ላለፉት 10 ወራት ድጋፍ እንዳልተደረገላቸውም ተናግረዋል
በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ድባጤ ወረዳ የሚገኙ ከኹለት ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች ለእኛ የተላከው ሰብዓዊ ድጋፍ ተላልፎ ለጉምዝ ብሔረሰብ አባላት ተሰጥቶብናል ሲሉ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ አሰምተዋል።
በድባጤ ወረዳ በመጠለያ ጣቢያ ተጠልለው ያሉ ከኹለት ሺሕ በላይ ዜጎች ለ10 ወራት ያህል በተለያዩ ምክንያቶች የሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ክልሉ አልገባም በማለት የክልሉ መንግሥት ምንም ዓይነት ድጋፍ አላደረገልንም ብለዋል።
በእነዚህ ወራት የሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ክልሉ የገባበት ሂደት እንዳለ ያስታወሱት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ የተደጋጋሚ ቅሬታቸውን ወደ ጎን በመተው ለእነሱ መደረግ የነበረበትን የሰብዓዊ ድጋፍ ተላልፎ በወረዳው በጫካ ውስጥ መጠለያ ሠርተው ለሚኖሩ የጉምዝ ብሔረሰብ አባል ተብለው ለሚጠሩ ጎሳዎች የድባጤ ወረዳ አስተዳደር መስጠቱን ተናግረዋል።
እነዚህ ተፈናቃይ ዜጎች በፀጥታ ችግር ከተለያዩ ቦታዎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ቻግኒ ከተማ ከአራት ሺሕ በላይ የነበሩ ሲሆን፣ ከነሐሴ 2013 ጀምሮ ወደ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል እንደተመለሱ እና ከዚህ ውስጥ ከኹለት ሺሕ ያላነሱ ዜጎች በመተከል ዞን ድባጤ ወረዳ በመጠለያ ጣቢያ ተጠልለው የሚገኙ ናቸው።
ተፈናቃዮቹ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ድባጤ ወረዳ በሸራ መጠለያ ተሠርቶላቸው መኖር ከጀመሩ ዐስር ወራትን እንዳስቆጠሩ ተናግረዋል።
በመጠለያ ጣቢያ ተጠልለው በቆዩበት አንድ ዓመት ውስጥ ለአንድ ሰው 15 ኪሎ ግራም የስንዴ ምርት ለኹለት ጊዜ ብቻ ድጋፍ የተደረገላቸው ቢሆንም፣ ለ10 ወራት ያህል ግን ምንም ዓይነት የሰብዓዊ ድጋፍ እንዳልተደረገላቸው በመናገር ተፈናቃዮቹ እሮሯቸውን አሰምተዋል።
ተፈናቃዮች አክለውም፣ ድጋፍ ባልተደረጉባቸው ወራት በአካባቢው ከሚኖረው የማኅበረሰብ ክፍል የእለት ጉርስ እና እርዳታ በመጠየቅ ሕይወታችንን ለማቆየት ተገደናል ብለዋል።
በተቆጠሩት 10 ወራት ውስጥ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጉዳዩ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ተደጋጋሚ ቅሬታ ባቀረቡበት ወቅት፣ በፀጥታ ችግር እና በትራንስፖርት እጥረት ሳቢያ የሰብዓዊ ድጋፍ ወደ ክልሉ እንዳልገባላቸው የሚያስረዳ ምላሽ እንደሚሰጣቸው አስረድተዋል።
ይህ ምላሽ ከእውነታው የራቀ እንደሆነ እና የሰብዓዊ ድጋፉም ወደ ክልሉ ከመግባት ባለፈ ለሌላ ወገን ተላልፎ የሚሰጥበት ሂደት እንዳለ የጠቆሙት ተፈናቃዮች፣ ይህ ዓይነቱ አሠራር ተገቢነት እና ኃላፊነት የጎደለው በመሆኑ ይታወቅልን ብለዋል።
አዲስ ማለዳ ስለጉዳዩ የጠየቀችው የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የድባጤ ወረዳ ምክትል አስተዳደር ሀብታሙ አርጋሳ በበኩላቸው፣ በትራንስፖርት እጥረት ሳቢያ የሰብዓዊ ድጋፍ ወቅቱን ጠብቆ የማይመጣበት ጊዜ አለ ብለዋል።
ከዚህ አንፃር ለተፈናቃዮች በሚያዚያና በግንቦት ወር 2014 በወቅቱ የሰብዓዊ ድጋፍ ያልተደረገ ቢሆንም፣ በሌሎች ወራት ግን ድጋፉ አልተቋረጠባቸውም ይላሉ።
በወረዳው የሚገኙ የጉምዝ ብሔረሰቦችም ተፈናቃይ ዜጎች እንደመሆናቸው መጠን እንደማንኛውም ሰው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ያነሱት ምክትል አስተዳዳሪው፣ ከዚያ ባለፈ ግን የሌሎችን ተፈናቃይ ድጋፍ አሳልፈን አልሰጠንም ባይ ናቸው።
በቀጣይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር የሚቆራረጡ የሰብዓዊ ድጋፎችን ለማስተካከል እየሠሩ መሆናቸውን አክለው ጠቅሰዋል።
ከምሥራቅ እና ከምዕራብ ወለጋ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና ከሌሎች አካባቢዎችም ጭምር ሲፈጠሩ በነበሩ የፀጥታ ችግሮች ተፈናቅለው በመተከል፣ በካማሽ፣ በአሶሳ ዞን እና በተለያዩ ወረዳዎች በርካታ ተፈናቃይ ዜጎች ይገኛሉ።
ቅጽ 4 ቁጥር 198 ነሐሴ 14 2014



