አዲስ አበባ ለመግባት ኦሮሞ መሆን?

0
2063

ከተለያዩ የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በደብረ ብርሃን ወደ አዲስ አበባ የሚያቀኑ ዜጎች ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ፣ መንግሥት ከአንድ ወር በፊት የጀመረው ከመንገድ ላይ የመመለስ ተግባር በዐስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችና በሺዎች የሚቆጠሩ አሽከርካሪዎችን ለእንግልት ዳርጓል። ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ ደብረ ብርሃንን አልፈው ኦሮሚያ ክልል ሲገቡ መነሻ ቦታቸውና መታወቂያቸው እየታየ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ሲንገላቱ የነበሩ ዜጎች “መንግሥት የለም” እስከማለት የደረሰ እሮሮ እያሰሙ ነው።

የዜጎችን የመንቀሳቀስ መብት የነፈገው ችግር ከአንድ ወር በላይ ቢያስቆጥርም፣ መንግሥት ለችግሩ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ለአዲስ አበባ ደኅንነት ስል ያደረኩት ነው የሚል ምላሽ ሰጥቷል። ችግሩ አሽከርካሪዎችና ተጓዦች ወደ አዲስ አበባ እንዳንገባ ተከለከልን ከሚሉት ቅሬታ አልፎ አሽከርካሪዎችና ተሳፋሪዎቻቸው በመታወቂያቸው ላይ በተጠቀሰው ማንነት ብቻ ለድብደባና ለዛቻ መጋለጣቸውን አዲስ ማለዳ በቦታው ተገኝታ በደሉ ደረሰብን ከሚሉት አሽከርካሪዎችና ተሳፋሪዎቻቸው ሰምታለች።

መንግሥት ባሰማራቸው የጸጥታ ኃይሎች ወደ አዲስ አበባ አልፈው እንዳይገቡ በማንነታቸው በጅምላ መንገድ የተዘጋባቸው ዜጎች፣ ደብረ ብርሃንና አካባቢዋን አጨናንቀው ሰንብተዋል። በዚህም ባለፈው ረቡዕ (ነሐሴ 4/2014) ከማለዳ ጀምሮ የደብረ ብርሃን ከተማ ወጣቶች በማንነታቸው ብቻ ለእንግልት የሚዳረጉ ተጓዞች ችግር መፍትሔ ይሰጠው በሚል ደብረ ብርሃን መግቢያ ላይ መስመር ዘጉ ተብሎ ነበር።

አዲስ ማለዳ  በእለቱ አመሻሽ ላይ ተገኝታ እንደተመለከተችው ደብረ ብርሃን መግቢያ ላይ የተዘጋው መስመር ላይ ደብረ ብርሃን ወጣቶች አልነበሩም። ይልቁንም በሰዓቱ በቦታው የነበሩት የመንግሥት ፖሊሶችና ታጣቂዎች፣ እንዲሁም አሽከርካሪዎችና ተሳፋሪዎቻቸው ናቸው። በወጣቶች ተዘጋ የተባለው የደብረ ብርሃን መስመር ላይ የቆሙ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ወደ አዲስ አበባ የሚያቀናውን መስመር ዘግተው ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ የሚያቀናውን መስመር ክፍት አድርገው አዲስ ማለዳ ተመልክታለች።

በሰዓቱ ደብረ ብርሃን መግቢያ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ተሳፋሪዎቻቸውን ይዘው ወደ ደብረ ብርሃንም ይሁን ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ የታገዱት በቦታው በነበሩት የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ነው። አሽከርካሪዎች ለምን እንደቆሙ አዲስ ማለዳ በቦታው የነበሩ ታጣቂዎችን አነጋግራ ያገኘችው ምላሽ፣ “እኛ ብንሰዳቸውም ኦሮሚያ ክልል ሲገቡ አያሳልፏቸውም፣ ይመልሷቸዋል” የሚል ነበር።

