ካንሰርና አንበጦች

0
1202

ካንሰር አግባብ ባልሆነ የህዋሶች እድገትና መራባት የሚመጣ ገዳይ በሽታ መሆኑ ይታወቃል። ከዓመት ዓመት በካንሰር ተይዘው የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱን ተከትሎ ሕክምናውን ለመስጠት የሚያስችሉ ምርምሮችም አብረው እየተካሄዱ ይገኛል።

ምንም ሕክምና የሌለው በሽታ ከመባል ተነስቶ፣ በተወሰነ ደረጃ ሳይስፋፋ በፊት በሽተኛው እንዲያገግም የሚያደርጉ የተለያዩ ዓይነት ሕክምናዎች ተግባራዊ ሲደረጉም ቆይተዋል። ኬሞ ቴራፒን የመሳሰሉ ጊዜ የሚወስዱ የሕክምና መንገዶችን ጨምሮ፣ የተለያዩ ዘዴዎች አሉ እየተባለ አማራጭ ላጡ ሕመምተኞች አሁንም ድረስ እየተሰጠ ያለ የሕክምና ዘዴ ብዙ ነው።

ሕክምናው ውጤታማ እንዲሆን ከሚያስችሉ ጉዳዮች መካከል ካንሰር የተከሰተበትን ሕዋስ በጊዜ ለይቶ ማወቅ ወሳኙ የሕክምናው ሂደት መሆኑ ይነገራል። ለዚህም ሲባል በአንዳንድ የሰውነት ክፍሎች ላይ የሚከሰተውን እጢ ለመለየት ሰዎች ቢያንስ ሰውነታቸውን በየጊዜው እያስተዋሉ ለውጥ በሚያጋጥማቸው ወቅት በባለሙያ እንዲመረመሩ ይመከራሉ።

ካንሰሩ እንደሚከሰትበት የሰውነት አካባቢ የማወቂያ መንገዱም ሊለያይ ቢችልም፣ ተመራማሪዎች አሁንም ቢሆን ቀላልና ገና ከመነሻው ሊያሳውቅ የሚችል የመመርመሪያ መንገድን ለማወቅ እየሠሩ ይገኛሉ። ከምርምራቸው መካከል ዘመናዊ መሣሪያን እና ተፈጥሮን በቅንጅት ተጠቅመው በሽታውን ገና ከመነሻው ለማወቅ የሚያስችላቸውን መንገድ ሲሞክሩም ኖረዋል። የዚህ ምርምራቸው አካል የሆነ ውጤት ደግሞ ከሰሞኑ ማግኘታቸውን ይፋ አድርገዋል።

ቅጠል ወዳለበት በመንጋ እየተንቀሳቀሰ ሰብልንም ሆነ እፅዋትን የሚያወድመው አንበጣ በተፈጥሮው የማሽተት አቅሙ ከፍተኛ መሆኑን ያስተዋሉት የአሜሪካው ሚሺጋን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች፣ ነፍሳቱ በተፈጥሮ ያገኙት ይህ ብቃታቸው ካንሰር የሆኑ ህዋሶችን ለይተው ለማወቅ እንደሚያስችላቸው ማረጋገጥ ችለዋል።

ይህ ማለት ግን በሕይወት ያለ አንበጣን በሰውነት ላይ በማሯሯጥ ወይም በማስዋጥ ሆድ እቃ ውስጥ ገብተው እንዲመረምሩና እንዲያሳውቁ የሚደረግበት አይደለም። ሽታን ለይቶ የሚመራቸው የማሽተቻ ህዋሳቸው ላይ ያለውን ንጥረ ነገርንም ሆነ አሰራርን በማጥናት በዘመናዊ መሣሪያ አማካኝነት ተመሳሳዩን ፈብርኮ ጥቅም ላይ በማዋል አነፍንፎ በሽታው ያለባቸውን አካላት ለይቶ ማወቅ የሚያስችል ግኝት ነው ተብሎለታል።

ግኝቱ የታወቀው በሕይወት ያሉ አንበጣዎች ካንሰር ያለበትን ሕዋስ ከሌለበት አነፍንፈው መለየት መቻላቸው በቤተሙከራ ቀደም ብሎ ታውቆ ስለነበር ነው። የአንበጦችን የማሽተትና የመለየት ብቃት (insect olfactory neural circuits) ተጠቅመው የነፍሳቱን የተፈጥሮ ብቃት ጥቅም ላይ በማዋል ነው ዘዴውን ጥቅም ላይ ማዋል የቻሉት።

