መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናየመምህርነት ሙያ ሥልጠና መመሪያ ተግባራዊ ሊሆን ነው

የመምህርነት ሙያ ሥልጠና መመሪያ ተግባራዊ ሊሆን ነው

ለመምህራን የደረጃ እድገት አንድ መመዘኛ የሆነው የመምህርነት ሙያ ሥልጠና (PGDT) መመሪያ ተዘጋጅቶ ተግባር ላይ እንዲውል ለኹሉም ክልሎች መላኩን የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ገለጸ።

የሙያ ሥልጠናው ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝና በአጠቃላይ እንደ አገር በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት በክረምት ወራት በዩንቨርሲቲዎች ሲሰጥ የነበረው ሥልጠና ተቋርጦ በመቆየቱ፣ ላለፉት ዓመታት የመምህራን የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ መቆየቱ ነው የተገለጸው።

ስለሆነም፣ ማኅበሩ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ባደረገው ጥረት ችግሩን የሚፈታ መመሪያ ተዘጋጅቶ ለአፈጻጸም ተግባር ላይ ሊውል መሆኑን ነው ያሳወቀው።

በዚህም ትምህርት ሚኒስቴር የማስተማር ሙያ ሥልጠና ከመምህራን ደረጃ እድገትና ትምህርት ደረጃ መሻሻልን በሚመለከት ለቀረቡ ጥያቄዎች ስምምነት የተደረሰባቸውን ነጥቦች በመለየት ተግባራዊ እንዲሆኑ ለኹሉም ክልሎች በደብዳቤ አሳውቋል።

ለአብነትም የቅጥር ውል ፈርመው በኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያስተማሩ የሚገኙ የአፕላይድ ሳይንስ ተመራቂዎችን በተመለከት በተሰጠው ምላሽ፣ በኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በማስተማር ላይ ያሉ አገልግሎታቸው ከሦስት ዓመት በታች የሆኑ የአፕላይድ ሳይንስ ምሩቃን በፌዴራል የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ሆነው፣ የመምህርነት ሙያ ላሟሉ ጀማሪ መምህራን ከተፈቀደው አንድ ደረጃ ዝቅ ያለ መነሻ ደሞዝ እንዲያገኙ ይደረጋል ነው የተባለው።

በተለያዩ የመንግሥት ዩንቨርሲቲዎች ተመድበው የማስተማር ሙያ ሥልጠና ከጀመሩ በኋላ በኮሮና ወረርሽኝና በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ማጠናቀቅ ያልቻሉ ኹሉም የአፕላይድ ሳይንስ ተመራቂ መምህራን የአገልግሎት ጊዜያቸውን ግምት ውስጥ ያስገባ ለአንድ ጊዜ ብቻ የደረጃ እድገት የተፈቀደ መሆኑም ተገልጿል።

ይህም ከሦስት ዓመት በታች አገልግሎት ያላቸው ለጀማሪ መምህር የሥራ መደብ የተያዘውን መነሻ ደሞዝ የሚያገኙ ሲሆን፣ ከሦስት እስከ አምስት ዓመት አገልግሎት ያላቸው መለስተኛ መምህር ለሚለው ደረጃ የተያዘውን መነሻ ደሞዝ ያገኛሉ።

ከስድስት እስከ ስምንት ዓመት አገልግሎት ያላቸውና በማስተማር ላይ ያሉት ደግሞ መምህር ለሚለው እርከን የተያዘውን መነሻ ደሞዝ የሚያገኙ እንደሆነ ነው የታወቀው።

የትምህርት ዝግጅታቸውን ከዲፕሎማ ወደ መጀመሪያ ዲግሪ ለማሻሻል በመንግሥት ወጪ ሥልጠና እየተከታተሉ ያሉ ነባር መምህራን፣ ቀደም ባሉት ዓመታት ሥልጠናውን ሲከታተሉ ቆይተው በኮሮና ወረርሽኝና በጸጥታ ችግር ምክንያት የማስተማር ሙያ ሥልጠናውን ባያጠናቅቁም፣ የአካዳሚክ ኮርስ ስለማጠናቀቃቸው ሥልጠና ከሚወስዱበት ዩንቨርሲቲ ማስረጃ ካቀረቡ ለአንድ ጊዜ ብቻ ትይዩ የደረጃ እድገት ያገኛሉ ተብሏል።

በግል ትምህርት ተቋማት በማስተማር ሥራ የተሰማሩ የአፕላይድ ሳይንስ ተመራቂዎችን በተመለከተም፣ የማስተማር ሙያ ሥልጠና በቀጣሪዎች ወጪያቸው እየተሸፈነ ሥልጠናውን እንደሚወስዱና አሰራሩም በትምህርት ሚኒስቴር ቁጥጥር እንደሚደረግበት ነው የተገለጸው።

የተሰጠው ውሳኔ ተዛማጅ ባልሆኑ የትምህርት መስኮች የትምህርት ደረጃቸውን ከዲፕሎማ ወደ መጀመሪያ ዲግሪ ወይም ከመጀመሪያ ዲግሪ ወደ ኹለተኛ ዲግሪ ያሻሻሉ/የሚያሻሽሉ መምህራን የማይመለከት ነው።

ከዐስር ዓመት በላይ የማስተማር ሙያ ሥልጠና ሳይወስዱ ማስተማር ሥራ ላይ ያሉ የአፕላይድ ሳይንስ ተመራቂዎች፣ የትምህርት ጥራትን ቅድሚያ ከመስጠት አንጻር ከመምህርነት ሙያ እንዲወጡ ተደርጎ ወደ ድጋፍ ሰጪ ሥራ የሚሰማሩበት አግባብ ይመቻቻልም ተብሏል።

መመሪያው ከነሐሴ 1/2014 ጀምሮ ተፈጻሚ እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 196 ሐምሌ 30 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

አስተያየት

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች