ከ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ለሴቶች ተሰጥቷል

0
1141

በ2014 በጀት ዓመት ሴቶች ከ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ማግኘት መቻላቸውን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

በበጀት ዓመቱ ሴቶች ከስምንት ቢሊዮን ብር በላይ ብድር እንዲያገኙ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሴቶች ይህን ብድር እንዳገኙ ነው የተመላከተው። ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሴቶችም ከ3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ መቆጠብ እንደቻሉ ታውቋል።

ከክልልና ከተማ አስተዳደር እንዲሁም ከፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በበጀት ዓመቱ ከ830 ሺሕ በላይ ሴቶች በኅብረት ሥራ ማኅበራት በአባልነት እንዲታቀፉ ማድረግ መቻሉን ነገር ግን አፈፃፀሙ አነስተኛ እንደነበር ተመላክቷል።

አፈጻጸሙ ዝቅ ሊል የቻለበት ምክንያትም ሥራው በስፋት በሚሠራባቸው አካባቢዎች ማለትም በአማራና አፋር ክልሎች በነበረው የሰላም መደፍረስ ችግር ምክንያት ነው ተብሏል።

በገጠር የሚገኙ ሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንዲቻል የካዳስተር ልኬት ከ456 ሺሕ የሚልቁ ሴቶች የመሬት ባለቤትነት ማረጋገጫ ያገኙ ሲሆን፣ ይህም ከዕቅዱ አንጻር አፈጻጸሙ ዝቅተኛ ነበር ተብሏል።

አፈጻጸሙ ዝቅ ሊል የቻለበት ምክንያት፣ የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ተግባሩን ማከናወን ባለመቻሉ ሲሆን፣ በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል አዲስ መመሪያ እየወጣ ስለሆነ ለጊዜው ይቁም ስለተባለ በታቀደው ልክ መሠራት ባለመቻሉ መሆኑ ነው የተገለጸው።

ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሴቶችም በሙያና በጾታ አደረጃጀቶች የተደራጁ ሲሆን፣ ከ26 ሺሕ የሚበልጡ የሴቶች ልማት ቡድን ማቋቋም መቻሉም እንዲሁ ተመላክቷል።

በሌላ በኩል በበጀት ዓመቱ በሴቶች ዙሪያ በተከናወኑ ሥራዎች የብሔራዊ ወሲባዊ ጥቃት ወንጀል አድራሾች ብሔራዊ መረጃ ስርዓት (National Sex Offenders Registration System) ስርዓት ወደ ሥራ ለማስገባት ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከፍትህ ሚኒስቴር፣ ከማረሚያ ቤቶች አስተዳደርና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የአሠራር ማዕቀፍ መዘጋጀቱ ነው የተጠቆመው።

እንዲሁም በአገር ዐቀፍና በክልል ደረጃ ጥቃትን ለመከላከል ከኹለት ሺሕ በላይ ጸረ ጾታዊ ጥቃት አስወጋጅ ግብረ-ኃይል እንደተቋቋመም ተጠቅሷል።

በዚሁ ዓመትም ክልሎች በራሳቸው ባዘጋጁት ‹‹Verification tool›› ሰነድ መሠረት፣ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ 3 ሺሕ 141 ቀበሌዎች ከሴት ልጅ ግርዛት ነፃ መሆናቸው እንደተረጋገጠ ተገልጿል። በሚኒስቴሩ ዓመታዊ ሪፖርት የተካተተው ሌላው ጉዳይ፣ በበጀት ዓመቱ ከአንድ ሺሕ የማያንሱ የሕጻናት ፓርላማዎች ከክልል እስከ ቀበሌ እንደተደራጁና ከ800 ሺሕ የሚበልጡ ሕጻናት እንደተሳተፉ ነው።

የሴቶችን ውሳኔ ሰጪነትና ፖለቲካዊ ተሳትፎ በተመለከተም በተለይ በፌዴራል ደረጃ ከአጠቃላይ የፓርላማ መቀመጫዎች በሴቶች የተያዙ መቀመጫዎች ድርሻ 41 በመቶ መድረስ መቻሉንም ለማወቅ ተችሏል። ይሁን እንጂ ሌሎች ተግባራትንም ለማከናወን ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ያልተከናወኑ ዕቅዶች መኖራቸውን ተቋሙ ጠቅሷል።

በዚህም የሴቶች ልማት ፈንድ ለማቋቋም አንድ ዳሰሳ ጥናት ለማድረግ ታቅዶ፣ ጥናቱን ለማጥናት የሚያስችል የሀብት እጥረት በማጋጠሙ አልተከናወነም ነው ያለው። በተጨማሪም የወጣት አደረጃጀቶችን በተመለከተ ኹለት አገር ዐቀፍ ጥናት ለማድረግ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ በበጀት እጥረት የተነሳ ሊከናወን አለመቻሉን አመላክቷል።

በአገሪቱ የማኅበራዊ እሴቶች እየተሸረሸሩ መምጣትና በዚህም የጎዳና ተዳዳሪነት፣ የወጣት ሱሰኝነትና የማኅበራዊ ኑሮ ጠንቆች እየተባባሱ መምጣቱም እንደ ችግር ተነስቷል።

ማኅበረሰቡ ለሴቶችና አካል ጉዳተኞች ያለው አመለካከት ዝቅተኛ ከመሆኑ ባሻገር፣ በየክልሉ የሴክተሩ አደረጃጀት ወጥ አለመሆንና የሚበጀትለት በጀት ዝቅተኛ መሆን የተጣለበትን ተግባርና ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት እንዳላስቻለው ተገልጿል።


ቅጽ 4 ቁጥር 197 ነሐሴ 7 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here