ከተለያዩ የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ ተሽከርካሪዎችና ተሳፋሪዎቻቸው ደብረ ብርሃን  አልፈው ሸኖ ሲደርሱ በየቦታው ኬላ በፈጠሩ የኦሮሚያ ክልል የጸጥታ ኃይሎች መታወቂያቸው እየታየና የተነሱበት ቦታ እየተጠየቀ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ ሲመለሱ የነበሩት መጀመሪያ ሰሞን ከወሎ አካባቢ የሚነሱ ሰዎች ነበሩ። ችግሩ ቀስ በቀስ እያደገ የአዲስ አበባ መታወቂያ የሌለው ሰው መግባት አይችልም ወደሚል ምክንያት አድጎ ሳምንታት ካስቆጠሩ በኋላ፣ ችግሩ ዜጎች በብሔራቸው ምክንያት ተለይተው ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ የተከለከሉበት መሆኑን አዲስ ማለዳ መነሻቸውን ደሴ መዳረሻቸውን አዲስ አበባ አድርገው የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ከሚሰጡ አሽከርካሪዎች ሰምታለች።

አዲስ ማለዳ ደብረ ብርሃን መንገድ በተዘጋበት ሰዓት በቦታው ተገኝታ እንደተመለከተችው፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አሽከርካሪዎች ከእነ ተሳፋሪዎቻቸው እየተጉላሉ ነበር። በእለቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በብርድ እየተጠበሱ አዲስ ማለዳ በቦታው እስከቆየችበት ማለትም እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት (ከማለዳ እስከ ምሽት) ደብረ ብርሃን በሯ ላይ ቆመዋል። ዜጎች በአገራቸው የመንቀሳቀስ መብታቸው በጅምላ ያለ ምንም በቂ ምክንያት ሲገደብ የሚደርሰው ሰብዓዊ መብት ጥሰት ቀላል አለመሆኑን፣ የሕክምና ቀጠሮ እያላቸው “በሕመም ላይ ሕመም ተጨመረብን” ከሚሉ ተሳፋሪዎች አዲስ ማለዳ ተረድታለች።

ሕክምና ፍለጋ ከቤታቸው የወጡ ሕሙማን፣ ሴቶች፣ ሕጻናትና አዛውንቶች  የመንቀሳቀስ መብታቸውን በመነፈጋቸው ከደረሰባቸው እንግልት በላይ፣ እየደረሰባቸው ያለው እንግልት በማንነታቸው ብቻ ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ በጅምላ መከልከላቸው መሆኑን ይገልጻሉ። ኑሯቸውን በሥራ ምክንያት አዲስ አበባ አድርገው በአጋጣሚ በተለያየ ምክንያት ከደብረ ብርሃን አልፈው ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ አቅንተው የነበሩ ሰዎችም ባለፈው አንድ ወር የአዲስ አበባ መታወቂያ የላችሁም ተብለው ሥራቸውን ትተው ወደ ኋላ እንዲመለሱ በኦሮሚያ ክልል የጸጥታ ኃይሎች መንገድ ሲዘጋባቸው ነበር።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው አሽከርካሪዎች ከአንድ ወር ወዲህ ተሳፋሪ ጭነው ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ በኦሮሚያ ክልል መንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ብሔርን መሠረት ያደረገ ክልከላና ድብደባ እየተፈጸመብን ነው ብለዋል።

ባለፈው ረቡዕ ማለዳ ደብረ ብርሃን ላይ የተዘጋው መስመር በወጣቶች ነው ቢባልም፣ የታጠቁ የመንግሥት የጸጥታ ኃይል አካላት ተሽከርካሪዎች እንዳያልፋ መስመር ዘግተው ሲጠብቁ አዲስ ማለዳ ተመልክታለች። አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ተሳፋሪዎች እንዲጉላሉ ምክንያት የሆነው የኦሮሚያ ክልል ጸጥታ ኃይሎች ናቸው ብለዋል። አሽከርካሪዎች በበኩላቸው የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል ተሳፋሪዎቻችን በብሔር ለይተው ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ ከማድረጋቸው በተጨማሪ፣ ድብደባና ዘረፋ እየተፈጸመባቸው ነው ሲሉ ጠቁመዋል።

የኦሮሚያ ክልል (ኦ ሮ) ታርጋ ያላቸው ተሽከርካሪዎች በነጻነት ወደ አዲስ አበባ ሲገቡ ነበር የሚሉት አሽከርካሪዎች፣ በአንጻሩ የአማራ ክልል (አ ማ) ታርጋ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች ወደ አዲስ አበባ ለመግባት ከ500 እሰከ አንድ ሺሕ ብር ለኦሮሚያ ልዩ ኃይል ለመክፈል ይገደዳሉ ተብሏል።

