“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።
በሥራ አጋጣሚ የተሳተፍኩበት አንድ ሥልጠና ላይ አሠልጣኛችን የሆኑት መምህር የነገሩንን አጋጣሚ በማውሳት ልጀምር። ነገሩ እርሳቸው እንደነገሩን ቃል በቃል ባይሆንም፤ እኔ ጋር በቀረበት መጠንና መልክ ላጫውታችሁ።
አንድ አነስተኛ ገጠር ነው፤ በሴቶች ጉዳይ ላይ የሚሠራ ድርጅት ይሄዳል። የድርጅቱ ሠራተኞች በአካባቢው ለሚኖሩ ወጣት ሴቶች ምን ያስፈልጋቸውል የሚለውን ተመልክተው፤ ውሃ ለመቅዳት ወንዝ ይወርዳሉና ለምን የውሃ ቦኖ አንገነባላቸውም ብለው ያንን ያደርጋሉ፤ ሠርተውም ያስመርቃሉ።
ከዓመት በኋላ ድርጅቱ ሴቶቹን እንደምን ከረማችሁ ብሎ ሊጠይቅ ሲያቀና፤ በቦኖው ውሃ የሚጠቀመው እምብዛም ነበር። ምነው ሲባል፣ ለካ እነዛ ሴቶች ወንዝ ወርደው ውሃ ሲቀዱ ምንም እንኳ ድካም ቢኖረውም መንገድ ላይ ይወያያሉ፣ ይጫወታሉ፣ ምስጢራቸውን ይነጋገራሉ ወዘተ። ስለዚህ በጣም በቅርበት የተሠራላቸውን የውሃ ቦኖ አልፈለጉትም።
እርግጥ ነው! መፍትሄ ችግርን ከማወቅ ይጀምራል። ችግርን ለይቶ ማወቅም ቀላል ነገር አይደለም። ሐኪም የታካሚውን ገጽ ዐይቶ ‹በሽታህ እንዲህ ሊሆን ይችላል!› ብሎ መድኃኒት እንደማያዘውና መጀመሪያ ሕመምተኛውን እንደሚጠይቀው ሁሉ፤ ችግርህ ምንድን ነው፣ ይህ ነገር ይቸግርሃል ወይ ብሎ ባለጉዳይን መጠየቅ ወሳኝ፣ አግባብ እና ተገቢ ነው።
በቅርቡ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኀን ብዙዎች የአንዲት አስተናጋጅን በዝናብ መስተንግዶ ስትሠራ የሚያሳይ ምስል ሲቀባበሉ ነበር። ብዙዎችም አለባበሷ አግባብ እንዳሆልነና በርካታ ሆቴሎች አስተናጋጆች በተመሳሳይ ሰውነትን ለዝናብ ብቻ ሳይሆን ለፀሐይና ለዐይን የሚያጋልጡ ልብሶችን እንዲለብሱ ግድ እንደሚሏቸው ሲናገሩ ተሰምቷል። ለዛም ንቅናቄ መፍጠርና እንደዛ እንዳይሆን ማድረግ እንደሚገባ ብዙዎች ሲያሳስቡ ቆይተዋል።
ይህ ትልቅ ነገር ነው። ትኩረት አግኝቶ ሰዎች በዛ መጠን ጉዳያቸው አድርገው ለአስተናጋጆች ሲሞግቱና ‹እንዴት አይታሰብላቸውም› ብለው ሲሟገቱ መስማት ደስ ይላል። ነገር ግን አንድም አስተናጋጅ የሆነች ሴት ስትጠየቅ ወይም ስትናገር አልሰማሁም፣ አላየሁም። በእርግጥ ሁሉም ቦታ ላስስ ስለማልችል፣ ለእኔ ቅርብ በሆኑ አውዶች ሁሉ ማሰስ አልችልምና በጉዳዩ ላይ ሐሳብ የሰጠች አስተናጋጅ ካለች አላውቅም። ኖራ ወይም ኖረው ከሆነ ይቅርታ ይደረግልኝ።
ግን መጀመሪያ መጠየቅ ይቀድማል። በሁሉም ጉዳይ ማለቴ አይደለም። ምሳሌ እስከ ፍጻሜው የሚያጻና ስለማይሆን፣ በሁሉም ጉዳይ መጠያየቅ ላያስፈልግ ይችላል። ለምሳሌ ‹ምን ለብሳ ነበር?› የሚል በሴታዊት ንቃናቄ የተዘጋጀ አውደ ርዕይ ተጽእኖ መፍጠር የቻለው፣ መልዕክቱን እንዲሰሙ የተፈለጉ ዜጎች ጉዳዩን በቀጥታ ከባለታሪኮች ልብስ እንዲመለከቱ በመደረጉ ነው።
ልክ እንደዛው ሁሉ፤ በሰዎች ጫማ ውስጥ ሆኖ የሰዎችን ሕመም ማዳመጥ ወሳኝ ቢሆንም፤ መፍትሄ ለማምጣት ግን ከግምትና ስሜት ባሻገር ባለጉዳዩቹን ‹ምን እንድናደርግ ትወዳላችሁ?› ብሎ መጠየቅ መቅደም አለበት እላለሁ። እናንተስ ምን ትላላችሁ?
መቅደስ ቹቹ
ቅጽ 4 ቁጥር 197 ነሐሴ 7 2014


