የኢትዮጵያን የሳይበር ደኅንነትን ለማስጠበቅ የሚያስችል ምርምር ለማካሄድ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር እና ስምንት የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስምምነት መፈራረማቸው ተመላከተ። ተግባራዊ ሆኗል የተባለው ስምምነቱ ፊርማ ብቻ ሳይሆን ወደፊት የአገርን የሳይበር ደኅንነት ለማስጠበቅም ጭምር ነው ተብሏል። ከዚህም በተጨማሪ ትውልዱን በዘርፉ ለመቅረፅ እና ለመሥራት እድል የሚፈጥር መሆኑ ተዘግቧል።
የምርምር ማካሄድ ስምምነቱ በአገር ጉዳይ ላይ የሚፈጠሩ የሳይበር ደኅንነት ችግሮችን በጋራ ከመፍታት አኳያ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫዎት ነው የተመላከተው። ስምምነቱን የተፈራረሙት ዩኒቨርሲቲዎችም ስምንት ሲሆኑ፣ እነሱም ጎንደር፣ ሀዋሳ፣ አርባምንጭ፤ ባሕርዳር፤ ሐረማያ፤ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፤ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የመከላከያ ዩኒቨርሲቲዎች መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል። በመሆኑም ስምምነቱ በአቅም ግንባታና ተሰጥኦ ልማት ዙሪያ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ስለመሆኑ ነው የተነገረው።
ቅጽ 4 ቁጥር 197 ነሐሴ 7 2014



