አርብ ነሐሴ 13 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የጤና ሚኒስቴር 100 ሺሕ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ነጻ የጤና ምርመራና የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታውቋል።
አገልግሎቱ “በጎነት ለጤናችን” በሚል መሪ ቃል ከነሐሴ 16 እስከ 21 ቀን 2014 ድረስ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች በበጎ ፈቃደኛ የጤና ባለሙያዎች እንደሚሰጥ ገልጿል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አገልግሎቱን አስመልክቶ በሚኒስቴሩ ቅጥር ግቢ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ለስድስት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው የበጎ ፈቃድ ሥራ አቅመ ደካማ ለሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችና ለጎዳና ተዳዳሪዎች የተለያዩ የሕክምና አገልግሎት እንደሚሰጣቸው ሚኒስትሯ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ከሚሰጡ የጤና ምርመራዎች ውስጥ የስኳር ህመም፣ የደም ግፊት፣ የአይን ሕመም ሕክምና እንዲሁም ሌሎች ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ይገኙበታል ተብሏል።
ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን አስመልክቶ ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እንደሚከናወንም ዶክተር ሊያ ገልጸዋል።



