ከትራፊክ ቅጣት ከ361 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል

0
1461

በአዲስ አበባ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ361 ሚሊዮን ብር በላይ በትራፊክ ቅጣት ገቢ ማግኘት መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

ቢሮው ከትራፊክ ቅጣት ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት ያቀደ ቢሆንም፣ ማሳካት የቻለው ግን የእቅዱን 71 ነጥብ 3 በመቶ ብቻ እንደሆነ በ2014 ዓመታዊ ሪፖርቱ አሳውቋል።

መስመር በማቆራረጥ፣ መስመር ባለመሸፈን፣ ከታሪፍ በላይ በማስከፈል፣ ከመጠን በላይ በመጫን፣ ታፔላ ባለመስቀል፣ የታሪፍ ዝርዝር ባልሰቀለ፣ ተሳፋሪ በማጉላላት እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች የተነሳ በሁሉም የተሽከርካሪ ዓይነት የተፈጸሙ ጥፋቶች ከሰባት ሺሕ በላይ ሲሆኑ፣ ከዚህም ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሰበሰብ ተደርጓል ነው የተባለው።

ስለዚህም ቢሮው በበጀት ዓመቱ ከመደበኛ፣ ኮንትራትና ልዩ ትራንስፖርት አገልግሎት፣ ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ነዳጅ ሽያጭ አገልግሎት በመስጠት ትርፍ ለማስገኘት፣ ሸገር ብዙኀን ትራንስፖርት ለተለያዩ ተቋማት ኮንትራት አገልግሎት በመስጠት እና ከሌሎች የተለያዩ ዓይነት የገቢ ማግኛ መንገዶች ከ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ገልጿል። ከ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነው በአሽከርከሪ ተሽከርካሪ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት በኩል የተሰበሰበ ነው ተብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በበጀት ዓመቱ 19 ሺሕ በላይ ተሽከርካሪዎች ላይ ድንገተኛ የመንገድ ላይ ምርመራ የተከናወነ ሲሆን፣ ከዚህ መካከል ከስድስት ሺሕ በላይ ከባድ ጉድለት ያለባቸው ተቀጥተው የቴክኒክ ጉድለት አስተካክለው እንዲመጡ ተደርጓል። በዳግም ምርመራም ከአምስት ሺሕ የሚበልጡ ተሽከርካሪዎች ጉድለታቸውን ማስተካከላቸው ተረጋግጧል፡ ቀሪ ከ12 ሺሕ የሚልቁ ተሽከርካሪዎች የቴክኒክ ጉድለት ሳይገኝባቸው ምርመራውን በብቃት ያለፉ ናቸው ተብሏል።

የብዙኀን ትራንስፖርት አገልግሎትን በተመለከተም፣ አንበሳ እና ሸገር የብዙኀን ትራንስፖርት በአማካይ በየቀኑ ከ900 ሺሕ ሕዝብ በላይ ከቦታ ቦታ ማጓጓዛቸው የተገለጸ ሲሆን፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ድርሻቸው ከ39 በመቶ በላይ የደረሰ መሆኑ ተመላክቷል።

ቢሮው በበጀት ዓመቱ ያጋጠሙ ችግሮችንም ያስቀመጠ ሲሆን፣ ከእነዚህም አዲስ አደረጃጀት ተግባራዊ የሚደረግ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሥልጠናዎችን ለመስጠት መቸገር፣ ከተቋማት ጋር የጠነከረ የዘርፉ ቅንጂታዊ አሠራር አለመኖሩን እና በሕዝብ ትራንስፖርት የተሰማሩ አገልግሎት ሰጪ አካላት በተቀመጠው አሠራር መሠረት ያለመሥራት ችግሮችን ጠቅሷል።

እንዲሁም የአበዳሪ ድርጅቶች ግብአት እና ይሁንታ ለመስጠት ዳተኛ መሆን፣ የሰው ኃይልና የተሽከርካሪ እጥረት፣ ለመኪና ማቆሚያ፣ ለመጫኛና ማውረጃ ቦታ (ፌርማታ) ብሎም ለማሠልጠኛ ተቋማት ግንባታ ቦታ አለማግኘትና የተፈቀደው ቦታ ለሌላ አገልግሎት መዋላቸው ተጨማሪ ችግሮች እንደነበሩ ተገልጿል።

የዓለም ዐቀፍ ተቋማት ሠሌዳ አቅርቦት (ፌዴራል ፐብሊክ ትራንስፖርት )፣ የተግባር ፈተና ኮምፕሌክስ  ግብዓቶችን ማሟላት፣ የተገልጋይ ወረፋ መጠበቂያ ኪዮስክ ማሽን፣ የዓለም ዐቀፍ ሰሌዳዎች ሥያሜ (ፌዴራል) በእቅድ መሠረት ያልተፈቱ ችግሮች መሆናቸውም ተጠቅሷል።

በ2014፣ 34 ሺሕ 989 የአዲስ ተሽከርካሪ ምዝገባ የተከናወነ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 197 ነሐሴ 7 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here