መነሻ ገጽዜናወፍ በረር ዜናበ2014 በጀት ዓመት የኦሮሚያ ክልል ከወርቅ ሽያጭ ከ314 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ...

በ2014 በጀት ዓመት የኦሮሚያ ክልል ከወርቅ ሽያጭ ከ314 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

የኦሮሚያ ክልል የማዕድን ልማት ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተስፋዬ መገርሳ፣ ክልሉ በዘንድሮ በጀት ዓመት 4 ሺሕ 316 ኪሎ ግራም ወርቅ ለማእከላዊ ገበያ እንዲሁም ለሲሚንቶ ምርት ግብዓት የሚሆን 461 ሺሕ ቶን የከሰል ድንጋይ ለስሚንቶ ፋብሪካዎች ማቅረቡን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ መልኩ በአዲስ አበባ ለሚከናወኑ ግንባታዎች ከ22 ሚሊዮን ቶን በላይ የጠጠር ድንጋይ ማቅረባቸውን የተናገሩት ኃላፊው፣ በሥራ እድል አኳያም በዘርፉ ለ129 ሺሕ ሰዎች የሥራ እድል መፈጠሩን አንስተዋል።

በክልሉ በርካታ ማዕድናት ቢኖሩም እስካሁን በተደረገው መለስተኛ ጥናት 48 የተለያዩ ማዕድናት ተለይተዋል። ከዚህም ባሻገር ያሉትን በርካታ ማዕድናት በጥናት ለመለየትና በተገቢዉ ሁኔታ ለአገር እድገት ለማዋል ባለሥልጣኑ ሰፊ እንቅስቃሴ ላይ ነው ብለዋል። ለዚህም ሲባል እስካሁን ያልነበረ መመሪያና ደንብ በማዘጋጀት ማዕድን ለማውጣት ፈቃድ የተሰጣቸው ሰዎች ብቻ በሥራው እንዲሳተፉና ማዕድናቱም ተገቢውን ገቢ እንዲያመነጩ እየተሠራ መሆኑ ተነግሯል።

ከዚህ አንጻር ባለሥልጣኑ ከተቀመጠው መመሪያ ውጪ የሚንቀሳቀሱ 48 የሚሆኑ ግለሰቦችና ድርጅቶች የሥራ ፍቃድ መሰረዙን ያነሱት ተስፋዬ፣ በሌላ በኩል በየአካባቢው ተደራጅተው መመሪያውን በማክበር ለሚሠሩ በተለይ በወርቅ ማዕድናት ላይ ለተሰማሩ ማኅበራት ወርቅን የሚያጥቡ ስምንት ዘመናዊ ማሽኖች ማቅረባቸውን አስታውቀዋል።

ከዚህ በፊት ማዕድናቱን አውጥተው ከመጠቀም ውጪ ለአካባቢ እንክብካቤና ለሰዎች ደኅንነት እምብዛም ትኩረት ስለማይሰጥ ዘርፉ ከሚያደርሰው ጉዳት የተነሳ በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ እንደነበር ያወሱት ኃላፊው፣ አሁን ግን የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ ለኅብረተሰብ ልማት ፈንድና አካባቢውን መልሶ ለማልማት የሚውል ከማዕድናቱ ከሚገኘው ገቢ አራት በመቶ ለአካባቢው ኅብረተሰብ እንደሚከፈል ተናግረዋል።

ሆናም ግን በክልሉ ከተፈጠረው የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ማዕድን የማውጣት ሥራ ላይ ተፅእኖ መፈጠሩንና በአንዳንድ የክልሉ ዞኖች ታጣቂዎች ማዕድናቱን በመዝረፍ ለጦር መሣሪያ መግዣ እንደሚጠቀሙ ጠቁመዋል። በተለይ በጉጂ አካባቢ በጸጥታ ችግር ምክንያት ወርቅ ወደ ማዕከላዊ ገበያ ሳይመጣ በኬንያና በሱማሊያ በኩል ወደውጭ ሲወጣ መቆየቱን አንስተዋል።

ከሕገወጥ ንግድ ጋር ተያይዞ በሕገ ወጥ ንግድ ላይ በመሰማራት መንግሥትና ሕዝብ ማግኘት የነበረባቸውን ገቢ ያሳጡት 20 የውጭ አገር ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ ለኢኮኖሚ እድገቱ ተመራጭ እየሆነ የመጣውን የማዕድን ዘርፍ ከሕገ ወጥ ንግድና ከታጣቂዎች ዘረፋ ለመታደግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።


ቅጽ 4 ቁጥር 198 ነሐሴ 14 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች