በጋምቤላ ክልል የቡና ማሳችንን ተነጥቀናል ያሉ አርሶ አደሮች መንግሥት ፍትህ ሊሰጠን አልቻለም አሉ

0
1143

በጋምቤላ ክልል የቡና ማሳችንን በሕገ ወጥ መንገድ ተነጥቀናል ያሉ አርሶ አደሮች መንግሥት ፍትህ ሊሰጠን አልቻለም ሲሉ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ አቀረቡ።

አርሶ አደሮቹ ከ10 ዓመት በፊት ሕጋዊ መሬታችን ታግዶ በሙስና ለባለሀብት በመሰጠቱ ቤተሰቦቻችን እንዲበተኑና የጎዳና ተዳዳሪ እንድንሆን የተገደድን በመሆኑ፣ መሬታችን እንዲመለስልን በተደጋጋሚ የተወሰነልን ቢሆንም የሚያስፈጽምልን አካል ባለመኖሩ ፍትህ ተነፍጎናል ሲሉ ተናግረዋል።

በክልሉ ማጃንግ ብሔረሰብ ዞን፣ መንገሽ ወረዳ የሪ ቀበሌ ነዋሪ የነበሩና የሸሲ ቡና ተክል አምራች ገበሬዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መሥራችና የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አደመ ገ/ጻዲቅ፣ በ1998 መንግሥት ከአራት ሄክታር በላይ መሬት ያላቸው ገበሬዎች በማኅበር እንዲደራጁ ወይም የኢንቨስትመንት ፍቃድ እንዲያወጡ በጠየቀው መሠረት 13 ሆነው ተደራጅተው 200 ሄክታር የሚደርስ መሬታቸውን ለማልማት በ2006 ፈቃድ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ፣ የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ገበሬዎቹን ደን መንጥረዋል በሚል ሐሰተኛ ክስ ይዞታቸውን አስለቅቆ ለባለሀብቶች በሙስና ሰጥቷል ነው ያሉት።

በዚህም ከለውጡ በፊት በነበረው ጊዜ ይግዛው በዛብህ ሀጎስና ገብረ መድኅን ፀጋየ ለሚባሉ አካላት 1 ሺሕ 400 ሄክታር የሚደርስ የአርሶ አደርች መሬት በድብቅ ለ50 ዓመት ካርታ የተሠራላቸው ሲሆን፣ ከለውጡ በኋላ ደግሞ በሐሰት ካርታ የተሠራበት መሬት ለመሬት ባንክ ይመለስ ሲባል ከእነሱ ተነጥቆ ወደ ባንኩ ከገባ በኋላ ለሌሎች ባለሀብቶች ተሰጥቷቸው እያለሙበት ነው በማለት ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎም ከአንድ ሺሕ በላይ አርሶ አደሮች ቡና አብቃይ የሆነ መሬታቸውን በግፍ ተነጥቀው የተበተኑ መሆኑን በማንሳት፣ ብዙዎች ለልመና እና ለጎዳና ሕይወት ተዳርገዋል ነው ያሉት።

በመሆኑም፣ ምንም ማድረግ ያልቻሉት ሲበተኑ፣ ክስ ያቀረቡትን ደግሞ በውሸት በአካባቢው በሚነሱ ግጭቶች ተጠያቂ በማድረግ ለሀሰተኛ እስር በመዳረግና በመደብደብ ለ10 ዓመት ያህል እንግልት የደረሰብን ሲሆን፣ ለክልሉ መንግሥትና ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ጉዳዩን አቅርበን አራት ጊዜ እንዲመለስልን ቢወሰንም የሚያስፈጽም አካል አጥተናል ሲሉ ተደምጠዋል።

አሁንም ቢሆን መሬታችን የሚገኝበት የሪ ቀበሌ የሚመለከተው አካል መጥቶ ርክክብ እንዲያደርግ ጠይቋል። የዞኑ ፍርድ ቤትም ከደን ምንጣሮ ጋር የተነሳብን ክስ ተመልክቶ በሕጋዊ መንገድ የለማ ነው በማለት በነጻ አሰናብቶናል። የክልሉ መንግሥትም ለዞኑ አስተዳደር መሬታችን እንዲሰጠን በዚሁ ዓመት የፈቀደ ቢሆንም፣ ውሳኔው እንዲተገበር ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት በጽሑፍ ምላሽ ወደታች እንዲወርድ ስላላደረገ መሬታችንን ማግኘት አልቻልንም ብለዋል።

‹‹እንዲያውም አሁን ላይ የዞኑ ምክር ቤት ጉዳዩን ዐይቶ ለእኛ የወሰነ ቢሆንም፣ የዞኑ አስተዳደር ከዚህ በፊት የተወሰኑ ውሳኔዎች አይመለከቱኝም። ለማስፈጸምም አልገደድም በማለት ዋና አስተዳዳሪ ቢሮዬ አትምጡ ያለ ሲሆን፣ የክልሉ አስተዳደርም ከዚህ በፊት አራት ጊዜ ውሳኔ ሰጥተናል። ከእንግዲህ የምንሰጠው ምላሽ የለም በማለት፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትም ከወረዳና ከቀበሌ ስልክ አምጣ በማለት ከተነጋገሩ በኋላ ‹የፈለግህበት ሄደህ ክሰስ› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል›› ነው ያሉት።

ስለሆነም፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አይመለከተኝም ከማለትና በቃል ከሚሰጠው መልስ ይልቅ መሬታችን መሆኑ በሕግ የተገለጸ በመሆኑ፣ የጽሑፍ ምላሽ እንዲሰጥና እንዲያስፈጽምልን ሲሉ ጠይቀዋል።

አርሶ አደሮቹ መሬታችን በሙሉ ተወስዶ ያለምንም ነገር ከመቅረታችንም በላይ፣ በምናመለክትበት የመንግሥት ቢሮ ኹሉ፣ መሬታችንን ለሚጠቀሙበት ሰዎች መረጃው ቀድሞ የሚደርሳቸው በመሆኑ አቤቱታችን እንዲታፈን ያደርጋሉ ሲሉ ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ ጉዳዩን አስመልክቶ ማብራሪያ ለማግኘት ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት በተደጋጋሚ ብትደውልም ሳይሳካ ቀርቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 197 ነሐሴ 7 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here