መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናዶሮ አርቢዎች ንብረታቸውን ሸጠው ሥራ የማቆም አድማ ሊያደርጉ መሆኑ ተሰማ

ዶሮ አርቢዎች ንብረታቸውን ሸጠው ሥራ የማቆም አድማ ሊያደርጉ መሆኑ ተሰማ

ዶሮ አርቢዎች በእጃቸው ላይ የሚገኝ ንብረታቸውን በጅምላ ሸጠው ካጠናቀቁ  በኋላ ሥራ የማቆም አድማ ለማድረግ ማቀዳቸውን በኢትዮጵያ የተለያዩ የክልል ከተሞች የሚገኙ የዶሮ አርቢዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በዘርፉ የተሰማሩ አብዛኛዎቹ አርቢዎች እስከዛሬ ሲሸጡበት ከነበረው ዋጋ ቀንሰው ሙሉ ንብረታቸውን በማስረከብ ላይ መሆናቸውን የጠቆሙ ሲሆን፤ ለዶሮ እርባታ ሥራ መንግሥት በቂ ትኩረት ስላልሰጠበት ከትርፉ ይልቅ ጉዳቱ ሚዛን እየደፋ መምጣቱን በዝርዝር አብራርተዋል።

በሥራው የተሰማሩት ሰዎች በተናገሩት መሰረት፣ ከወራት በፊት ተከስቷል ተብሎ በነበረው ዶሮ ገዳይ ወረርሽኝ መንግሥት ባደረገው እገዳ በርካታ እንቁላል ባለመሸጡ ኪሳራ ስለገጠማቸው፤ የመኖ ዋጋ ስለተወደደባቸው እንዲሁም ክረምት በመጣ ቁጥር ሥራቸው ላይ ፈተና ስለሚሆንባቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

ሥራውን ለማቆም በሂደት ላይ መሆናቸውን የገለጹት ዶሮ አርቢዎቹ፤ ከምንም በላይ ግን የመኖ ዋጋ መጨመር ቀንደኛ ፈተና እንደሆነባቸው ነው የሚናገሩት። የአንድ ኩንታል መኖ ዋጋ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ኹለት ሺሕ ኹለት መቶ ብር እንደነበር ያስታወሱ ሲሆን፤ በዘንድሮው ዓመት ግን ወደ ሦስት ሺሕ አራት መቶ ከፍ ብሏል ነው ያሉት።

ደብረ ማርቆስ፤ ሐዋሳ፤ ደብረ ዘይት፤ አዲስ አበባ፤ ቢሾፍቱ የሚገኙ በዶሮ እርባታ ሥራ ከተሰማሩ ዓመታትን ያስቆጠሩ ዶሮ አርቢዎች፤ ያላቸውን ሸጠው ሥራ ለማቆም ከሚሯሯጡት ዶሮ አርቢዎች መካከል የተወሰኑት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ደብረ ማርቆስ አካባቢ ያሉ ዶሮ አርቢዎችም ሥራውን ለማቆም ለእርባታ የገዟቸውን ዶሮዎች እና እንቁላል ከስረው በመሸጥ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ኹሉም ዶሮ አርቢዎች ሥራ ካቆሙ ደግሞ ዶሮና የዶሮ ውጤት ማግኘት እንደማይቻልም ሳይናገሩ አላለፉም። ሐዋሳ ዙሪያ በተመሳሳይ ሥራ ተሰማርተው የሚገኙ ሰዎች በበኩላቸው፣ ያሏቸውን ዶሮዎች፤ እንቁላል እንዲሁም ትሪውን (የእንቁላል ማስቀመጫ) በመሸጥ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደገለጹት ከሆነ፤ እስከዛሬ 400 ብር ሲሸጡ የነበሩትን ዶሮዎች አሁን ላይ 250 ለመሸጥ ተገደዋል።

በኹሉም አካባቢዎች የሚገኙ አርቢዎች ወረርሽኙን በተመለከተ ተጥሎ በነበረው እገዳ በርካታ እንቁላል ከጥቅም ውጭ እንደሆነባቸው የገለጹ ሲሆን፤ ወረርሽኙ በደብረ ዘይት ለዛውም በአንድ ሰፈር በመከሰቱ መንግሥት እገዳ አድርጎ መቆየቱ <ሌላ ያሰበው ሴራ ስላለ ነው> ሲሉ በተደጋጋሚ ገልጸዋል።

በዶሮ አርቢዎቹ በኩል ኹለት ዓይነት አቋም መኖሩን አዲስ ማለዳ ሰምታለች። ከፊሎቹ ዘርፉን እየፈተነ ያለውን ችግር ተቋቁመን ሥራችንን እንቀጥላለን ባይ ሲሆኑ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ ያላቸውን ሽጠው አድማ እናድርግ ባይ ስለመሆናቸው ተነግሯል።

ችግሩን መቋቋም እንዳለባቸው ያመኑት ዶሮ አርቢዎች መንግሥት በወረርሽኙ ነጋዴዎችን ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ እገዳ የጣለው ነጋዴዎች በሚገጥማቸው ኪሳራ ተበሳጭተው ሥራ እንዲያቆሙ ለማድረግ መሆኑን በመረዳት ነው ብለዋል።

ቀሪዎቹ ደግሞ በመኖም መወደድም ሆነ ተጥሎ በነበረው እገዳ ሥራው ኪሳራ ውስጥ ስላስገባቸው ለመተውና ይህንኑ መንግሥት አስቦታል ያሉትን ሴራ ለማክሸፍ ኹሉም በዘርፉ የተሰማሩ ሰዎች ሥራ የማቆም አድማ እንዲያደርጉ በማመን መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎችና አቀነባባሪዎች ማህበር ሥራ አስኪያጅ ብርሃኑ ሚሊዮን በበኩላቸው፣ አብዛኛዎቹ በወረርሽኙም ሆነ በመኖ ዋጋ መወደድና በእንቁላል ዋጋ ማነስ ምክንያት በርካታ ዶሮ አርቢዎች ከሥራው ለመውጣት መወሰናቸውን ገልጸዋል።

ይህ ከሆነ በአንድ ወቅት የእንቁላል ዋጋ ከፍተኛ ዋጋ ላይ መድረሱ የማይቀር ስለሆነ በዘርፉ የተሰማሩት ሰዎች በነበሩበት እንዲቀጥሉ ከመንግሥት ጋር እየተነጋገርን ቢሆንም እስካሁን ችግሩ አልተቀረፈም ነው ያሉት።


ቅጽ 4 ቁጥር 198 ነሐሴ 14 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች