ክረምትና ድንገተኛ አደጋ

0
1375
© SANDILE NDLOVU

የተፈጥሮ ድንገተኛ አደጋ የምንለው በሕይወት፣ በአካል ወይም በንብረት ላይ ያልታሰበ ድንገተኛ አደጋ በሚከሰትበት ወቅት ነው። በዚህም እንደ እሳት፣ ጎርፍ፣ ሰደድ  እሳት፣ ከፍተኛ ሙቀት እና የመሬት መንሸራተት እንዲሁም የመሬት መንቀጥቀጥና አውሎ ነፋስን የመሳሰሉ አደጋዎች በድንገተኛ አደጋ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው።

ከእነዚህ መካከል ደግሞ የብዙ ኢትዮጵያዊያንን ሕይወት እና ንብረት በየወቅቱ ከሚያሳጣ መካከል የእሳት እና የጎርፍ ድንገተኛ አደጋ ተጠቃሽ ነው።

በ2014 በጀት ዓመት በአዲስ አበባ እና በአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን 362 የእሳት ቃጠሎ እና 148 የተለያዩ ድንገተኛ አደጋዎች በአጠቃለይ 510 ድንገተኛ አደጋዎች መድረሳቸውን የአዳስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና ድንገተኛ አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን መረጃ ይጠቁማል።

በተያዘው የክረምት ወቅት በሐምሌ ወር ብቻ በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ልዩ ዞን 9 ሰዎች ወንዝ ውስጥ ገብተው ሞተው ተገኝተዋል ተብሏል። በተጨማሪ በዚሁ የክረምት ወቅትም በተከሰተው ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ በአማራ ክልል እንዲሁ ኹለት ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ እና በንብረትም ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ተነግሯል።

ይህ የክረምት ወቅት እና ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ ጦሱን እያስፋፋ ብዙዎችን እያሰጋቸው እንደሚገኝም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ሲያነሱ ይደመጣል።

ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ እና የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በተያዘው ዓመት የክረምት ወራት ከመጠን ያለፈ ዝናብ መጣሉን ተከትሎ ከፍሳሽ ማስወገጃ ወይም ከድሬኔጅ መስመር አልፎ በዋናው የአስፓልት መንገድ ላይ ዘልቆ በሞላው ጎርፍ ሳቢያ ብዙ እግረኞች መቸገራቸውንና እየተጓዙ የነበሩ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎችም በተለያዩ የከተማዋ አውራ ጎዳናዎች ለመቆም መገደዳቸውን ተናግረዋል።

በዚህም ምክንያት ከአንድ ኪሎ ሜትር በላይ የእግር ጉዞ በመጓዝ በሌላ አቅጣጫ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችን መጠቀም ቢቻልም፣ በቋሚነት ተቀጥረው በሚሠሩበት ድርጅት የሥራ ገበታቸው ላይ በሰዓት መድረስ አለመቻላቸውን ገልፀዋል።

በተጨማሪ ለሥራ ጉዳይ ለአንድ ጋዜጣዊ መግለጫ በወቁቱ መገኘት ቢኖርባቸውም፣ ከላይ በተከሰተው ችግር ምክንያት በወቅቱ መገኘት አለመቻላቸውን በመናገር በጎርፍ ምክንያት ሥራዬ ላይ እንቅፋት አጋጥሞኛል ብለዋል።

በተጨማሪ የፍሳሽ ማስወገጃዎች በጎርፍ ተሞልተው የእግረኛ መስመር ላይ ተፅዕኖ ሲያሳድር ማስተዋላቸውንም ተናግረዋል።

እንደ መፍትሄ መንግሥት መንገዶች ለጎርፍ ተጋላጭ እንዳይሆኑ እና የፍሳሽ ማስወገጃዎችም ፍሳሾችን በአግባቡ እንዲያስወግዱ በየወቅቱ ክትትል በማድረግ ኅብረተሰቡ በተደጋጋሚ ከሚያጋጥሙት የአደጋ ገጠመኞች ለመታደግ ሊሠራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ሌላው በጉዳዩ ላይ ሐሳቡን ለአዲስ ማለዳ ያካፈለው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆነው ፍቅረሚካኤል ዘየደ ነው። ፍቅረሚካኤል በተያዘው የክረምት ወቅት የተከሰተው የጎርፍ አደጋ ያደረሰውን ጉዳት በማውሳት፣ ለአብነት ከቀናት በፊት በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 አካባቢ በጣለው ዝናብ የተከሰተውን ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ ጠቅሷል። በዛም በጥቃቅን እና አነስተኛ ተደራጅተው ሥራ በሚሠሩ ኮንቴይነር ቤቶች ውስጥ ዘልቆ በመግባት በንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል ብሏል። አንዳንድ ንብረቶችን መታደግ የተቻለ ቢሆንም፣ በገንዘብ ያልተተመነ ንብረት ላይ ግን ጉዳት መድረሱንም ጠቅሷል።

