበረ፤ በጎ አድራጊዎች ባለሃብቶች እንዲሁም ሌሎች ሰዎች የቻሉትን እርዳታ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 196 ሐምሌ 30 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here