0
815

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አጠቃላይ የደንበኞቹ ቁጥር 4 ሚሊዮን 304 ሺሕ በላይ መድረሱን አስታወቀ

👉በበጀት ዓመቱ በ1 ሺሕ 50 የተቋሙ አመራር እና ሠራተኞች ላይ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች ተወስደዋል

ሐሙስ ነሐሴ 12 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አጠቃላይ የደንበኞቹ ቁጥር 4 ሚሊዮን 304 ሺሕ 942 መድረሱን አስታወቋል።

ተቋሙ የ2014 በጀት ዓመት የግብ አፈፃፀም እና 2015 በጀት ዓመት ዕቅድ አሰመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫውም ተቋሙ በ2014 በጀት ዓመት የትግራይ ክልልን ጨምሮ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ፤ 367 ሺህ 466 ደንበኞችን በማገናኘት የዕቅዱን 32 ነጥብ 84 በመቶ አፈፃፀም ማስመዝገቡን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሽፈራው ተሊላ ተናግረዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ የተቋሙ አጠቃላይ የደንበኛ ቁጥር 4 ሚሊዮን 304 ሺሕ 942 መድረሱን ነው ዋና ሥራ አስፈፃሚው የገለጹት።

ተቋሙ ደንበኞቹን በቅርበት ለማገልገል የአደረጃጀት ማሻሻያ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን የተናገሩት ሽፈራው፤ በተገባደደው በጀት ዓመት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል እና የሲዳማ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ፅ/ቤቶች በማቋቋም የተቋሙ አጠቃላይ ሪጅኖች ወደ 13 ከፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

በዚህም ተቋሙ በአሁን ወቅት 13 ሪጅኖች፣ 26 ዲስትሪክቶች፣ 554 የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት እና ከ5 ሺሕ 838 በላይ ሳተላይቶችን አደራጅቶ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ከማሳደግ አንጻርም፤ 425 አዳዲስ የገጠር ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ ታቅዶ 204 ከተሞችን ተጠቃሚ በማድረግ የእቅዱን 48 በመቶ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።

የተቋሙን ገቢ ከማሳደግ አንጻር ደግሞ ከኢነርጂ ሽያጭ ለመሰብሰብ ከታቀደው 23 ነጥብ 84 ቢሊየን ብር ውስጥ፤ 20 ነጥብ 94 ቢሊየን ብር በመሰብሰብ 88 በመቶ አፈጻጸም አስመዝግቧል ብለዋል፡፡

አገልግሎቱ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኪ.ዋ. ሰዓት ከ8 ቢሊየን በላይ እና የፓወር አቅርቦት በኪ.ዋ 21 ሚሊየን በላይ ኃይል ገዝቶ፤ ለዚህም አቅርቦት ከ9 ቢሊየን 926 ሚሊየን ብር በላይ ክፍያ መፈጸሙንም ሽፈራው ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ተቋሙ ከአዲስ ደንበኞች የኤሌክትሪክ መስመር ማስቀጠያ 6 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ከአሮጌ ንብረት ሽያጭ 113 ነጥብ 13 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ገልጸዋል።

ተቋሙ የተጠያቂነት ስርዓትን ለማስፊን በሰራው ሥራ ከባለድርሻ አካላት በተሰጡ 145 ጥቆማዎች 221 አመራርና ሠራተኞች ላይ ማጣራት ተካሂዶ፤ በ120ዎቹ ላይ አስተዳደራዊ እርምጃዎች የተወሰደ ሲሆን፤ ቀሪ 101 የሚሆነት ደግሞ በተቋሙ የዲሲፕሊን ኮሚቴ በመታየት ላይ መሆናቸውን ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ከደንበኞች የመጣውን ጥቆማ ጨምሮ ተቋሙ ያስቀመጠውን የውስጥ አሰራርና ሥርዓት ያላከበሩ እና የሥነ-ምግባር ጥሰት በፈጸሙ፤ በድምሩ 1 ሺሕ 50 የተቋሙ አመራር እና ሠራተኞች ላይ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች ተወስደዋል ብለዋል።

እርምጃዎቹም 27 የቃል ማስጠንቀቂያ፣ 356 የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ 568 የደሞዝ/ገንዘብ/ ቅጣት 24 ከታ ማንሳት እንዲሁም 75 የሥንብት እርምጃዎች መሆናቸውን ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የገንዘብ መጠናቸው 100 ሚሊየን 601 ሺሕ 952 ብር የሆነ 81 የፍትሃብሄር ክሶችን መመስረቱን የተናገሩት ሽፈራው፤ ከእነዚህ ወስጥ 28 መዝገቦች ሙሉ በሙሉ ለተቋሙ የተወሰነ ሲሆን፤ በዚህም 12 ሚሊየን 559 ሺሕ 688 ብር ለተቋሙ ገቢ መደረጉን አመላክተዋል።

የኢሌክትሪክ መሰረተ ልማትና ሃይል ሥርቆት ጋር በተያያዘም 759 የወንጀል ክሶችን ሲከታተል መቆየቱንና በእነዚህ የወንል ድርጊቶች ተቋሙ ላይ 130 ሚሊየን 984 ሺሕ 279 ብር ኪሳራ መድረሱን ገልጸዋል፡፡

ይህን ተከትሎ በ36 መዝገቦች ላይ ፍርድ ቤት ባስተላለፈው የመጨረሻ ዉሳኔ በ64 ተከሳሾች ላይ ከ6 ወር እስከ 12
ዓመት ጽነ እስራት ተወስኖባቸዋል፡፡

ድርጊቱን የፈፀሙት በኦሮሚያ ክልል 22 ግሰለቦች፤ ከ6 ወራት እስከ 9 ዓመት፣ በደቡብ ክልል 25 ግለሰቦች ከ2 ዓመት እስከ 12 ዓመት እንዲሁም በአዲስ አበባ 17 ግለሰቦች ከ6 ወራት እስከ 7 ዓመት ጽኑ እስራት ተፈርዶባቸዋል ብለዋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here