1- የመስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር የሆኑት ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ታላቁ የህዳሴ ግድብ የማመንጨት ኃይል ከ6 ሺሕ 500 ሜጋ ዋት ወደ 5 ሺሕ 150 ሜጋ ዋት እንዲቀነስ መደረጉን አምነዋል። ይህንን የተናገሩት ዛሬ ለሚኒስትሮች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ሲሆን በተርባይን ቅነሳው ላይ የግብፅ ፕሮፖዛል ጥቅም ላይ ውሏል የሚለው ሀሳብ መሰረተ ቢስ መሆኑን ተናግረዋል። በሌላ በኩል ግድቡ የኢትዮጵያ የኃይል ፍላጎትን ከመሙላት ባሻገር ለዓሳ ሀብት ልማትና ለቱሪዝም እድገትም ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለዉ ገልጸዋል። (ዋልታ)
…………………………………………………………
2- መንግስት በቅርቡ በከፊል ወደ ግል ከሚዛወሩ እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ያሉ ቁልፍ ኢንተርፕራይዞች የሚያገኘውን ገቢ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ልማት ባንክ የወሰደው ብድር ለመከፈል ሊጠቀምበት እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል። በተጨማሪ የሚገኘው ገቢ የሁለቱን ተቋማት ካፒታል ለማሳደግ መንግስት ሊጠቀምበት እንደሚችል የብሔራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ ተናግረዋል። (ብሉምበርግ)
…………………………………………………………
3-የሐረሪ ክልል ምክር ቤት የካቢኔ ወንበርም ከ10 ወደ 14 በአዲሱ የሥልጣን ክፍፍልም የሀርሪ ብሄራዊ ሊግና የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እኩል ስባት፣ ስባት ወንበር ይኖራቸዋል ተብሏል። ክልሉም ከ3 ወራት ገደማ መጓተት በኋላ አመታዊ በጀቱን አፅድቋል። (ቪኦኤ)
…………………………………………………………
4-በአፋር ክልል በአፋምቦ ወረዳ በኦብኖ ቀበሌ በሚኖሩ ንፁሃን አርብቶ አደር ሴቶች፣ ህፃናትና አዛውንቶች ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ ሰመራና አዋሽ ሰባት ኪሎ ነዋሪዎች ዛሬ ጥቅምት 6/2012 ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል። ሰልፈኞቹ መንግሥት ጣልቃ በመግባት ዜጎቹን የመጠበቅና በእነርሱ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት የመከላከል ግዴታውን ሊወጣ እንደሚገባ ገልጸዋል። (ኢቢሲ)
…………………………………………………………
5- በአዲስ አበባ ከተማ ዉስጥ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ከመኪና ውስጥ ሰርቀው ለማምለጥ ሙከራ ያደረጉ ሦስት ተጠርጣሪዎች በኅብረተሰቡ እና በፖሊስ የተቀናጀ ሥራ መያዛቸዉን አዲስ አበባ ፖሊስ አስታዉቋል። ጥቅምት 4/2012 የግል ተበዳይ የሆኑት ሚስተር ፒን ላፊ ላንግ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ከሚገኘው አዋሽ ባንክ ቅርንጫፍ ከ1.2 ሚሊዮን ብር በላይ አውጥተው በኮድ 2 B 23934 አዲስ አበባ ቪትዝ መኪና ዉስጥ ገንዘቡን አስቀምጠው ለምሳ ወደ ሆቴል ሲገቡ እንደሆነ ገልጸዋል። (አዲስ ማለዳ)
…………………………………………………………
6- በያዝነው በጀት ዓመት 152 የመንግሥት አገልግሎቶች በኤሌክትሮኒክስ እንዲሰጡ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታውቋል። በብሔራዊ የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት መተግበሪያ ፕሮጀክት መሰረት፤ እስከ አሁን 126 የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎቶች በ34 ተቋማት ወደ ትግበራ ገብተዋል። (አዲስ ማለዳ)
…………………………………………………………
7-የአማራ ክልል ደኅንነትና የጸጥታ ምክር ቤት በማዕከላዊ እና በምዕራብ ጎንደር ዞኖች የተፈጠረውን ግጭት ለማረጋጋትና አካባቢውን ወደ ቀደመው ሰላም ለመመለስ የክልሉ መንግሥት ለፌዴራል መንግሥት ጥያቄ ማቅረቡን አስታውቋል። በጥያቄው መሰረት የፌዴራል የፀጥታ ኃይል መከላከያን ጨምሮ ማንኛውንም ሕጋዊ እርምጃ ወስዶ ቀጠናውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተሟላ ሰላም እና መረጋጋት እንዲያሸጋግር መመሪያ መተላለፉን ምክር ቤቱ አስታወቋል። (ቪኦኤ)
…………………………………………………………
8-በአዲስ አበባ ከሚገኙ 121 ወረዳዎች 62ቱ የዲጂታል መታወቂያ እየሰጡ መሆናቸውን የከተማው ወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ አስታውቋል። በዋናነት በቦሌ፣ ጉለሌ፣ ኮልፌ፣ ንፋስ ስልክ እና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች በተሻለ ደረጃ አገልግሎቱ የሚሰጥ ሲሆን ከሐምሌ 15/2011 ጀምሮ 44 ሺሕ የዲጂታል መታወቂያዎች ለኅብረተሰቡ መስጠት መቻሉ ተገልጿል። (ኢቢሲ)



