የመንግሥት እና የግል አጋርነት – በታዳሽ ኃይል ዘርፍ

0
913

ዕረቡ ነሐሴ 25 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የተፈጥሮ ታዳሽ ኃይል ምንጭ ያላት አገር መሆኗ ይታመናል። ነገር ግን በዛ አቅም መጠን ኃይል አመንጭታ ተጠቃሚ አልሆነችም።

በኢትዮጵያ የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሱልጣን ዋሊ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ከውኃ ሀብት 45 ሺሕ ሜጋ ዋት፣ ከጂኦተርማል 10 ሺሕ ሜጋ ዋት፣ ከንፋስ ኃይል 100 ጌጋ ዋት እንዲሁም ከፀሐይ ብርሃን ከፍተኛ ኃይል የማመንጨት አቅም አላት። ሆኖም እስከ አሁን መጠቀም የተቻለው ከውኃ ኃይል ሲሆን ይህም ከ5000 ሜጋ ዋት ያነሰ ነው ብለዋል።

ዘርፉ ከፍተኛ አቅም እንደሚፈልግ የጠቀሱት ዴኤታው፣ ረዘም ላለ ጊዜ መንግሥት ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ሲያፈስ እንደነበርና በመንግሥት ብቻ የተያዘ ጉዳይ ሆኖ እንደቆየ አንስተዋል። ‹‹የመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ አጋርነት አልተጠናከረም ነበር።›› ካሉ በኋላ ፖሊሲዎችን ከመከለስና ከማሻሻል ጀምሮ የግሉ ባለሀብት በዘርፉ እንዲሳተፍና የመንግሥትና የግል አጋርነት (Public-Private Partnership) እንዲፈጠር አሁን በርካታ እድሎች እንደሚከፈቱ አስረድተዋል።

ይህን የሰማነው ካለፈው ነሐሴ 23/2014 ጀምሮ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ካለው ዓለም ዐቀፉ የሶላር አላያንስ (International Solar Alliance) አራተኛው ቀጠናዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ነው።

ኮሚቴው በስብሰባው እስካሁን በነበሩት የሥራ ሂደቶች እና ስኬቶች እንዲሁም የወደፊት ዕቅዶች ላይ ዝርዝር ውይይቶችን እያከናወነ ሲሆን፣ በ2030 ለማከናወን ለታቀደው የሶላር ኢንቨስትመንት ሥራ የተበጀተውን 1 ትሪሊዮን ዶላር በምን መልኩ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ እየመከረ ይገኛል።

በዚህ ስብሰባ ላይ የዓለም ዐቀፉ የሶላር አላያንስ ዋና ዳይሬክተር አጃይ ማቱርን ጨምሮ የኢትዮጵያ የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ጊና፣ ማሊ፣ ጊኒ ቢሳው፣ ኮሞሮስ እና ሶማሊያ መንግሥታት ሚኒስትሮች ተሳታፊ ናቸው።

ኮሚቴው በትላንትናው እለት ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፤ አፍሪካ 10 ቢሊዮን ኪሎ ዋት ለማመንጨት የሚያስችል የተትረፈረፈ የፀሐይ ኃይልን ጨምሮ ለታዳሽ ኃይል የሚሆን ያልተገደበ እምቅ አቅም ያላት መሆኑ ተወስቷል። ይህን የፀሐይ ኃይል ጥቅም ላይ ለማዋልና ፈጣን ለውጥ ለማግኘትም ከፍ ያለ ኢንቨስትመንትና የአቅም ግንባታ ሥራዎች ብሎም የፖሊሲ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑ ተጠቅሷል።

ዓለማቀፉ የሶላር አላያንስ ይህን እውን ለማድረግ የፀሐይ ብርሃን መሰብሰቢያ መሣሪያዎችን፣ የፀሐይ ብርሃን መሰብሰቢያ ፓርክን እና የተቀናጀ ፋይናንስን ጨምሮ የተለያዩ መፍትሔዎችን በማመቻቸት ላይ መሆኑን አስታውቋል። ከዚህም በተጓዳኝ የፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ለማሰራጨት እና የፀሐይ ብርሃን ኃይልን ተደራሽ ለማድረግ 1 ትሪሊዮን ዶላር በጀት መያዙ በመግለጫው ተነግሯል።ዓለማቀፉ የሶላር አላየንስ ሕንድ እና ፈረንሳይ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ጫና የማያሳድር እና የአካባቢን ሥነ ምህዳር የሚጠብቅ የኃይል አማራጭ መፍትሔ ለመስጠት የፈጠሩት የጋራ ጥምረት ነው።

ጥምረቱ ወጪ ቆጣቢ እና ለውጥ አምጪ የኃይል መፍትሔ አማራጮችን በማዘጋጀት እና ለሁሉም ተደራሽ በማድረግ ሀገራት (በተለይም አባል ሀገራት) ዝቅተኛ የካርቦን ልቀትን እንዲያዳብሩ ለማገዝ ይሠራል።

የቀጠናው ኮሚቴ ስብሰባ ዛሬ ነሐሴ 25/2014 ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here