ካንሰር አምጪ ንጥረ ነገሮች ሰውነት ላይ ጉዳት በሚያደርሱበት ወቅት ያጠቁት ሕዋስ የተለየ ጠረን ማውጣቱን መለየት በመቻሉ ነበር ይህን ሽታ ለይቶ እንዲያሳውቃቸው የሚያስችላቸውን መንገድ ተመራማሪዎቹ ሲፈልጉ የቆዩት። ከዚህ ቀደም አንበጣዎች ተፈጥሮ የለገሳቸውን ብቃት ተጠቅመው ጠረንን ከሩቅ ጭምር መለየት መቻላቸው በመታወቁ፣ ለአሁኑ ምርምር እጩ አድርገው ሊጠቀሙባቸው ችለዋል።

የነፍሳቱን ተፈጥሮ መሠረት በማድረግ ዘመናዊ ሰው ሠራሽ መመርመሪያ ቁስን በመጠቀም የካንሰር ህዋስ መኖሩን ለማወቅ የሚያስችል የተለየ ግኝት መሆኑን ተመራማሪዎቹ ይፋ አድርገዋል። ውጤታማ ነው የተባለው ይህ የመመርመሪያ መንገድ እስካሁን ድረስ ተግባራዊ ከሚደረጉ መንገዶች የተለየ ነው ሲሉ የገለፁት ሲሆን፣ ቀላሉም መንገድ ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም አንድ ሰው ላይ ካንሰር መኖሩ የሚታወቀው የውጭ የሰውነት አካልን ወይም የውስጥ አካልን በመመርመር ነበር። ይህ መንገድ በቶሎ ለማወቅ ካለማስቻሉም በላይ አስተማማኝነቱ ያን ያህል እንዳልሆነ የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ። በተለይ በካንሰር የተያዙ ህዋሶች ገና ሳያድጉና እጢው ጎልብቶ ሳይስፋፋ በፊት ለመለየት ያስቸግር ነበር። ይህ በመሆኑም በቶሎ ያልታወቀን በጊዜ አክሞ እንዲያገግም ለማድረግ የሚካሄደውን ተግባር አስቸጋሪ ሲያደርገው ቆይቷል።

ካንሰር ያጠቃቸው ህዋሶች የተፈጥሮ ባህሪያቸውን የሚቀይሩ ወይም ‹ሚውቴትድ› የሆኑ በመሆናቸው አንበጣን በመሳሰሉ ነፍሳት የመለየት እድላቸው ከፍተኛ ነው ተብሏል። የካንሰር እጢዎች የተለያየ የሰውነት ክፍል ላይ እንደመገኘታቸው እነሱን በተመሳሳይ መንገድ ገና ከመነሻቸው ለይቶ ለማወቅ አስቸጋሪ እንደነበር የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚናገሩ ኔቸር ወርልድ ኒውስ ዘግቧል።

ሙሉ በሙሉ ከካንሰር የሚያድን ሕክምና እስካሁን የተገኘ ባይሆንም፣ ነፍሳት ለባዮ ኢንጂነሪንግ እያበረከቱ ካለው አስተዋፅኦ አንፃር ከፍተኛ ለውጥ ይገኛል ሲሉ በርካታ ተመራማሪዎች ተስፋ ያደርጋሉ። የዚህም ሙከራቸው አንድ አካል የሆነው የአሜሪካ ተመራማሪዎች የሰሞኑ ውጤት እንደሚያሳየው፣ አዲሱ ዘዴ በሽታው ላይ ለሚደረጉ ሌሎች ምርምሮችም እንደግብአት እንደሚያገለግል ነው።

የካንሰር በሽታን ዘግይቶ ለማከም ከማዳገቱ ባሻገር የታወቀበት ወቅት ለሕክምናው በጣም ወሳኙ ጉዳይ መሆኑ ይወቃል። ቢያንስ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስና ሕይወትን ለማራዘም የበሽታው መነሻ በቶሎ እንዲታወቅ ስለሚያስፈልግ እንዲህ ዓይነት በጊዜ የሚያሳውቁ መመርመሪዎች ጥቅማቸው የጎላ ነው ተብሏል።

ባዮአርካይቭ (BioRxiv) መጽሔት ላይ በወጣው በዚህ ግኝት መሠረት አንበጣዎች ጤነኛ ህዋስን በካንሰር ከተለከፈው መለየት ብቻ ሳይሆን፣ የተለያዩ የካንሰር ዓይነቶችንም የመለየቱ ብቃት እንዳላቸው ታውቋል።