አሽከርካሪዎች በቀን ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ ሲከለከሉ፣ በሌሊት ወደ አዲስ አበባ ለመግባት ሲሞክሩ በየቦታው መስመር ላይ የቆሙ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይሎች ብር ካልከፈላችሁ አታልፉም ተብለው ብር ከፍለው ያለፉበት አጋጣሚ መኖሩን ጠቁመዋል።

አሽከርካሪዎች ወደ አዲስ አበባ ለመግባት ደብረ ብርሃንን አልፈው ሸኖ ሲደርሱ ጀምሮ፣ በየቦታው ኬላ በፈጠሩ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይሎች የሚደርስባቸውን እንግልት ሰልችተው ሥራ እስከማቆም የደረሱበት አጋጣሚ መፈጠሩን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው አሽከርካሪዎች ጠቁመዋል። ‹‹የሚሰማን አጣን!›› የሚሉት አሽከርካሪዎቹ፤ መንገዱ ነጻ ሆኖ በነጻነት እንድንሠራ በተደጋጋሚ ከመንግሥት አልፈን ለሚዲያ ብንጮህም ሰሚ አጥተናል ይላሉ።

የዚህ ሁሉ ችግር መነሻ፣ መንግሥት ከሰሜን የኢትዮጵያ አካባቢ ተመሳስለው ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ የጸጥታ ስጋት የሚሆኑ ሰዎች እየገጠሙኝ ነው ብሎ የጀመረው መርጦ የማስገባትና የመመለስ አካሄድ ሲሆን፣ ቀስ በቀስ ወደ ብሔር አድጎ የአዲስ አበባ መታወቂያ የሌለው አያልፍም ከሚል ምክንያት በአደባባይ የአማራ መታወቂያ የያዘ ሰው ወደ አዲስ አበባ እንዳይገባ ተከልክሎ ከርሟል። ‹‹ሲፈልጉ ይመልሱናል፤ ሲፈልጉ ገንዘብም ይቀበላሉ” የሚሉት አሽከርካሪዎች፣ በረራ ያላቸው ሰዎች ፓስፖርት እያሳዩ እንዲመለሱ ሲገደዱ ነበር ይላሉ።

የዜጎች የመንቀሳቀስ መብት ከአንድ ወር በላይ ከተገደበ በኋላ ባለፈው ሐሙስ የደብረ ብርሃን አዲስ አበባ መንገድን አስተጓጉለዋል ተብለው በአሽከርካሪዎችና በተሳፋሪዎቻቸው በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲቀርብባቸው የነበሩት፣ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይሎች ከኬላዎች ተነስተው በፌዴራል ፖሊስ መተካታቸው ተሰምቷል። ይሁን እንጂ መንግሥት በርካታ ዜጎችን ለእንግልት እየዳረገ ስላለው ችግር በግለጽ የሰጠው አቅጣጫም ይሁን ማስተካከያ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ የለም።

ከደብር ብርሃን በቅርብ ርቀት ላይ ከምትገኘው ሸኖ ጀምሮ ሰንዳፋ እና ለገጣፎ ላይ ኬላ ላይ የተሰማሩ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይሎች በፌዴራል ፖሊስ እንዲተኩ ተወስኗል ከመባሉ ውጪ፣ ዜጎች ያለመገለል ወደ አዲስ አበባ መግባት ይችላሉ አይችሉም የሚለው ጉዳይ በውል ውሳኔ አላገኘም።

በዚህ ጉዳይ የተለያዩ አካላት ችግሩ የዜጎችን የመንቀሳቀስ መብት በጅምላ የመገደብ ጉዳይ መሆኑን በማንሳት ዜጎች የመንቀሳቀስ መብት እንዲከበር እየጠየቁ ነው። መንግሥት ስጋት ካለበት ስጋቱን በሕግና በስርዓት መከላከል እንጂ፣ በጅምላ ዜጎችን በማንነታቸው እየለየ የመንቀሳቀስ ነጻነት መብትን የመገደብ ሥልጣን የለውም።


ቅጽ 4 ቁጥር 197 ነሐሴ 7 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here