በሰቆጣ ከተማ በኤሌክትሪክ እጦት በቀን 300 ሕሙማን የሕክምና አገልግሎት ያጣሉ ተባለ

0
1144

በሰቆጣ ከተማ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለመኖሩ በነዳጅ እጥረት በቀን 300 የሚደርሱ ሰዎች የሕክምና አገልግሎት ፈልገው ማግኘት እንደማይችሉ በሰቆጣ ከተማ የሚገኘው የተፈራ ኃይሉ መታሰቢያ ሆስፒታል ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

በአማራ ክልል በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሰቆጣ ከተማ የተፈራ ኃይሉ መታሰቢያ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ፋሲካ ንጋቴ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በከተማዋና በአጎራባች አካባቢዎች በሰሜኑ ጦርነት ወቅት በደረሰው ጉዳት ሳቢያ እስካሁን ባለው ጊዜ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለመኖሩ ጀነሬተሩን ነዳጅ በመሙላት ለመጠቀም መገደዳቸውን ጠቁመዋል።

በአሁን ወቅት በሰቆጣ ከተማ ከ45 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች እና ከ85 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ እና ለእነዚህ ተፈናቃይ ዜጎች ባለፉት ስምንት ወራት የተፈራ ኃይሉ መታሰቢያ ሆስፒታል የነጻ አገልግሎት እየሰጠ ነበር። ሆኖም በበጀት እና በነዳጅ እጥረት ምክንያት ከባለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ የሕክምና አገልግሎት የማይሰጡባቸው ቀናት እንዳሉ ሥራ አስኪያጁ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በዚህም ሳቢያ ሆስፒታሉ በሳምንት ከአንድ እስከ ኹለት ቀን ለሰዓታት የሚሆን ጊዜ በሚቋረጥበት ወቅት የሕክምና አገልግሎት የማይሰጥበት ወቅት እንዳለ ተገልጿል። በዚህም በመደበኛነት ተኝተው ከሚታከሙት ሕሙማን በተጨማሪ 30 የሚሆኑ ካለ እድሜያቸው የተወለዱ እና ማሞቂያ የሚያስፈልጋቸው ሕጻናት እንዲሁም 300 የሚጠጉ ተመላላሽ ታካሚዎች የሕክምና አገልግሎት የማያገኙበት ሁኔታ እንዳለም ተናግረዋል።

በተጨማሪ በፍሪጅ እና በበረዶ ውስጥ የሚቀመጡ መድኃኒቶችም እየተበላሹ እና ከአገልግሎት ውጪ እየሆኑ መሆናቸውን ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።

በሰቆጣ ከተማ የሚገኘው የተፈራ ኃይሉ መታሰቢያ ሆስፒታል የውስጥ ገቢን በመሰብሰብ የመድኃኒት እና የሕክምና ቁሳቁሶችን ማሟላት የመጀመሪያ ሥራው ቢሆንም፣ በየወቅቱ ለአገልግሎት የሚያግዝ ነዳጅ ለመግዛት ከፍተኛ ወጪ እንዲያወጣ እየተገደደ ነው ተብሏል።

ባለፉት ስምንት ወራት ሆስፒታሉ ከሰቆጣ ከተማ አስተዳደር በኩል በሚጠይቀው ልክ ባይሆንም የነዳጅ ድጋፍ እየተደረገለት እንደነበር እና በተቋሙም በኩል የነዳጅ ግዥ በመጠቀም አገልግሎት እየሰጠ ነበር ተብሏል።

አሁን ላይ ሆስፒታሉ ከአቅሙ በላይ እንደሆነ እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩም ጭምር በበጀት እጥረት ምክንያት እየተፈተነ በመሆኑ ከአቅሙ በላይ መሆኑን እየገለጹ ይገኛሉ።

ሥራ አስኪያጁ አክለውም፣ መረጃውን ለአዲስ ማለዳ እስካረጋገጡበት ወቅት ድረስ ስጋቱ እንዳለ እና በቀጣይ ሙሉ ለሙሉ አገልግሎቱ ሊቆም የሚችልበት ሂደት በመኖሩ መንግሥትም ሆነ የተለያዩ የተራድኦ ድርጅቶች የበጀት እንዲሁም የነዳጅ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በተጨማሪ መንግሥት ከተማዋ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የምታገኝበትን ሂደት በማመቻቸት እንዲሠራ ጠቁመዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በተመሳሳይ ባለፉት ስምንት ወራት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለመኖሩ እና ነዳጅ ገዝቶ በጀነሬተር መጠቀም ባለመቻሉ በትምህርት ተቋማትም ላይ ተፅእኖ ማሳደሩን የጠቆመው የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር ነው።

ለአብነትም በሰቆጣ ከተማ የሚገኘው መምህራን ኮሌጅ እና የሙያ እና ቴክኒክ ኮሌጂ የተግባር ትምህርት ለተማሪዎቻቸው ለመስጠት ተቸግረው እንደነበር ተነግሯል።

ችግሩን ተረድተው የሚመለከታቸው አካላት እርዳታ እንዲያደርጉ እና ችግሩ ወደ ቀጣይ 2015 እንዳይቀጥል ርብርብ እንዲደረግ የከተማ አስተዳደሩ ጠቁሟል።


ቅጽ 4 ቁጥር 197 ነሐሴ 7 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here