አንድ የትምህርት ተቋም ፍቃድ የተሰጠው ለማስተማር እንጂ፤ መጽሐፍም ሆነ ደብተር ለመሸጥ አይደለም ሲል የአዲስ አበባ ትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ ማንኛውም የግል ትምህርት ቤቶች ከመመሪያ ውጪ ያልተገባ ክፍያ አስከፍለው እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ገልጿል። በመመሪያ አተገባበሩ ላይ የተለያዩ ጥቆማዎች እየደረሱት እንደሚገኝም ባለስልጣኑ አክሏል።
በመመሪያ አተገባበሩ ላይ ከመጡት ጥቆማዎች ውስጥ አንዳንድ ተቋማት የምዝገባ ክፍያ መጨመር፣ በዓይነት መቀበል ለአብነት እሽግ ወረቀት እና የመፀዳጃ ቤት የንፅህና እቃዎችን የሚጠይቁ እንዳሉበት ነው የተመላከተው።
ማንኛውም የግል ትምህርት ቤቶች ከመደበኛ ክፍያ ውጪ በየትኛውም መልኩ ክፍያ ማስከፈል አይቻልም፤ አንድ የትምህርት ተቋም ፍቃድ የተሰጠው ለማስተማር እንጂ መጽሐፍም ሆነ ደብተር ለመሸጥ አይደለም ነው የተባለው።
ከተሰጠው ፍቃድ ውጪ ሲንቀሳቀስ በሚገኝ ተቋም ላይ እርምጃ ይወሰድበታል፤ የሰበሰበውን ገንዘብም ሆነ ማንኛውንም አይነት ቁሳቁስ እንዲመልስ ይደረጋል ሲልም ባለስልጣኑ አስገንዝቧል።
ቅጽ 4 ቁጥር 197 ነሐሴ 7 2014