የአንበጣዎች የተፈጥሮ የማሽተት ብቃት ላይ ተመርኩዞ ካንሰርን አነፍንፎ እንዲለይ ይሠራል የተባለው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ እንደዚህ ቀደሙ ሙሉ የሰውነት አካልን መመርመር አይጠበቅበትም ተብሏል። እንደተመራመሪዎቹ እምነት ተፈጥሮ ላይ የተመሠረተው ይህ መመርመሪያ መሣሪያ ከሰውነት ጋር ንክኪ እንዳይኖረው የታሰበ ነው። የተመርማሪውን ትንፋሽ በመውሰድ ሰውነቱ ውስጥ በካንሰር የተጠቃ ህዋስ ስለመኖሩ የሚታወቅበት እንደሚሆን የስራቸውን ውጤት ይፋ ባደረጉበት ፅሁፍ ላይ አመልክተዋል።

ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት፣ የፍጥረታት አፍንጫ ድንቅ የሆነ ብቃት ያለውና ገና ብዙ ያልተጠና መስክ እንደሆነ ነው። የማሽተት ብቃታቸው የተጎዳባቸውን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመተካት የሚደረግ ሙከራ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ የሚናገሩት ባለሙያዎች፣ እንደአፍንጫ በሰው ሰራሽ ዘዴ የተወሰኑ ነገሮችን እንዲለዩ ማድረጉ ለህክምናው ዘርፍ በጣም ጠቃሚ ነው።

አፍንጫዎች ከአቀማመጣቸው ጀምሮ የምንመገበውንም ሆነ የምንነካውን ነገር አጢነን እንድንለይና ጤናችንን እንድንጠብቅ ካላቸው ጥቅም አንፃር እስካሁን እምብዛም ጥቅም ላይ አልዋሉም። ተመራማሪዎቹ አርቲፊሻል ወይም ሰው ሠራሽ አፍንጫን ለመፈብረክ ከ15 ዓመት በላይ ቢመራመሩም፣ ከተፈጥሮው መርቀቅ የተነሳ እስካሁን ውጤታማ መሆን አልቻሉም። ነገር ግን፣ ከሰው ልጆች የስሜት ሕዋሳት በላይ የእንስሳትና የነፍሳት እንደተፈጥሯቸው የሚለያይ በመሆኑም፣ የእነሱን መሠረት በማድረግ ምርምሮች እየተካሄዱና አመርቂ ውጤት እየተመዘገበባቸው እንደሆነ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ።

ከጅምሩ አንስቶ በስሜት ሕዋሳታችን የማይታወቀው ካንሰር በሰውነታችን የሚከሰተው በካንሰር አምጪ ሕዋስ አማካኝነት ሲሆን፣ በማንኛውም የሰውነት ክፍል ላይ ተከስቶ በፍጥነት የሚስፋፋ ነው። በቀላሉም እጢው አድጎ በትሪሊዮን የሚቆጠሩ ሕዋሶችን ሊያበላሽ የሚችል እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ።

እንደዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ ካንሰር የዓለማችን ገዳይ ከሆኑ በሽታዎች መካከል ዋናው ነው። እስከ 2020 ድረስ ለ10 ሚሊዮን ሰዎች ሞት መንስዔ መሆኑ የተመዘገበ ሲሆን፣ ከስድስት ሟቾች አንዱ በካንሰር እንደሚሞት ታውቋል።

በካንሰር ሕይወታቸውን የሚያጡት ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣቱን ተከትሎ በጤና ባለሙያዎች ዘንድ መድኃኒት ለማግኘት ርብርብ ቢደረግም፣ እስካሁን ምንም አይነት ሙሉ ለሙሉ የሚያድን ሕክምና አልተገኘለትም። የሚያስከትለውን ጉዳት እና የህዋሶችን የፈጠነ ርቢ ለመቀነስ የሚያስችሉ የተለያዩ የተጓዳኝ ሕክምናዎች ቢሰጡም በቂ እንዳልሆኑ ይሰማል።

ለዚህም ሲባል በሽታውን የማወቂያ ወቅቱ ወሳኝ ሆኖ ይነገራል። ቶሎ ሳይስፋፋ የመገኘቱ አጋጣሚ ለማገገምና ሕክምናውን እየተከታተሉ ለመቆየት ሰፊ እድል ይሰጣል። ይህም የሚሆነው ኅብረተሰቡ ሕመም ተሰምቶት ሐኪም ጋር ሲሄድ ብቻ ሳይሆን፣ አስቀድሞ ለራሱ ሳይታወቀው በምርመራ እንዲታወቅለት በማድረግ ነው። ለዚህም የሚረዳ ትንፋሽን ተጠቅሞ የሚመረምር ዘዴን አገኘን ብለው የአሜሪካ ተመራማሪዎች ስለተናገሩ ነው በብዙ


ቅጽ 4 ቁጥር 198 ነሐሴ 14 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here