በተጨማሪ ከኹለት ሳምንት በፊት ከመጠን በላይ በጣለው ዝናብ የተሽከርካሪ መንገዶች በጎርፍ ተጥለቅልቀው የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ የነበሩ ተሽከርካሪዎች ባሉበት ቆመው እንዲቆዩ የተገደዱበት ጊዜ እንዳጋጠመውም ፍቅረሚካኤል ጠቅሷል።

ለእነዚህ ተደጋጋሚ ችግሮች ደግሞ በየዓመቱ ለጎርፍ ተጋላጭ ተብለው የተለዩ ቦታዎች ላይ መሥራት አለመቻል ለችግሩ አንዱ ተጠቃሽ ምክንያት ነው ብሏል።

በተጨማሪ፣ በቦሌና በቄራ አካባቢ በረዥም ጊዜ እቅድ ታስቦባቸው የተሠሩ የመንገድ መሠረተ ልማቶች ያሉ ሲሆን፣ አብዛኛው በሚባል ደረጃ በመዲናዋ ለትራንስፖርት መስመሮች የተዘረጉ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች ላይ የተሠራው ሥራ አናሳ እንደሆነ ይናገራል።

በመፍትሄነት መንግሥት ከዚህ በኋላ የሚሠሩ የመንገድ መሠረተ ልማቶች ተፋሰስን ትኩረት ያደረጉ፣ ተዳፋት እና መጋቢ መንገዶችንም እንዲሁ ታሳቢ አድርጎ ቢሠራ እና ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑት ላይ ትኩረቴ ተሰጥቶ እንዲሠራ ጠይቋል።

በዚሁ የክረምት ወቅት የአዲስ አበባ እሳት እና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እንደተናገረው፣ በከተማዋ በተፈጠሩ 27 የጎርፍ አደጋዎች ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወድሟል።

ከአንድ ሳምንት በፊት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 አማኑኤል ሆስፒታል አካባቢ በመጋዘን ቤት ውስጥ ውሃ በመሙላቱ ግንቡ ተደርምሶ ከስር በሚገኙ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ በነበሩ ሰዎች ላይ ጉዳት በማድረስ የ1 ሰው ሕይወት ሲያልፍ 2 ግለሰቦች ላይ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸውም ተጠቁሟል።

ከዚህ በተጨማሪም በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 እና ወረዳ 9 በተመሳሳይ ወቅት ላይ በጣለው ከባድ ዝናብ ድልድይን ጨምሮ በአካባቢው መሠረተ ልማት ላይ ጉዳት መድረሱም ተነግሯል።

ኮሚሽኑ እንደሚያስረዳው፣ በተጠናቀቀው ሐምሌ ወር ብቻ በአዲስ አበባ እና ዙሪያው እድሜያቸው ከ18 እስከ 60 የሚገመት የ9 ሰዎች ሕይወታቸው አልፎ ከወንዞች ወጥተዋል ብሏል። በከተማዋ 27 የጎርፍ አደጋ ሲያጋጥም የ93 ሰዎች ሕይወት በአደጋ ጊዜ ባለሙያዎች መታደግ መቻሉም ተመላክቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ንጋቱ ማሞ እንደገለጹት፣ በ2014 በጀት ዓመት እንዲሁ 362 የእሳት ቃጠሎ እና 148 ከእሳት ውጪ ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች በአጠቃላይ 510 ድንገተኛ አደጋዎች ተከስተዋል ብለዋል።

ከተከሰቱት አደጋዎች 449 የሚሆኑት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ክልል ውሰጥ የተከሰቱ ሲሆን፣ በደቡብ ክልል አንድ ድንገተኛ አደጋ፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞኖች 60 ድንገተኛ አደጋዎች ናቸው የተከሰቱት ብለዋል።

በአደጋው የ115 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፣ 200 ሰው ደግሞ የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ሲሆን የ57 ሰዎችን ሕይወት ማዳን እንደተቻለም ገልጸዋል።

ከተከሰቱት ጠቅላላ 510 የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ውስጥ 488 ወይም 95 ነጥብ 69 በመቶ አደጋዎችን በስታንዳርዱ መመሪያ መሠረት (ማለትም ከፈጠነ በሦስት ከዘገየ በ15 ደቂቃ ውስጥ አደጋው ቦታ መድረስ መቻል) መድረስ የተቻለ ሲሆን፣ 22 ወይም 4 ነጥብ 31 በመቶ የሚሆኑ አደጋዎች ላይ ግን በተለያዩ ምክንያቶች በስታንዳርዱ መሠረት መድረስ አለመቻሉን ባለሙያው ጠቁመዋል።

ኮሚሽኑ ድንገተኛ አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅት በትንሹ በሦሰት ደቂቃ፤ ዘገየ ከተባለ ደግሞ በ15 ደቂቃ መድረስ ቢኖርበትም፣ አደጋውን ለመቆጣጠር ሦሰት እና አራት እጥፍ ዘግይቶ በቦታው የሚደርስበት ሁኔታ እንዳለ ንጋቱ ይናገራሉ።

በበጀት ዓመቱም 22 የሚሆኑ አደጋዎችን በስታንዳርዱ መሠረት ተገኝቶ መቆጣጠር ያልተቻለበት ምክንያት በመንገድ ወይም በትራፊክ መዘጋጋት ምክንያት ነው ብለዋል።

ባለሙያው አክለውም፣ በአደጉ አገሮች ድንገተኛ አደጋዎች በሚፈጠሩበት ወቅት የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ላይ የሚሠሩ ተቋማት የሚንቀሳቀሱበት ራሱን የቻለ የትራፊክ መስመር ያለ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ግን ከኢኮኖሚ አቅም  አንጻር ይህን ማድረግ እንዳልቻለች ይገልፃሉ።

ኮሚሽኑ የሚነሱ ጥያቄዎች እና ክፍተቶችን ለመቅረፍ በተቻለ መጠን የትራፊክ ፍሰት የማይበዛባቸውን እና አማራጭ ወይም አቋራጭ መንገዶችን በመጠቀም አደጋዎችን ለመቆጣጠር የሚቻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪ ድንገተኛ አደጋዎች በሚያጋጥሙበት ወቅት ኮሚሽኑ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና ለአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ቀድሞ ድንገተኛ ተሽከርካሪዎች እና ሠራተኞች የሚያልፉበትን የትራፊክ መስመር እንዲያስከፍቱ በማድረግ እና የትራፊክ ፍሰቱ የሚቀንስበትን ሁኔታ በማቃለል ረገድ በጋራ በመሆን ሥራዎችን እየሠሩ መሆናቸውን ባለሙያው ጠቁመዋል።

በ2014 በጀት ዓመት ከተከሰቱ አደጋዎች ዝርዝር መካከል ወቅቱ የክረምት እንደመሆኑ ከጎርፍ ጋር የተገናኙት እየተበራከቱ መምጣታቸው ይነገራል። እስከ ሰኔ 30/2014 የነበረው አሐዝ እንደሚያሳየው ወንዝ ውስጥ ከገቡ 29 ሰዎችም 27ቱን ማትረፍ አልተቻለም። ኹለት ሰዎች ሐይቅ ውስጥ ገብተው ሕይወታቸው አልፏል። ኹለት ሰዎች ደግሞ ትቦ ውስጥ የገቡ ሲሆን የአንዱን አንዱን ሕይወት ማትረፍ ሳይቻል ቀርቷል። ድልድይ ውስጥ ከገቡ ኹለት ሰዎችም በተመሳሳይ የአንደኛውን ሕይወት መታደግ አልተቻለም።

የጎርፍ አደጋ ካጋጠማቸው 29 ሰዎች መካከል 11ዱ ሕይወታቸው አልፏል። በኩሬ አደጋ አንድ ሰው፣ በመሬት መደርመስ 7 ሰው፣ ለሕንፃ የተቆፈረ ውሃ የሞላው እንዲሁም የተለያዩ ጉድጓዶች ውስጥ የገቡ 4 ሰዎች፣ ውሃ ታንከር ውስጥ የገቡ 2 ሰዎች፣ ውሃ በመፈንዳቱ 1 ሰው፣ ዛፍ ወድቆባቸው 2 ሰዎች ከውሃ ጋር በተገናኘ ሕይወታቸው አልፏል።

በበጀት ዓመቱ ከደረሱ አጠቃላይ 511 አደጋዎች 338ቱ ምክንያታቸው ያልታወቀ ሲሆን፣ 63 በኤሌክትሪክ ኮንታክት ምክንያት የተከሰቱ አደጋዎች ናቸው። በከባድ ዝናብ 24 እንዲሁም ለመዋኘት ብለው የገቡ 16 ሰዎች ላይ የተከሰቱ የድንገተኛ አደጋዎች ምክንያት ከቀዳሚዎቹ ተርታ ይሰለፋሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 197 ነሐሴ 7 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here