ሐሙስ ነሐሴ 12 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በደብረታቦር ከተማ የሚካሄደው <ደብረታቦርን በደብረታቦር> የተሰኘ የቡሄ በዓል አከባበር ለአራተኛ ጊዜ በድምቀት ተጀምሯል።
አከባበሩን እና ዝግጅቱን በሚመለከት ለመገናኛ ብዙኀን መግለጫ የሰጡት የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አነጋግረኝ ጋሻው (ዶ/ር)፣ ዝግጅቱ የአካባቢውን ባህል ትውፊትና ታሪክ እንዲሰነድ ለማስቻል ዩኒቨርሲቲው ከሚሠራቸው ሥራዎች ጋር በተያያዘ እንዲከበር የተወሰነ መሆኑን አውስተዋል።
<<ትውፊቶቻችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተረሱና እየጠፉ እንዲሁም በውጪ ባህል እየተወረሩ መሆኑ ይታያል። የቡሄ አከባበርም እንደዛው እየተመናመነ ነው። ባህላዊም ሆነ ሃይማኖታዊ ትውፊት ያለው በዓል ስለሆነ እንደገና መታየት አለበት ተብሎ ታምኗል።>> ብለዋል።
ባለፈው ዓመት በዚህ ወቅት አካባቢው ጦርነት ላይ እንደነበር ያስታወሱት ፕሬዝዳንቱ፤ <<ዘንድሮ ያ ሁሉ አልፎ በሕይወት ቆይተን ለዚህ ደርሰናል። ደብረታቦር ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ ዋና አካባቢ ነበር። አገርን በማትረፍ በኩል ትልቅ ሚኒ የተጫወተ አካባቢ ነው።>> ብለዋል። በነበረው አለመረጋጋትና ጦርነት የተነሳም በዓሉ ባለፈው ዓመት ሳይከበር እንደቀረም አስታውሰዋል።
ይህን ሀይማኖታዊ ብቻ ሳይሆን ባህላዊ እሴቶች ያሉትን በዓል የማክበር ዝግጅት በፌስቲቫልነት የማስቀጠል እቅድ እንዳለም በመግለጫው ተጠቅሷል።
ዩኒቨርሲቲው የአካባቢው ባህል እንዲጠበቅ ብሎም እንዲያድግ መሥራትም ድርሻው ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ባህላዊ ትውፊቶችን ለልማት ማዋል፣ በቱሪዝሙ ላይ ድርሻ እንዲኖራቸው ለማድረግና የኢኮኖሚ ጥቅም ለማግኘት እንደሚረዳ እንደሚታመን ጠቅሰዋል። ይህም <ደብረ ታቦርን በደብረ ታቦር> ዝግጅት ዓመታዊና የሚጠበቅ ፌስቲቫል ለማድረግ በትጋት የሚሠራ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
ደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ከ15 ሺሕ በላይ ተማሪዎችን የሚያስተምር ሲሆን፤ ከተመሠረተ 10 ዓመታትን አስቆጥሯል።
በቴክኖሎጂ ዘርፍ በትኩረት የሚሠራው ተቋሙ፣ በቅርቡም በተማሪዎችና መምህራን የተሠራ ሮኬት ማምጠቁ የሚታወስ ነው። <<ይህ የልጆች ሕልም መቀጠል አለበት። ለኢትዮጵያ ኩራት የሚሆኑ ውጤቶች ይገኙበታል>> ሲሉ አነጋግረኝ ተናግረዋል።
በዓሉ ዛሬ (ነሐሴ 12/2014) በአውደ ጥናት የሚጀምር ሲሆን፣ ነገ ረፋድ ጀምሮ በዓሉ በድምቀት እንደሚከበር ይጠበቃል።



