“ለምን ከሥራ ቦታዬ እቀየራለሁ?” በሚል ምክንያት የቅርብ አለቃውን በክላሽ ተኩሶ የገደለው የፌዴራል ፖሊስ በእስራት ተቀጣ

0
1020

አርብ ነሐሴ 13 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) “ለምን ከሥራ ቦታዬ እቀየራለሁ?” በሚል ምክንያት የቅርብ አለቃውን በክላሽ ተኩሶ የገደለው የፌዴራል ፖሊስ በእስራት መቀጣቱ ተገለጸ።

ተከሳሽ ረ/ሳጅን ከበደ ባይሳ ሀምሌ 29 ቀን 2011 ከቀኑ 06፡00 ሰዓት ሲሆን፤ በአራዳ ክ/ከተማ ወረዳ 01 ክልል ልዩ ቦታው ማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ግቢ ውስጥ እሱ እና ሦስት የሥራ ባልደረቦቹ ከሚሰሩበት ማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ወደ ጃንሜዳ ካምፕ እንደተዘዋወሩ ሲነገራቸው፤ ተከሳሽ “ለምን ከሥራ ቦታዬ እቀየራለሁ?” በማለት የቅርብ አለቃዉ የሆነውን ዋ/ሳጅን ፈይሳ ከድርን ለሥራ በተሰጠው ክላሽ መሳሪያ ጀርባዉን እና እግሩን ኹለት ጊዜ ተኩሶ በመምታት ህይወቱ እንዲያልፍ ማድረጉ ተገልጿል።

በዚህም በ1996 የወጣውን የኢፌዲሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 539/1/ሀ በመተላለፍ በፈፀመው ከባድ የሆነ የሰው ግድያ ወንጀል እንዲሁም፤ ተከሳሽ የተኮሰው ጥይት በሟች ፈይሳ ከድር ሰውነት ውስጥ አልፎ በመውጣት በቅርበት ላይ የነበረውን ሟች ረ/ሳጅን ታሪኩ ተመስገንን የቀኝ ደረቱን በመምታት ህይወቱ እንዲያልፍ ያደረገ በመሆኑ፤ የኢፌዲሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 58/1/ለ እና 540 በመተላለፍ በፈፀመው የሰው መግደል ወንጀል አጠቃላይ 2 ክሶች በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ መስርቶበታል፡፡

ተከሳሹ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ከባድ ውንብድና እና ግድያ ወንጀል ችሎት ቀርቦ የእምነት ክህደት ቃሉን ሲጠየቅ ድርጊቱን አልፈፀምኩም በማለቱ፤ ዐቃቤ ህግ ያሰባሰባቸውን የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን በማቅረብ አስረድቷል።

ተከሳሽም 2 መከላከያ ምስክሮችን አቅርቦ ያሰማ ቢሆንም የዐቃቤ ህግን ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻላቸው ፍ/ቤቱ ተከሳሹ በኹለቱም ክስ ጥፋተኛ ነው በማለት፤ ነሐሴ 11 ቀን 2014 በዋለው ችሎት ተከሳሹ በ12 ዓመት ጽኑ እስራት እና ለ3 ዓመት ከህዝባዊ መብቶቹ እንዲታገድ ሲል ወስኖበታል፡፡

ዐቃቤ ሕግ ፍርድ ቤት በሰጠው የቅጣት ውሳኔ ላይ ይግባኝ ለመጠየቅ የውሳኔ ግልባጭ ጠይቆ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ ከፍትሕ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here