ተቋሙ በ2014 በጀት ዓመት የትግራይ ክልልን ጨምሮ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ፤ 367 ሺሕ 466 ደንበኞችን በማገናኘት የእቅዱን 32 ነጥብ 84 በመቶ አፈፃፀም ማስመዝገቡን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሽፈራው ተሊላ ተናግረዋል።
ተቋሙ ደንበኞቹን በቅርበት ለማገልገል የአደረጃጀት ማሻሻያ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን የተናገሩት ሽፈራው፤ በተገባደደው በጀት ዓመት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል እና የሲዳማ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ፅሕፈት ቤቶች በማቋቋም የተቋሙ አጠቃላይ ሪጅኖች ወደ 13 ከፍ ማድረጉን ተናግረዋል። በዚህም ተቋሙ በአሁን ወቅት 13 ሪጅኖች፣ 26 ዲስትሪክቶች፣ 554 የአገልግሎት መስጫ ማእከላት እና ከ5 ሺሕ 838 በላይ ሳተላይቶችን አደራጅቶ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ከማሳደግ አንጻርም 425 አዳዲስ የገጠር ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ ታቅዶ 204 ከተሞችን ተጠቃሚ በማድረግ የእቅዱን 48 በመቶ ማሳካት ተችሏል ብለዋል። የተቋሙን ገቢ ከማሳደግ አንጻር ደግሞ ከኢነርጂ ሽያጭ ለመሰብሰብ ከታቀደው 23 ነጥብ 84 ቢሊዮን ብር ውስጥ፤ 20 ነጥብ 94 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ 88 በመቶ አፈጻጸም አስመዝግቧል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ተቋሙ ከአዲስ ደንበኞች የኤሌክትሪክ መስመር ማስቀጠያ 6 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ከአሮጌ ንብረት ሽያጭ 113 ነጥብ 13 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ገልጸዋል።
ተቋሙ የተጠያቂነት ስርዓትን ለማስፈን በሠራው ሥራ ከባለድርሻ አካላት በተሰጡ 145 ጥቆማዎች 221 አመራርና ሠራተኞች ላይ ማጣራት ተካሂዶ፤ በ120ዎቹ ላይ አስተዳደራዊ እርምጃዎች የተወሰደ ሲሆን፤ ቀሪ 101 የሚሆነት ደግሞ በተቋሙ የዲሲፕሊን ኮሚቴ በመታየት ላይ መሆናቸውን ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።
በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ከደንበኞች የመጣውን ጥቆማ ጨምሮ ተቋሙ ያስቀመጠውን የውስጥ አሠራርና ስርዓት ያላከበሩ እና የሥነ-ምግባር ጥሰት በፈጸሙ፤ በድምሩ 1 ሺሕ 50 የተቋሙ አመራር እና ሠራተኞች ላይ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች ተወስደዋል ብለዋል። እርምጃዎቹም 27 የቃል ማስጠንቀቂያ፣ 356 የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ 568 የደሞዝ/ገንዘብ/ ቅጣት 24 ከቦታ ማንሳት እንዲሁም 75 የስንብት እርምጃዎች መሆናቸውን ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 198 ነሐሴ 14 2014


