ሰኞ ነሐሴ 16 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ሩሲያ በፌደራል መንግስት እና በህወሃት መካከል ለሚደረገው ድርድር በአፍሪካ ህብረት በኩል እየተካሄደበት ያለውን ጥረት እንደምትደግፍ አስታውቃለች።
የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል ያለውን ኹኔታ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የወሰዳቸው እርምጃዎችም በአወንታዊንት መንገድ እንደምትቀበለውም ገልፃለች።
የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመረጃ እና ፕረስ ምክትል ጉዳዮች ዳይሬክተር ኢቫን ኔቻዬቭ፤ በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ህወሃት ዙሪያ ስለሚደረገው ድርድር መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም፣ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ለመፍታት በአፍሪካ ህብረት በኩል እየተካሄደበት ያለውን ጥረት ሩሲያ እንደምትደግፍ መናገራቸውን በአዲስ አበባ የሚገኘው የሩሲያ ኢምባሲ አስታውቋል።
ሩሲያ የፌዴራሉ መንግስት በትግራይ ክልል የተከሰተውን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት እያደረገው ያለውን ጥረት በአወንታዊንት እንደምትቀበለውም ተገልጿል።
የፌደራል መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ማወጁ፣ ተጥሎ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማንሳት፣ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለመጀመር በሂደት ላይ መሆኑ እና ሌሎች የሰላም አማራጮች እየተከተለ መሆኑ ግጭቱን ለማስቆም ጥሩ እርምጃ መሆኑም በመግለጫው ተመላክቷል።
በተጨማሪም፤ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ይፋ ያደረጉት ከህወሃት ጋር ያለምንም ቅድመ ኹኔታ በየትኛውም ቦታ እና ጊዜ ለመደራደር ዝግጁ መሆኑ ሌላኛው መልካም ነገር መሆኑም ተጠቅሷል፡፡
በአጠቃላይ ሩሲያ፤ ኢትዮጵያ ከህወሃት ጋር የተደረገውን ጦርነት ለመፍታት እየሄደችበት ያለውን ሂደት እንደምታደንቅ ገልጻ፤ “በአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎች” በሚለው መርህ መሰረት፤ የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ መልዕክተኛ ኦልሴጎን ኦባሳንጆ በኩል እየተካሄዱ ያሉ ጥረቶችን እንደምትደግፍም በመግለጫው አስታውቃለች።



